ፈልግ

ስለ ወንጌል ተልዕኮ የሚገልጽ አዲስ መጽሐፍ፣ ስለ ወንጌል ተልዕኮ የሚገልጽ አዲስ መጽሐፍ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ እገዛ የወንጌል ተልዕኮን መፈጸም አይቻልም”!

ባለውፈው የጎርጎሮሳዊያኑ ጥቅምት ወር ታስቦ ያለፈውን የወንጌል ተልዕኮ ወርን መሰረት አድርጎ በታተመው መጽሐፍ፣ የወንጌል ተልዕኮን አስመልክቶ ለቀረበላቸው በርካታ ጥያቄዎች ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መልስ መስጠታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል።  ቅዱስነታቸው በዚህ ቃለ ምልልሳቸው “ወንጌልን ለዓለም የማታበስር ቤተክርስቲያን እንደ ቤተክርስቲያን ልትቆጠር አትችልም ማለታቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ መስቀል ስጦታን ሲያበረክቱ፣
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ መስቀል ስጦታን ሲያበረክቱ፣

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥቅምት 12/2010 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የወንጌል ልኡካን ቀን በተከበርበት ዕለት ልዩ የወንጌል ልኡካን ቀን በ2012 ዓ. ም. እንደሚከበር መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ለሕዝቦች የሚቀርበውን የወንጌል ተልዕኮ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በአዲስ ተነሳሽነት መጀመር እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸው ይታወሳል። በዚህ ርዕሥ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰፋ ያለ ሃሳብ ያካፈሉበትን መጽሐፍ ጃኒ ቫሌንቴ ለሕትመት ማብቃቱ ታውቋል።

ቤተክርስቲያን ለወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት መነሳቷ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጣት ትዕዛዝ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እና የእርሱን መልካም ዜና ለዓለም ለማዳረስ ቆርጦ መነሳትን እንደሚያስፈልግ ማሳሰባቸውን ፊደስ የተባለ የዜና ማዕከል አስታውቋል። የዜና ማዕከሉ ከዚህ ጋር በማማያዝ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቤተክርስቲያን ለወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት መነሳት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጣት ትዕዛዝ እንደሆነ መናገራቸው በመጽሐፉ ተገልጿል። ይህ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ትዕዛዝ ወንጌላዊው ማርቆስ እንደገለጸው የወንጌል ልኡካኑ ወደ ዓለም ሁሉ እንዲሄዱ የሚጠይቅ መሆኑን ይናገራል። ለወንጌል ተልዕኮ ያልቆመች ቤተክርስቲያን እንደ ቤተክርስቲያን ልትቆጠር አይቻላትም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተክርስቲያን የወንጌል አገልግሎትን ለማበርከት በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የማትገኝ ከሆነ ዓላማዋን ዘንግታለች፣ አገልግሎቷንም ታዛባለች ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ይህች ቤተክርስቲያን የተጠራችበትን ቀዳሚ ዓላማ የዘነጋች፣ ሥነ ምግባርን እና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ለማስተላለፍ የቆመች የባለ ብዙ ድርጅቶች ማኅበር ብቻ እንጂ ቤተክርስቲያን ተብላ ልትጠራ የምትችል አይደለችም ብለዋል።  ቅዱስነታቸው በማከልም ቤተክርስቲያን ተብላ የማትጠራበት ዋናው ምክንያት የኢየሱስ ክርስቶስን ታላቅ ሥራ ከመመስከር እና ከእርሱ ጋር ከመገናኘት ይልቅ የግል ዕቅዶቿን እና ፍላጎቶቿን ለመፈጸም ስለምትጥር ነው ብለው የወንጌልን መልካም ዜና ለማብሰር የተነሳች ቤተክርስቲያን አገልግሎቷን ለመፈጸም የሚያስችላት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ እና ሃይልን እና ጥበብን የሚሰጥ መንፈስ ቅዱስ ነው ብለዋል።    

የሐዋርያትን ፈለግ መከተል፣

አዲስ በወጣው መጽሐፍ ውስጥ በሰፈሩት ቃለ ምልልሶች ውስጥ የሐዋርያትን ሥራ በመጥቀስ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያት ያከናወኑ ለነበሩት አገልግሎት በሙሉ ቀዳሚ ተዋናይ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያስረዱት ቅዱስነታቸው አስራ ሁለቱ ሐዋርያት ለአገልግሎታቸው ስኬት ከመንፈስ ቅዱስ ያገኙት ሃይል እና ብርታት የሁል ጊዜ ምሳሌ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ሐዋርያት በአገልግሎታቸው ሁለተኛውን ደረጃ እንደሚይዙ፣ ለአገልግሎት የሚያዘጋጃቸው፣ ፈጻሚውም መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አስረድተው በምስጢረ ጥምቀት የምንቀበለው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለወንጌል አብሳሪነት ብቁ ያደርገናል ብለዋል። የወንጌል ተልዕኮ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እንደሆነ ያስረዱት ቅዱስነታቸው የወንጌል ማብሰር አገልግሎት ያለ መንፈስ ቅዱስ እቅድ እና ብርታት የሚጀመር ካልሆነ አንዳንድ ጊዜ ግባቸውን ሳይደርሱ እንደሚፈርሱ ማሕበራዊ አገልግሎቶች ይሆናል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን የምታድገው በኢየሱስ ፍቅር በመማረክ ነው፣

“ቤተክርስቲያን የምታድገው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ስትማረክ ነው” ያሉትን የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛን መልዕክት ያስታወሰው መጽሐፉ፣ ቤተክርስቲያን ሰዎችን መጋበዝ የምትችለው የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በመመስከር መሆኑን አስገንዝቧል። የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ መመስከር ማለት ደግሞ አሳማኝ ምክንያቶችን አቅርቦ ግንዛቤን በማስጨበጥ፣ ግፊትን በማድረግ ወይም በጠረጴዛ ዙሪያ የተደረገውን ውሳኔ ለማስፈጸም የራስ ተነሳሽነትን መውሰድ ሳይሆን ከሁሉ አስቀድሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በመማረክ እና ለእርሱ በመገዛት እንደሆነ በመጽሐፉ ውስጥ ተገልጿል። በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር መማረካችንን ሌሎች በቀላሉ ሊረዱት እንደሚችሉ በመጽሐፉ ተገልጾ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም እንደተናገሩት የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ማደግ ወይም የቤተክርስቲያን እድገት እንደ አንድ ሕዝባዊ ድርጅት የአገልግሎት ዘርፍ ማደግ ወይም በርካታ ተመልካቾች የሚገኙበት ትርዕት ለማዘጋጀት ማስታወቂያዎን ማዳረስ ሳይሆን አስገራሚ እድገቶችን በማሳየት፣ ካለ ኢየሱስ ክርስቶስ መሪነት ምንም ዓይነት ለውጥን ወይም እድገትን ማምጣት እንደማይቻል ግንዛቤ የሚገኝበት አገልግሎት መሆኑ ተገልጿል።

ምዕመናንን እምነት ማስቀየር ሁከትን ይፈጥራል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቃለ ምልልሳቸው በማንኛውም የሐይማኖት ተቋም ውስጥ የተከታዮችን ቁጥር የማሳደግ ሃሳብ እና ምኞት እንዳለ ገልጸው ይህም በየቁምስናዎች፣ በክርስቲያን ማሕበረሰብ፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እና በሃይማኖታዊ ጉባኤዎች ውስጥ ይታያል ብለዋል። ይህ በሚደረግበት ወቅት በምዕመናን መካከል ሁከት ይፈጠራል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ የሚሆነውም የምዕመናንን የእምነት ነጻነት፣ እምነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበትን ትክክለኛ መንገድ ስለማይከተል ነው ብለዋል። የወንጌልን መልካም ዜና ማብሰር ማለት ምዕመናን ለሚያደርጉት ተስፋ እውቅናን መስጠት፣ የወንጌል ምስክርነትን ያለተጨማሪ ማግባቢያ ንግግር መስጠት እንደሚያስፈልግ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የገለጠልን የማዳን ሃይል የሰዎችን ልብ ለመስበር በቂ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 November 2019, 16:35