ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የግብጹን ኢማም አህመድ አል ጣይብን በቫቲካን ተቀብለዋቸው፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የግብጹን ኢማም አህመድ አል ጣይብን በቫቲካን ተቀብለዋቸው፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የግብጹን ኢማም አህመድ አል ጣይብን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት ዓርብ ህዳር 5/2012 ዓ. ም. ከግብጹ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም የሆኑትን አህመድ አል ጣይብን በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸውን ከቫቲካን ዜና አገልግሎት የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ከተቀበሏቸው እንግዶች መካከል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጠቅላይ ሚንስትር ሳይፍ ቢን ዛይድ አል ናያን፣ በቅድስት መንበር የግብጽ ሪፓብሊክ መንግሥት አምባሳደር የሆኑት ክቡር ማሕሙድ ሳሚ እና በግብጽ የአል አዛር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተወካዮች መገኘታቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳስታወቀው እንግዶቹ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉት ውይይት ያተኮረው ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም አህመድ አል ጣይብ በተባበሩት አረብ ኤምረቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ በሕብረት ሆነው ያጸደቁት የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ተግባራዊነት ላይ መሆኑን መግለጫው አስታውቋል። ያለፈው ዓመት በነሐሴ ወር ላይ የተቋቋመው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ምክር ቤት ዋና ተልዕኮ፣ በጋራ በምንኖርባት ዓለማችን ሰላምን ማንገሥ እና ተቻችል የመኖርን ባሕል ለማሳደግ መሆኑን ጋዜጣዊ መግለጫው አስታውሷል። ትናትን ዓርብ ህዳር 5/2012 ዓ. ም. በተካሄደው ከፍተኛ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች መካከል ከቅድስት መንበር በኩል በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ የግል ጸሐፊ የሆኑት፣ ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ላዚ ጋይድ መገኘታቸው ታውቋል።

በዕለቱ ከተወያዩባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል በዲጅታሉ ዓለም በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ተባበሩት አረብ ኤምረቶች ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት እና በሁለቱ የሐይማኖት ተቋማት መካከል ሰብዓዊ ወንድማማችነትን፣ ሰላምን እና አንድነትን ለማሳደግ የተቋቋመው ምክር ቤት የእስካሁን ተግባር ተመልክተው ተጨማሪ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ዶ/ር ኢሪና ጆርጂቫ ቦኮቫን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መተዋወቃቸው ታውቋል። የሰብዓዊ ወንድማማነት ምክር ቤት በማከልም ባለፈው መስከረም 2012 ዓ. ም. በኒው ዮርክ በይፋ የተጀመረው እና “የአብርሐም ቤት” በመባል የሚታወቀው የሕንጻ ሥራ ፕሮጀችት የደረሰበት ደረጃ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሪፖርት ማቅረቡ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
16 November 2019, 16:35