ፈልግ

በስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ ለቅዱስነታቸው አበባ ተበርክቶላቸዋል፣  በስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ ለቅዱስነታቸው አበባ ተበርክቶላቸዋል፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በታይላንድ እና ጃፓን ያሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከህዳር 9-16/2012 ዓ. ም. ጀምሮ የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች በሆኑት ታይላንድ እና ጃፓን ያደረጉትን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት መፈጸማቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ኤማኑኤላ ካምፓኒለ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ከጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ አውሮፕላን ማረፊያ ከመነሳታቸው በፊት በሥፍራው ለተገኙት ከፍተኛ የመንግሥት እና ሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በአውሮፕላን ጣቢያ በተደረገ የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ ለቅዱስነታቸው አበባ ተበርክቶላቸዋል።  በታይላንድ እና በጃፓን ባደረጉት ስምንት የሐዋርያዊ ጉብኝት ቀናት ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች፣ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ሕዝባዊ ማሕበራት ተወካዮች፣ ከካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ካቶሊካዊ ምዕመናን ወጣቶች እና ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማዕከላት ሠራተኞች ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው እና መልዕክት ማስተላለፋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በእነዚህ አገራት ውስጥ የተዘጋጁ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓትን መምራታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአቅመ ደካሞች እና በድሆች ላይ የሚደርሰው ጭቆና እንዲያበቃ፣ በሕይወት እና በተፈጥሮ ሃብት ላይ የደረሰው አደጋ እንዳይደገም፣ አውዳሚ የሆነ አቶሚክ የጦር መሣሪያ ምርት ቆሞ ለሕይወት በሙሉ አስፈላጊው እንክብካቤ እና ጥበቃ እንዲደረግ፣ የወጣቶች ሕይወት በወንድማማችነት ባሕል ላይ እንዲገነባ የሚያሳስቡ ጠንካራ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ መቆየታችው ታውቋል። መላውን ሕይወት ከሞት አደጋ መታደግ ሰብዓዊ ክብርን ማስጠበቅ እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስገንዝበው የጋራ ውይይት አስፈላጊነትን በመረዳት የሐይማኖት ተቋማት የሚጫወቱት ሚና ፍትሕ ያለበትን ማሕበረሰብ ለመገንባት እና ለሰብዓዊ መብቶች ክብርን ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ሰብዓዊ ወንድማማችነትን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክታቸው ሰንዱ በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች መካከል ስለሚደረግ የጋራ ውይይት ብቻ ሳይሆን ከተቀሩት የሐይማኖት ተቋማት መካከልም ዘላቂ ውይይቶች እንዲደረጉ የሚያሳስብ ሰነድ እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቶኪዮ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው ጉዞአቸውን ወደ ሮም ካቀኑ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ለጃፓኑ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊነታቸው ኑሩሂቶ የቴሌግራም መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በዚህ መልዕክታቸው ወደ ጃፓን ሲደርሱ ላደረጉላቸው የክብር አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው ከመላው የጃፓን ሕዝብም ለተደረገላቸው መስተንግዶ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ በዘወትር ጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው በማረጋገጥ መለኮታዊ ቡራኬአቸውን ልከውላቸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 November 2019, 18:52