ፈልግ

በበለጸጉ አገራት ውስጥ ለሕይወት ስሜት የማጣት ትልቅ አደጋ እየተከሰተ ይገኛል!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በኅዳር 17/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ተለመደውና ከእዚህ ቀድም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ጀምረውት የነበረ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል የነበረ ሳይሆን በሚትኩ በቅርቡ ከኅዳር 09-16/2012 ዓ.ም ድረስ በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል አድረገውት ስለነበረው 32ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት የተሳካ ይሆን ዘንድ አስተዋጾ ላደረጉ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች የምስጋና መልእክት ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር እንደ ገለጹት “በበለጸጉ አገራት ውስጥ ለሕይወት ስሜት የማጣት ትልቅ አደጋ እየተከሰተ ይገኛል!” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 17/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቅርቡ ከኅዳር 09-16/2012 ዓ.ም ድረስ በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል አድረገውት ስለነበረው 32ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት የተሳካ ይሆን ዘንድ አስተዋጾ ላበረከቱ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች የምስጋና መልእክት አስተላልፈዋል፣ የእዚህን መልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በታይላንድ እና በጃፓን ሳደርገው የነበረውን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቂቄ ትላንት (ኅዳር 16/2012 ዓ.ም) የተመለስኩኝ ሲሆን ለእዚህ ለተሰጠኝ ጸጋ ጌታን እጅግ በጣም አስመሰግናለሁኝ። ለጋበዙኝ እና በታላቅ ደስታ ለተቀበሉኝ፣ ለእነዚያ ሁለት ሀገራት ባለሥልጣናት እና ጳጳሳት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የታይላንድ እና የጃፓንን ህዝብ ለማመስገን እፈልጋለሁ። ይህ ጉብኝት ለእነዚያ ህዝቦች ያለኝን ቅርበት እና ፍቅር እንዲጨምር አድርጉዋል፡ እግዚአብሔር በተትረፈረፈ ብልፅግና እና ሰላም ይባርካቸው ።

በታይላንድ የነበረው ጥንታዊ ስረወ መንግሥት በአሁኑ ወቅት እጅግ ዘመናዊ ሁኑዋል። ከንጉሱ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር በተገናኘሁበት ወቅት የታይላንድ ሕዝቦች ስላላቸው ቱባ የሆነ መንፈሳዊ እና ባህላዊ እሴቶች ገልጬ የነበረ ሲሆን በእዚያም በነበረኝ ቆይታ ሕዝቡ “በውብ ፈገግታ” የተሞላ እንደ ሆነ በመግለጽ ምስጋናዬን አቅርቢያለሁ። እዚያ ያሉት ሰዎች በፈገግታ የተሞሉ ናቸው። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ በኢኮኖሚ ልማት ሁሉም ሰው ተጠቃሚ እንዲሆን እና የጉልበት ብዝበዛ የሚፈጸምባቸው በተለይም ሴቶችን እና ለአቅመ ሔዋን/አዳም ያልደርሱ ታዳጊ ሕጻናት ላይ የሚፈጸመው የጉልበት ብዝበዛ ለማስቀረት ባለስልጣናቱ እንዲሰሩ እና ቁርጠኛ እንዲሆን አበረታትቻለሁ። የቡድሃ ሃይማኖት የዚህ ህዝብ ታሪክ እና ሕይወት ዋና አካል ነው፣ ስለሆነም በአገሪቷ የሚገኘው የቡድሃ እምነት ዋና መሪ የሆኑትን ጎብኚቼ የነበረ ሲሆን ከእኔ ቀደም የነበሩት ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት የጀመሩትን የጋራ የመከባበር መንገድ ላይ በመቀጠል፣ በዚህም በዓለም ውስጥ የርኅራኄ እና የወንድማማችነት መንፈስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩሌን አስተዋጾ እንደ ማበረክት ገልጬላቸዋለሁ። በዚህ ረገድ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኘው ትልቁ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተካሄደው የሐይማኖት ሕብረት እና ከእዚህ ጋር ተያያዢነት ያላቸው ስብሰባዎች መካሄዳቸው እጅግ ወሳኝ የነበረ አጋጣሚ ነው።

በታይላንድ ውስጥ ያላቺው ቤተክርስቲያን እየሰጠችው የምትገኘው ምስክርነት ለሕሙማን እና አቅመ ደካማ ለሆኑ ሰዎች በምትሰጠው አገልግሎት የታጀበ ነው። ከነዚህ ተግባራት ውስጥ አንዱ የሆነውን የቅዱስ ሉዊስ ሆስፒታል እየሰጠ የሚገኘውን የላቀ አገልግሎት በሥፍራው ተገኝቼ የጎበኘው ሲሆን በእዚያ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰሩትን የጤና ባለሙያዎችን እና ከተወሰኑ ሕሙማን  ጋር በተገናኘውበት ወቅት ይህንን እየሰጡት የሚገኘውን አገልግሎት አጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ አበረታትቻቸዋለሁ። ከዚያ በመቀጠል በአገሪቷ ውስጥ ለሚገኙ ካህናት እና ገዳማዊያን/ገዳማዊያት፣ ከብጹዓን ጳጳሳት እና እንዲሁም ከወንድሞቼ የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባላት ጋር ቆታ አድርጊያለሁኝ። በባንኮክ በሚገኘው በካቴድራል ውስጥ ለተገኙ ወጣቶች መስዋዕተ ቅዳሴ አሳርጊያለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ በተመሠረተው አዲሱ ቤተሰብ ውስጥ የታይላንድ ሕዝብ ፊቶች እና ድምጾች ውስጥ መኖራቸው ይንጸባረቃል።

ከዚያ በመቀጠል ያቀናሁት ወደ ጃፓን ነበር። በቶኪዮ በሚገኘው የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት መኖሪያ በደረስኩበት ወቅት በአገሪቷ የሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት አቀባበል ያደረጉልኝ ሲሆን ወዲያውኑ የአንዲት ትንሽዬ ቤተክርስትያን እረኛ መሆን የራሱ የሆነ ተግዳሮቶች ያሉት መሆኑን የተነጋገርን ሲሆን ነገር ግን የሕይወት ምንጭ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ወደ እዚያ አገር በማምጣታቸው የተነሳ ሊጽናኑ እንደ ሚገባ ገልጨላቸዋለሁ።

በአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ የተነሳ ከፍተኛ ጠባሳ ጥሎ ያለፈባትን ጃፓን እና እንዲሁም ለመላው ዓለም መሠረታዊ መብቶች እና ሰላም ቃል አቀባይ በመሆን “እያንዳንዱን ሕይወት መንከባከብ ይገባል” የሚል መሪ ቃል በማንገብ ነበር የጃፓንን ጉብኝት የጀመርኩት። በናጋሳኪ እና በሂሮሻማ ጸሎት አድርጊያለሁኝ፣ በእዚህ የአቶሚክ ቦንብ ሰለባ የሆኑ ሰዎች የተወሰኑ ቤተሰቦችን ተገናኝቻለሁ፣ እናም የአቶሚክ የጦር መሳሪያ ቦምቦችን ማምረት እና በመሸጥ ስለ ሰላም ማውራት ግብዝነት መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዣለሁ። ከዚያ አደጋ በኋላ ጃፓን ለሕይወት ክብር መስጠት ያስቻላትን ከፍተኛ የሆነ ችሎታ አሳይታለች። እ.ኤ.አ. በ2011 ዓ.ም በመሬት መንቀጥቀጥ እና በሱናሚ አደጋዎች ምክንያት በኒውክለር የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የተከሰቱትን አደጋዎች ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች።

ሕይወትን ለመንከባከብ በቅድሚያ ሕይወትን መውደድ ይገባል፣ ዛሬ እጅግ በጣም ባደጉ አገራት ውስጥ እየተከሰተ የሚገኘው አደገኛ ነገር ለኑሮ ስሜት ማጣት ነው። ሕይወታቸው ባዶ እንደ ሆነ የሚሰማቸው ተጎጂዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ ወጣቶች ናቸው፣ ስለሆነም በእዚህ የተነሳ በቶኪዮ ውስጥ ለወጣቶች ብቻ የተዘጋጀ አንድ ስብሰባ አድርገናል። ጥያቄዎቻቸውንና ሕልሞቻቸውን አዳምጬ ነበር፣ ሁሉም ማነኛውንም ዓይነት የጉልበተኛነት ስሜት እንዲያስወግዱ እና እንዲቃወሙ፣ እራሳቸውን ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ፣ በጸሎት እና ለሌሎች አገልግሎት ራሳቸውን በመክፈት ፍርሃትንና ብቸኝነትን እንዲያሸንፉ አበረታትቻቸው ነበር። ከወጣቶች ባሻጋር ከመምህራን ማኅበርሰብ ጋር በመሆን “ሶፊያ” በመባል የሚታወቀውን ዩኒቬርሲቲ ጎብኝቻለሁኝ። ይህ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሁሉም የካቶሊክ የትምህርት መስጫ ተቋማት በጃፓን ውስጥ በጣም ታዋቂ የሆነ ተቋም ነው።

በቶኪዮ የምስጋና መግለጫዬን ለማቅረብ ያስችለኝ ዘንድ የአገሪቷ ንጉሠ ነገሥት የሆኑትን ኑሩሂቶን ለመጎብኘት እድል አግኝቼ ነበር፣ በአገሪቷ ከሚገኙ ባለሥልጣናትና ከዲፕሎማሲ ልዑካን ጋር ተገናኝቼ ነበር። በጥበብ እና አድማሰ ሰፊ በሆነ መልኩ በመግባባት ላይ የተመረኮዘ የውይይት ባህል ሊኖር እንደ ሚገባ ገልጫለሁ። ለሐይማኖታዊ እና ሥነ ምግባራዊ እሴቶቻቸው ታማኝ በመሆን እና ለቅዱስ ወንጌል መልእክት ራሳቸውን  ክፍት በማደረግ፣ ጃፓን ይበልጥ ፍትሃዊ እና ሰላማዊ፣ በሰው እና በተፈጥሮ መካከል የተጣመረ ስምምነት እና ሕብረት ያለባት አገር ልትሆን እንደ ምትችል ጨምሬ ተናግርያለሁ።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ የታይላንድን እና የጃፓን ህዝቦችን የእግዚአብሔር ቸርነት እና ደህንነት በአደራ እንስጥ። እናመሰግናለሁ።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 November 2019, 15:52