ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጃፓን ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግር ሲያደርጉ፣              ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጃፓን ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግር ሲያደርጉ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ጃፓን ባሕላዊ ቅርሶቿን በማሳደግ አንድነቷንም እንድትጠብቅ አሳሰቡ።

የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች በሆኑት ታይላንድ እና ጃፓን 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የታይላንድ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ጃፓን መጓዛቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በጃፓን ውስጥ በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ባደረጉት ንግግር ጃፓን ባሕላዊ ቅርሶቿን በማሳደግ አንድነቷንም እንድትጠብቅ አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸው ከመጀመራቸው አስቀድመው ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኩል ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው በስፍራው ለተገኙት ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት እና ለውጭ አገር ዲፕሎማቶች በሙሉ የከበረ ሰላምታቸዋን አቅርበውላቸዋል። የጃፓን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት አቅም በፈቀደ መጠን ለአገርራቸው ሰላም እና ለብልጽግና የበኩላቸውን ጥረት በማድረገ ላይ እንደሚገኙ አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ወቅት በጃፓኑ ንጉሠ ነገሥት ኑሩሺቶ በኩል ለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበው ለንጉሣዊ ቤተሰብ እና ለመላውን የጃፓን ሕዝብ ባርከው፣ በቅርቡ ለነገሡት ለኑሩሺቶ መልካም የሥልጣን ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው የቅድስት መንበር እና የጃፓን ግንኙነት የተመሰረተው እና አድናቆትን ያገኘው በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የወንጌል አገልግሎትን ለማበርከት በተላኩት ሚሲዮናዊያን በኩል እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ለወንጌል ምስክርነት ወደ ጃፓን የተላኩት የኢየሱሳዊያን ማህበር አባል የነበሩት አባ አሌሳንድሮ ቫሊኛኖ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1579 ዓ. ም. በተናገሩት መልዕክታቸው “እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጣቸውን በረከት ማየት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ ጃፓን ይምጣ እና ይመልከት” ያሉት ጠቅሰው ታሪክ እንደሚገልጸው በጃፓን እና በቅድስት መንበር መካከል ተመሥርቶ ለረጅም ዓመታት የዘለቀው መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የውጥረት እና የችግር ዓመታትን እንድንሻገር ረድቶናል ብለዋል። 

ወደ ጃፓን ከመጡበት ምክንያቶች አንዱ በጃፓን የሚገኙ ካቶሊካዊ ምእመናን በእምነታቸው ጥንካሬ በመታገዝ ለሚኮሩበት አገራቸው እና በጃፓን ውስጥ እርዳታን ለሚሹት ድሃ ማሕበረሰብ ያበረከቱት እና በማበርከት ላይ የሚገኙት የቸርነት አገልግሎት የሚያስመሰግን መሆኑን ላረጋግጥ ነው ብለዋል። ጃፓን እንደ አገር በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ላይ ለወደቁት ዜጎቿ በተለይም ለአካል ጉዳተኞች የምትራራ እና የምትጨነቅ አገር መሆኗን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸዋል። በጃፓን ከህዳር 12-16/2012 ዓ. ም. በሚያደርጉት 32ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ማስተላለፍ የሚፈልጉት ቀዳሚ መልዕክት መላውን ሕይወት ከአደጋ እና ከሞት መታደግ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በምንም መንገድ ሊገረሰስ የማይችል ሰብዓዊ ክብር በሁሉም ዘንድ እውቅናን አግኝቶ፣ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለሚያቀርቡት የእርዳታ ጥያቄ አንድነታችንን በመግለጽ የምንችለውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለብን ለማሳሰብ ነው ብለዋል። የጃፓን ሕዝብ በተለያዩ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ መጎዳቱን ከተለያዩ ምንጮች መስማታቸውን የተነገሩት ቅዱስነታቸው የጃፓንን ሕዝብ በደረሰው አደጋ ልባቸው የተነካ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእራሳቸው ቀድመው መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ያገለገሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ፈለግ በመከተል ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በጃፓን ለማድረግ የመጡ መሆናቸውን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን ውስጥ በሚገኙ ሁለት አካባቢዎች ማለትም በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ የተከሰተው የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት እንዳይደገም በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሰዎች በሙሉ ለማበረታታት እና ከእነርሱም ጋር በመሆን የእግዚአብሔርን እርዳታ ለመለመን መሆኑን አስረድተዋል። በሰዎች መካከል እና በአገር ውስጥ የሚከሰተውን አለመግባባት እና አመጽ ማስወገድ የሚቻለው ብቸኛ የሰላም መንገድ በሆነው በጋራ ውይይት እንደሆነ ከታሪክ መማር እንችላለን ብለው ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ምርትን በተመለከተ የሚቀርቡ ሰፊ እቅዶችን መመልከት የሚቻለው ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ሂደቶችን በማጥናት፣ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ የሚችል ሰፋ ያለ ዓለም አቀፍ ስምምነት ላይ መድረስ ሲቻል መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ጥበብ የተሞላበትን የጋራ ውይይት የማሳደግ ባሕል የበለጠ ፍትሐዊ እና ወንድማማችነት ያለበትን ዓለም ለመገንባት ያግዛል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጃፓን የትምህርት፣ የባሕል፣ የስፖርት እና የቱሪዝም ዘርፎችን ማሳደግ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘቧን ገልጸው ይህም በጃፓን ሕዝብ መካከል መግባባትን፣ ፍትሕን፣ አንድነትን እና እርቅን በማጣት ሰላምን ለመገንባት እጅግ የጠቀማት መሆኑን አስረድተዋል። ጃፓን ከዚህ በፊት ባስተናገደቻቸው ዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ጨዋታ ውድድሮች አማካይነት በገሃድ ማየት ተችሏል ብለው በሚመጣው አመት በጃፓን የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችም በጃፓን ሕዝብ እና በአካባቢው አገሮች መካከል አንድነትን እና ወንድማማችንትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖን እንደሚያበረክት ያላቸውን እርግጠኘት ገልጸዋል።

በጃፓን በማድረግ ላይ ከሚገኙት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ጃፓን ከረጅም ዓመታት ጀምራ በማሳደግ ያቆየቻቸው ባሕላዊ፣ መንፈሳዊ እና ስነ ምግባራዊ እሴቶች ያላት መሆኑን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚኖረው መልካም ግንኙነት ሰላምን ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን በማሕበረሰብ መካከል በስነ ምግባር እና በፍትህ የታነጸ ትውልድን ለመገንባት ያግዛል ብለዋል። በጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. በአቡዳቢ ከተማ፣ ከግብጹ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም ከሆኑት አህመድ አል ጣይብ ጋር የተደረገው የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት ለጋራ ውይይት አመቺ መንገዶችን ለመፍጠር፣ በመካከላቸው የእርስ በእርስ መተጋገዝ እና መግባባት እንዲኖር ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

በስነ ጥበብ ልጆቿ ሲጠቀስ የቆየው የጃፓን የተፈጥሮ ውበት ከማንም ዓይን ሊሰውር እንደማይችል የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥንቃቄ የሚያሻው የጃፓን የተፈጥሮ ሃብት፣ ባሁኑ ጊዜ ለተፈጠሮ እና ለሰው ሰራሽ አደጋ የተጋለጠው የጋራ መኖሪያ የሆነው ምድራችንም ከፍተኛ እንክብካቤን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል። የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከውድመት ለመታደግ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም የበኩሉን ጥረት በማድረግ ባለበት ባሁኑ ወቅት ወጣቶችም በበኩላቸው የጋራ አስተዋጽዖ ለማበርክት ቆራጥ ውሳኔን በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ወጣቶች የሚያቀርቡትን ጥያቄ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለወጣቶች ባዶ ተስፋን መስጠት ሳይሆን ምድራችንን ከጥፋት በመታደግ ለኑሮ አመቺ የሆነ ዓለምን በማውረስ የገባንላቸውን ቃል በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ፣ የሰው ሥነ-ምህዳራዊነቱ መታሰብ አለበት ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰዎች መካከል የሚታየው ፍትሃዊ ያልሆነ የተፈጥሮ ሃብት ክፍፍል፣ አብዛኛው የዓለማን ሕዝብ በድህነት ሕይወት በሚገኝበት ወቅት ጥቂቶችን ብቻ ለማበልጸግ የቆመ የኤኮኖሚ ስርዓት እንዲያበቃ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን ችግር ለመቅረፍ የጃፓን መንግሥት በማድረግ ላይ ያለውን ጥረት በቅርበት እመለከተዋለሁ ያሉት ቅዱስነታቸው በአገሪቱ ውስጥ ለሚወጠኑ የጋራ ልማት እቅዶች የዓለም መንግሥታት በጋር እንዲቆሙ ብርታትን በመስጠት የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ ብለዋል። በማሕበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሰብዓዊ ክብር ቀዳሚ ስፍራ ሊሰጠው ይገባል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በድህነት የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉት ሰዎች ሕይወት ግንዛቤን አግኝቶ ተገቢው ማሕበራዊ ድጋፍ ሊደርግላቸው ያስፈልጋል ብለዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ በሚገኙ ማሕበራዊ ችግሮች ላይ የሚገኙትን ወጣቶች ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ከእነርሱም ጋር አቅመ ደካማ የዕድሜ ባለጸጋዎች እና ከማሕበረሰቡ መካከል የተገለሉ ረዳት የሌላቸውን ሰዎችንም አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ የአንድ አገር ሕዝብ እድገት የሚለካው አገሩ በሚገኝበት ከፍተኛ የኤኮኖሚ እድገት ሳይሆን የእያንዳንዱን ግለሰብ ሕይወት ወደ መልካም ደርጃ ለማድረስ በሚያደርገው ጥረት ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማገባደድ በተቃረቡበት፣ ጃፓንን እንዲጎበኙ በማለት ጥሪያቸውን ያቀረቡትን በሙሉ፣ በጃፓን ቆይታቸውም መልካም መስተንግዶን ላደረጉት፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውም ፍሬያማ እንዲሆን ያደረጉትን በሙሉ አመስግነዋቸዋል። የጃፓን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ዲፕሎማቶች በሙሉ እርሳቸው ያቀረቡላቸውን ሃሳብ ሰምተው ለተግባራዊነት እንዲነሳሱ ጠይቀው፣ በተለይም መላውን ሕይወት ከጥፋት አደጋ በመታደግ፣ የእያንዳንዱ ሰው ክብር ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ በአደራ መልክ አሳስበው ለቤተሰቦቻቸው እና ለሚያገለግሉት የጃፓን ሕዝብ የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ቡራኬ ከተመኙላቸው በኋላ ምስጋናቸውን በማቅረብ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

              

25 November 2019, 15:44