ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሁሉ አቀፍ ኤኮኖሚያዊ እድገት አስተባባሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ሆነው፣   ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሁሉ አቀፍ ኤኮኖሚያዊ እድገት አስተባባሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ሆነው፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ክፍፍል ስነ ምግባርን የተከተለ እንዲሆን አሳሰቡ።

ትናንት ህዳር 1/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው የሁሉ አቀፍ ኤኮኖሚያዊ እድገት አስተባባሪ ምክር ቤት ተወካዮች ባስተላለፉት መልዕክታቸው በምጣኔ ሃብት እድገት ውስጥ ለሰው ልጅ ቅድሚያን የሚሰጥ፣ ስር ነቀል ለውጥን ያደረገ ልብ እና አእምሮ እንዲኖር ያስፈልጋል ብለው የሚያስፈልገው ብዙ እንዲኖረን ሳይሆን ብዙዎች ሆነን መገኘት ነው ማለታቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ ዴቦራ ዶኒኒን የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ያለውን ድህነት፣ በስፋት የሚታየውን የኑሮ አለመመጣጠን፣ ፍታሃዊ ያልሆነ የምጣኔ ሃብት ክፍፍልን የሚያስወግድ እና አንገብጋቢ የሆኑ የዓለማችን የእድገት ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል የምጣኔ ሃብት ስርዓት መዘርጋት አስቸኳይ ተልዕኮ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። “ፎርቹን ታይም” የተባለ ድርጅት በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ. ም. በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ፎረም ላይ ያቀረበውን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ የተናገሩት ቅዱስነታቸው አሁን የምንጠቀምበት የምጣኔ ሃብት ስርዓት በርካታ የማሕበረሰብ ክፍሎችን ከሚመኙት የእድገት ደረጃ ያገለለ፣ ጥቂት ሰዎች ብቻ በምጣኔ ሃብት እንዲበለጽጉ የሚያደርግ በመሆኑ ይህን በሰዎች መካከል የተፈጠረውን የዕድገት ክፍተት መቀነስ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሦስት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ርዕሠ ጉዳይ ላይ የተወያየ የሁሉ አቀፍ ኤኮኖሚያዊ እድገት አስተባባሪ ምክር ቤት ተወካዮችን ተቀብለው ማወያያታቸው ሲታወስ ከእነዚህም መካከል በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን መገኘታቸው ታውቋል።

የልግስና ሞዴሎችን መከተል ያስፈልጋል፣

የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ እና የሥራ ዕድሎችን የሚከፍቱ ተቋማትን ማበረታታት አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝም፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንዳሳሰቡት፣ እነዚህ ተቋማት ቀዳሚ ዓላማቸውን በምጣኔ ሃብት እድገት ብቻ የሚያደርጉ ከሆነ ሁሉ አቀፍ የሰው ልጅ እድገት ሊመጣ እንደማይችል፣ ነገር ግን የአንድ ሰው እድገት የሁሉን ሰው እድገት የሚያካትት መሆን እንዳለበት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበው፣ ይህ ማለት ደግሞ የተለያዩ የፍጆታ ምርቶችን በማቅረብ ማሕበረሰብን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ማድረግን የሚጠይቅ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። አክለውም ይህን ስርዓት በድህነት ውስጥ በሚገኝ ማሕበረሰብ መካከል ተግባራዊ ለማድረግ የልግስና ሞዴሎችን መከተል የሚያስፈልግ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

“ስነ ምግባር የጎደለው የምጣኔ ሃብት ስርዓት ይባስ ብሎ በሰዎች መካከል የመበላለጥ እና የመናናቅ ባሕልን ያሳድጋል እንጂ ትክክለኛ እና የተረጋጋ ማህበራዊ ሕይወትን ሊያመጣ አይችልም። በተቀራኒው ከቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮች መካከል አንዱ የሆነው እና ግብረ ገብን የተከተለ የምጣኔ ሃብት ስርዓት እውነተኛ ማሕበራዊ እድገትን ሊያመጣ ስለሚች አስፈላጊው ክብር ሊሰጠው ይገባል። የልግስናን መንገድ በመከተል የሌሎችን እድገት በመሻት፣ በመጠበቅ እና በማስጠበቅ ሁሉ አቀፍ እድገትን ማምጣት ይጠበቅብናል”።   

ሁሉንም የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ ለተቀበሏቸው የሁሉ አቀፍ ኤኮኖሚያዊ እድገት አስተባባሪ ምክር ቤት ተወካዮች ባሰሙት ንግግር ምክር ቤቱ ልግስናን መሰረት ያደረገ የጋራ እድገት፣ ለሰው ልጅ እድገት የቆመ እና ስነ ምግባርን የተከተለ የምጣኔ ሃብት ስርዓት ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ አሳስበዋል። በጎርጎሮሳዊው 2008 ዓ. ም. የዓለማችን ምጣኔ ሃብት ክፉኛ መጎዳቱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቀውሱ የደረሰው የምጣኔ ሃብት ስርዓት በአጭር ጊዜ ትርፍ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው ብለው ዘላቂ እና ትክክለኛ የምጣኔ ሃብት ስርዓት መዘርጋት የሚቻለው ምርታማ፣ ዘላቂ እና ማህበራዊ ኃላፊነትን ያካተተ የረጅም ጊዜ እቅድ ሲኖር ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የሁሉ አቀፍ ኤኮኖሚያዊ እድገት አስተባባሪ ምክር ቤት ቀዳሚ ተልዕኮ የዓለማችን የተፈጥሮ ሃብት ለሁሉም ሰው በበቂ ሁኔታ የሚዳረስበትን መንገድ በማሳየት፣ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን ቅዱስነታቸው ለምክር ቤቱ አባላት አስገንዝበዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ የዓለማችንን የተፈጥሮ ሃብት በበቂ ሁኔታ ማዳረስ ሲባል ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ባለቤት መሆን ሳይሆን የከፍተኛ ምርት ተጠቃሚ ቁጥር ማሳደግ እንደሆነ አስረድተው ይህ ደግሞ በማሕበራዊ እድገት ውስጥ ለሰው ልጆች ቅድሚያን በመስጠት የመሠረተ ልማት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ማድረግ ነው ብለዋል።    

ከምክር ቤቱ ተወካዮች ጋር መገናኘታቸው ተስፋን የሚሰጥ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት ምክር ቤቱ ፍታሃዊ የምጣኔ ሃብት ክፍፍል ስርዓትን ለማሳደግ ብለው ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበው ማንንም ወደ ጎን የማይል፣ መጭውን ትውልድ በሙሉ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ፣ ትክክለኛ እና የተሻለ ዓለምን መገንባት የሚያስችል የምጣኔ ሃብት ስርዓት ሊኖር ያስፈልጋል በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
12 November 2019, 16:47