ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ “መለኮታዊ ጥበብን መሻት፣ ማግኘት እና ለሌሎች ማዳረስ ያስፈልጋል”።

የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች በሆኑት ታይላንድ እና ጃፓን 32ኛን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የፈጸሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን ያደረጉትን ጉብኝት ከመፈጸማቸው በፊት በቶኪዮ ከተማ የሚገኘውን ሶፊያ ዩኒቨርሲቲ በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር መለኮታዊ ጥበብንም መፈለግ፣ ማግኘት እና ለሌሎች ማዳረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበው በማከልም ጥራት ያለውን ትምህርት የመቅሰም መብት የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም መሆን አለበት ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወደ ጃፓን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም ከማቅናታቸው በፊት በቶኪዮ ከተማ በሚገኝ ሶፊያ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ጃፓንን እንዲጎበኙ ላበቃቸው እግዚአብሔር ምስጋናቸውን አቅርበው ለተሰጣቸው ዕድልም የጃፓንን ሕዝብ አመስግነዋል። ጃፓን ቅዱስ ፍራንሲስ ዛቬር እና በርካታ ሰማዕታት ክርስቲያናዊ ምስክርነታቸውን ያሳይባት አገር መሆኗንም ገልጸዋል። በጃፓን ውስጥ የክርስቲያኖች ቁጥር ትንሽ ነው ቢባልም መኖራቸው ጎልቶ ይታያል ያሉት ቅዱስነታቸው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ በጃፓን የምታበረክተውን ሐዋርያዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች፣ ከጃፓን ሕዝብ ጋር ያላትን ጠቅላላ ግንኙነት በቅርብ ለመመልከት እና ለመመስከር መቻላቸውን ገልጸው ቤተክርስቲያኒቱ ከሕዝቡ ጋራ ያላት መልካም የእርስ በእርስ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና እንደሚያድግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው ከዚህም በላይ በጃፓን ሕዝብ መካከል የመግባባት፣ የርህራሄ እና የምሕረት መንፈስ እንዳለ መመልከታቸውን አስረድተዋል።

ዕውቀትን መቅሰም እና ማስተንተን የአንድ ባሕል መለያ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ጥንታዊው የጃፓን ባሕልም በዚህ ልምድ የተካነ መሆኑን አስታውሰዋል። ጃፓን ከመላው የእስያ አገሮች አስተሳሰብ እና እምነት ጋር በቀላሉ ሊዋሄድ የቻለ አገር፣ ማንነቱንም የሚገልጽበት ባሕል ያለው አገር መሆኑን ተናግረው ለዚህም ጉልህ ምስክር ቅዱስ ፍራንሲስ ዛቬየር የተማረከበት የአሺካጋ ትምህርት ቤት መሆኑን በመጥቀስ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የጥናት፣ የአስተንትኖ እና የምርምር ማዕከላት ዛሬ በምንኖርነት ባሕል ውስጥ እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው መልካም ትውልድን ለማፍራት የአንድ ባሕል ራስ ገዝነትን እና ነጻነትን ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲዎች የወደፊት መሪዎች ሰልጥነው የሚወጡባቸው የመጀመሪያ የእውቀት ማዕከል እንደመሆናቸው ማሕበራዊ እድገትን ለማፋጠን የሚያግዙ እውቀቶች እና ባሕሎች ልዩነትን ሳያደርጉ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሁሉም ሊዳረሱ ይገባል ብለዋል።             

ሀብታችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር እንዲቻል እውነተኛ ነጻነት ሊኖር ይገባል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቴክኖሎጂን መሠረት ላደረገ ማህበረሰብ ዩኒቨርሲቲ የምሁራን ማፍለቂያ ብቻ ሳይሆን የተሻለ ማሕበረተሰብ እና የወደ ፊት ተስፋ ሙሉ ሆኖ የሚገኝበት ቦታ መሆን አለበት ብለዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ ባሕል ተፈጥሮን የመንከባከብ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከአደጋ የመከላከል ባሕል በእስያ አገሮች ውስጥ በተግባር የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል። አዲስ ውህደትን የሚጋብዝ እውነተኛ ስብዕና የሚገኘው ባንገነዘበውም በቴክኖሎጂ ባሕል ውስጥ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

በጃፓን የሚገኘው የሶፊያ ዩኒቨርሲቲ ስነ ሰብዓዊ፣ ክርስቲያናዊ እና ዓለም አቀፍዊ መለያ አለው በማለት ያስረዱት ቅዱስነታቸው ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በውስጡ በማስተማር ሥራ ላይ የተሰማሩ መምህራን ከተለያዩ አገሮች የተመረጡ መሆናቸውንም አስታውሰዋል። አክለውም እነዚህ መምህራን ምንም እንኳን በቅራኔ ውስጥ ከሚገኙ አገሮች የሚጡ ቢሆንም ያላቸውን እውቀት ከጃፓን ወጣቶች ጋር ለመጋራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል ብለዋል። የጃፓን ምሁራንም ቢሆኑ ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍል በመሄድ እውቀታቸውን በመጋራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው የጃፓን ዩኒቨርሲቲ ባሕል ወደ ሌሎች የዓለማችን አካባቢዎች በመድረስ በዘመናችን የሚታየው የቴክኖሎጂ እድገት ለሰው ልጅ የሚሰጠውን አገልግሎት በማሳደግ በስነ ምሕዳርም በቂ እውቀት በማስጨበጥ አገልግሎት እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በያዝነው ዓመት በኢየሱሳውያን ማሕበር ተዘጋጅቶ እርሳቸው ያጸደቁት “ጠቅላላ ሐዋርያዊ አማራጮች” የተባለ ሰነድን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ወጣቶችን በቅርብ ተከታትሎ ማገዝ በመላው ዓለም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አገልግሎት መሆኑን ገልጸው ይህን አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኝ የቅዱስ ኢግናሲዮስ ተቋምም ለወጣቶች የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል። የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስም የወጣቶችን ጉዳይ በስፋት ተመልክቶ ባወጣው ሰነድ ይህን ሃሳብ ይገልጻል ብለዋል።

በጃፓን የሚገኝ የሶፊያ ዩኒቨርሲቲ ስነ ማህበረሰብ ጥናት ክፍልም ተጨማሪ የምርምር ምርጫ አለው ያሉት ቅዱስነታቸው እርሱም በድህነት ሕይወት ውስጥ ከሚገኙት እና ከማሕበረሰቡ መካከል ከተገለሉት ጋር መጓዝ ነው ብለው የዩኒቨርሲቲው ተልዕኮ ምናልባት ከጃፓን ሕዝብ ባሕል ውስጥ ያልገቡትን እውነታዎች መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በማከልም የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ስርዓት የስነ ማሕበረሰብን ዘርፍ በማሳደግ ለሰው ልጅ ሊቀርቡ የሚገቡ መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶችን ቢያሳድግ መልካም ይሆናል ብለው፣ ጥራት ያለውን ትምህርት የመቅሰም መብት የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም መሆን አለበት ብለዋል።

ከተማሪዎች ጀምሮ ለመላው የሶፊያ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ ባሰሙት ንግግራቸው ከዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ ጋር ያደርጉት ውይይት በእያንዳንዱ የዩኒቨርሲቲው ማሕበረስብ ሕይወት ፍሬን እንዲያፈራ ያላቸውን ምኞት ገልጸው፣ እግዚአብሔር እና እርሱ የመሠረታት ቤተክርስቲያን መለኮታዊ ጥበብን በመፈለግ፣ በማግኘት እና ለሌሎች በማዳረስ አገልግሎታቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጉብኝታቸው የመጨረሻ አገር የሆነችው ጃፓንን ከመሰናበታቸው በፊት ባስተላለፉት መልዕክት ወደ ጃፓን ሲደርሱ ለተደረገላቸው የክብር አቀባበል እና በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ለተደረገላቸው መልካም መስተንግዶ መላውን የጃፓ ሕዝብ አመስግነው፣ በዘወትር ጸሎታቸውም የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 November 2019, 17:04