ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በታይላንድ በስዋዕተ ቅዳሴ ባደረጉበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በታይላንድ በስዋዕተ ቅዳሴ ባደረጉበት ወቅት  

የመጀመሪያዎቹን ሚስዮናዊያን ፈለግ በመከተል ወደ ፊት ልንጓዝ ይገባል!

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከኅዳር 09-16/2012 ዓ.ም ድረስ በታይላንድ እና በጃፓን በቅደም ተከተል የሚያደርጉትን 32ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በኅዳር 09/2012 ዓ.ም አመሻሹ ላይ መጀመራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በኅዳር 11/2012 ዓ.ም በታይላንድ ብሔራዊ ቤተመንግሥት ውስጥ ተገኝተው የአገሪቷን ጠቅላይ ሚንስትርን ጨምሮ በስፍራው ለተገኙ የአገሪቷ ባለስልጣናት እና የተለያዩ አገራት ልዑካን ንግግር ማደረጋቸውን መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ከእዚያም በመቀጠል ቅዱስነታቸው በታይላንድ የቡድሃ እምነት ቤተመቅደስ ውስጥ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፣ ከእዚያም በመቀጠል ቅዱስነታቸው በታይላንድ በሚገኘው የቅድስት ሉዊዛ ሆስፒታል ተገኝተው በእዚያ ለተገኙ የሕክምና ባለሙያዎች እና የአስተዳደር ሠራተኞች ንግግር ማደረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ከእዚያም በመቀጠል መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? በሚለው በእለቱ ከማቴዎስ 12፡48 ላይ ተወስዶ በተነበበው የእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ትኩረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” በማለት ኢየሱስ ባነሳው ጥያቄ በግልፅ እና በግልፅ በሚታየው አንድ ነገር ላይ እንዲያሰላስሉ በማደረግ የቤተሰባችን አባላት ፣ ዘመድ እና የምንወዳቸው ሰዎች እነማን ናቸው? በሚሉት ነጥቦች ላይ ያዳምጡት የነበሩ ሕዝቦች እንዲያሰላስሉ መንገዱን ከፍቶላቸው እንደ ነበረ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህ ጥያቄ በሕዝቡ ውስጥ እንዲሰርጽ ካደረገ በኋላ “የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም ሁሉ እርሱ ወንድሜ፣ እህቴ እና እናቴ ነው” በማለት እንደ መለሰላቸው አስረድተዋል።

“በዚህ መንገድ ፣ በዘመኑ የነበረውን ሃይማኖታዊ እና ህጋዊ ስርዓቶችን ብቻ ሳይሆን እራሳቸውን ከፍ አድርገው ከሚያስቡ አካላት ሁሉ አግባብ ያለው መልስ ኢየሱስ እንደ ሰጠ” በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህ ምላሽ ቅዱስ ወንጌልን ለመስማት ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ሁሉ የቀረበ ግብዣ እና ነፃ ስጦታ ነው ብለዋል።

“ሕይወት የመስጠት እና የማመንጨት ችሎታ ያለውን እውነት እንዲመረምሩ በመጋበዝ የደቀ መዛሙርትን ልብ ለማነቃቃትና ለማነሳሳት የሚችሉ ጥያቄዎችን በማንሳት አስገራሚ የሆነ ሁኔታ ኢየሱስ እንደ ፈጠረ” በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ልንገምታቸው ከምንችለው በላይ እጅግ በጣም ውብ የሆነውን አዲስ ስሜት ለማግኘት ልባችንን እና አእምሮአችንን እንድንከፍት የሚፈትኑ ጥያቄዎችን” ኢየሱስ ማንሳቱን ገልጸው መምህራችን የሆነው ኢየሱስ ሁል ጊዜ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ህይወታችንን እና የኛን ማህበረሰብ ሳይቀር ወደር በሌለው ደስታ ለማደስ የታሰቡ ጥያቄዎች መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

“እነዚህ እውነታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በእግራቸው ወደ እዚህች አገር (ታይላንድ) ለሄዱት ሚስዮናውያን ሁኔታው እንደዚህ ነበር” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ከደም ትስስር፣ ባህሎች ፣ ክልሎች ወይም ጎሳዎች ላይ ከመመርኮዝ ይልቅ ከማንኛውም ነገር እጅግ የሚልቅ የቤተሰብ አካል መሆናቸውን ተገንዝበው የጌታን ቃል በመስማትና ለጥያቄዎቹ ምላሽ በመስጠት፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተተክለው ቦርሳዎቻቸው በቅዱስ ወንጌል ተስፋ ተሞልቶ የማያውቋቸውን የቤተሰብ አባላትን ፍለጋ መጀመራቸውን” በስብከታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ክፍፍልን የሚፈጥሩትን ጥያቀዎች ለማሸነፍ በሚያስችል አዲስ አስተሳሰብ ልባቸው ከፍተው ሚስዮናዊ ተግባራቸውን በተግባር ላይ እንዳዋሉ ጨምረው የገለጹት ቅዱስነታቸው በእዚህ የተነሳ በርካታ የታይዋን “እናቶች እና ወንድሞችን” ለማግኘት መቻላቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

“ያ ባይሆን ኖሮ ክርስትና የእናንተን ዓይነት ፊት ዛሬ ባልኖረው ነበር” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ሚስዮናዊያኑ የነበራቸው የቅዱስ የወንጌል አገልግሎት ለተመረጡት ጥቂቶች ወይም ለአንድ የተወሰነ ባህል ብቻ የተገደበ አይደለም፣ ግን ከሰብዓዊ ስሌታችን እና ግምቶች ሁሉ የሚልቅ ፣ የእግዚኣብሔር አባት የፍቅርን ዕቅድ በበለጠ በመረዳት”  የፈጸሙት ተግባር እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው ጭምረው ገለጸዋል።

“ሚስዮናዊያኑ ወደ ጎዳናዎች ሁሉ በመሄድ ያገኙትን ሁሉ ወደ ሠርጉ ድግስ ጋበዙ” ፣ ለእኛ ይህ ግብዣ “የሕይወታችንን ሙሉ እውነት ለማግኘት እንድንችል እግዚአብሔር ከበፊቱ በላይ እንዲያመጣልን” ስለሚያስችለን ይህ ግብዣ የደስታ፣ የምስጋና እና የደስታ ምንጭ ነው፣ በወንጌል ጥናት ውስጥ የሁላችንም ጥረት ምንጭ እና ተነሳሽነት እዚህ ላይ እናገኛለን ” በማለት ቅዱስነታቸው በስብከታቸው መናገራቸው ተገልጹዋል።

“የጌታ ቤተሰብ ህያው ክፍል ስንሆን ሁላችንም ሚሲዮናዊ እና የጌታ ደቀመዝሙር እንሆናለን፣ ይህንን የምናደርገው እርሱ እንዳደረገው ራሳችንን ለሌልች በማቅረብ ነው፣ ከኃጢአተኞች ጋር በልቷል ፣ እነሱ በአብ  እና በዚህ ዓለም የማዕድ ስፍራ እንዳላቸው አረጋግጦላቸዋል፣ ርኩሳን ተደርገው የሚቆጠሩትን ይነካል ፣ እናም እኛም እነርሱን እንድንነካ በማስቻል እግዚአብሔር ለእነርሱ ቅርብ መሆኑን እንዲገነዘቡ እና የተባረኩ መሆናቸውን እንዲያስብ አስችሉዋቸዋል ብለዋል።

እዚህ ላይ በሴተኛ አዳሪነት ሥራ ላይ የተሰማሩትን እና አስገዳጅ የሰው ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሕፃናትንና ሴቶች በጣም አስፈላጊ በሆነው ሰብዓዊ ክብራቸው ዝቅ ተደርገው ስለሚታዩ እነርሱን ማሰብ እፈልጋለው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው  በአደገኛ ዕፅ ሱሰኝነት የተያዙ ወጣቶች እና ለሕይወታቸው ትርጉም ያጡ ሰዎችን፣ ሕልማቸው የተበላሸባቸውን ሰዎች ሁሉ ዛሬ በእዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ላስባቸው እፈልጋለሁ ብለዋል። በተጨማሪም ለስደት የተዳረጉ፣ ቤታቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን የተነፈጉ፣ ወላጅ አልባ የሆኑ ፣ የተተዉ ፣ አቅመ ደካሞችን ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ፈጥረው የተለመደውን ጥንካሬ እንዲሰጣቸው ብርታት እና መጽናኛ እንዲሆናቸው ትርጉም ያለው የሕይወት ግብ እዲኖራቸው ጸሎቴ እና ምኞቴ ነው ብለዋል።

የተከበራችሁ የታይላንድ ማኅበርሰቦች ፣ ጌታ ለእኛ ሊሰጠን የፈለጋቸውን የእናቶች እና አባቶች ፣ ወንድሞች እና እህቶች ፊት ለመገናኘት እና ለማወቅ ያበቁንን የመጀመሪያዎቹን ሚስዮናዊያን ፈለግ በመከተል ወደ ፊት እንድትራመዱ አደራ እላችኋለሁ ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

 

Photogallery

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታይላንድ በስዋዕተ ቅዳሴ ባደረጉበት ወቅት
21 November 2019, 13:39