ፈልግ

ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች ንግግር ሲያደርጉ፣  ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች ንግግር ሲያደርጉ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በመንግሥት አመራር ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ማደግ ያስፈልጋል አሉ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበው ለእርሳቸው እና ለጉባኤው ተካፋዮች ንግግር ያደረጉትን በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋሬል ምስጋናቸው አቅርበውላቸዋል።    

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ማደግ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ምክር ቤቱ በሚቀጥሉት ዓመታት ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ጠቃሚ መመሪያዎችን አስተላልፈው በቅድስት መንበር ሥር በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ሁለት ዓመት ገደማ የሚሆነው የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ከቅድስት መንበር ጋር ለመተባበር የተቋቋመ መሆኑን አስረድተዋል። ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማውያት፣ ምዕመናን ተባብረው መላዋ ቤተክርስቲያንን ለማገልገል መጠራታቸውን ገልጸው፣ የቤተክርስቲያን መሠረት ለሆነው የምዕመናን እና የቤተሰብ ሕይወት ማደግ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያን አባል የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ አሳስበዋል። የእያንዳንዱ ምዕመን እገዛ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት ከግለኝነት አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ ሌሎችም ዘንድ ለመድረስ ያስችላል ብለዋል።

ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በተወለዱበት፣ ባደጉበት፣ መንፈሳዊ ትምህርቶችን በተከታተሉበት ሀገረ ስብከት ተወስና የምትቀር አይደለችም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን እጅግ ሰፊ እና ዓለም አቀፋዊት መሆኗን አስረድተዋል። የቤተክርስቲያን ልብ እንዲኖር ያስፈልጋል ማለት ነገሮችን ሰፋ በማድረግ በካቶሊካዊ ዓይን መመልከት ማለት ነው ብለው የሁላዊት ቤተክርስቲያን ልጆች መሆን ማለት በጠቅላላው የቤተክርስቲያን ሕይወት አባል መሆኑን አስረድተዋል።

እያንዳንዱ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምዕመን ከተሰማራበት የሥራ ዘርፍ፣ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹን መጥቀስ ካለብን፣ የስነ መለኮት ትምህርት ሊቅ፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር፣ የሕክምና ዶክተር፣ መምህር፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት አሰልጣኝ፣ እነዚህ በሙሉ ከተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ በተጨማሪ የአገልግሎት አድማሳቸውን በማስፋት የእናት ቤተክርስቲያንን ፈለግ መከተል እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል። በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አባላት በሙሉ በሥራ ዓመታት ውስጥ ያካበቱትን ልምድ እና እውቀት በመጠቀም እናት ቤተክርስቲያን የምትጠይቃቸውን የሐዋርያዊ አገልግሎት ድርሻን እንዴት ልወጣው እችላለሁ በማለት ራሳቸውን መጠየቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አድልዎን እና ልዩነትን ያማታደርግ እናት ቤተክርስቲያን፣ በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ የልጆቿን ሕብረት ማየት እንደምትፈልግ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ፣ በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት አባላትም የቤተክርስቲያናቸውን አቋም በግልጽ በማሳየት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምዕመናን፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን፣ የሀገረ ስብከት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች፣ በቁምስና ውስጥ የተዋቀሩ የወጣት እና የጎልማሳ ማሕበራት በሙሉ በመካከላቸው እውነተኛ ሕብረትን ለማሳደግ ጥሩ ምሳሌ ሆነው እንዲገኙ አሳስበዋል። የመላዋ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምእመናን ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገትን እንዲያሳዩ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው እነዚህ ምዕመናን በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን እንቅፋቶች አልፈው፣ ፍራቻን አስወግደው በድፍረት ዕውቀታቸውን እና ተሰጥኦዋቸውን ተጠቅመው በፖለቲካም ሆነ በባሕል ዘርፍ በንቃት በመሳተፍ የሚኖሩበትን ማሕበረሰብ ማገልገል በሚችሉበት በአዲስ ተልዕኮ ውስጥ መሳተፍ ያስፈልጋል ብለዋል። ቤተክርስቲያን በተስፋ የምትኖር መሆኗን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእርሳቸው በፊት መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ያገለገሉት ሁለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያበረከቷቸውን መልካም ተግባራት በማስታወስ እንደተናገሩት፣ እናት ቤተክርስቲያን እስካሁን የኖረችበትን መንፈሳዊ ባሕሏን ተንከባክባ አቆይታዋለች ብለዋል።

በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የእይታ አድማሱን ሰፋ ማድረግ በተለያዩ ማሕበራዊ መዋቅሮች ውስጥ ለሚገኙት ወንድሞች እና እህቶች ፍሪያማ ሐዋርያዊ አገልግሎቱን በማበርከት ለእናት ቤተክርስቲያን ትልቅ አጋዥ እንደሚሆን አስረድተው በምስጢረ ጥምቀት የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች የሆኑት ሁሉ በደስታ ሐዋርያዊ ተልዕኮዋቸውን መፈጸም ይችላሉ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ለቤተክርስቲያን የሚያበረክተው አገልግሎት ፍሬያማ እንዲሆን ለማድረግ የሚያግዙ ሁለት ሃሳቦችን አስታውሰው እነዚህም እናት ቤተክርስቲያንን በትክክል የምትገልጽ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መመልከት ያስፈልጋል ብለው ሁለተኛው ሐዋርያት በወንድማማችነት እንዲኖሩ በማለት የልጇን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ማስተማሯን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ጳጳስዊ ምክር ቤቱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጎን በመሆን ከቅድስት መንበር ጋር እንዲተባበር ጠቀው የሚያበረክቱት አገልግሎት ለእያንዳንዱ ምዕመን እና ለመላዋ ቤተክርስቲያን እድገት እንዲሆን ከጠየቁ በኋላ ሐዋርያዊ ቡራኬ አቸውን ሰጥተው የጉባኤው ተካፋዮች በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
16 November 2019, 16:42