ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ትንሣኤ የሕይወት ትርጉም እና ዓላማ የሚገኝበት መሆኑን አስገነዘቡ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በያዝነው የጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን 13 ብጹዓን ካርዲናሎችን እና 147 ጳጳሳት በማስታወስ፣ ዛሬ ጥቅምት 24/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት መፈጸማቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደባ ኤማኑኤላ ካምፓኒሌ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ወቅት ባሰሙት ስብከታቸው ትንሳኤን በሚያስታውሱ ሦስት ርዕሦች ላይ አስተንትኖ ማድረጋቸው ታውቋል።     ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅታችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው እለት ማለትም በጥቅምት 24/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያቀረቡት የስብከተ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“አሁን የሰማነው የቅዱስ መጽሐፍ ንባብ፣ ወደዚህ ዓለም የመጣነው ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ለመሸጋገር እንጂ ሞተን ለመቅረት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ ወድ ፊሊጵስዩስ ሰዎች መጻፈው ሁለተኛው መልዕክቱ በምዕ. 3:20 ላይ “እኛ ግን የመንግሥተ ሰማይ ዜጎች ነን፤ ከዚያም የሚመጣውን አዳኝ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን (2ፊሊ. 3:20)። የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ቅዱስ ዮሐንስ እንደጻፈው በምዕራፍ 6:40 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ “የአባቴ ፈቃድ ወልድን የሚያይ እና በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲያገኝ ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ” በማለት ተናግሮአል። በተመሳስይ መልኩ በ2መቃ. 12:43 ላይም የትናሳኤን ክብር የሚገልጽ መልዕክት እናገኛለን። እኛም ብንሆን “የትንሳኤ መልዕክት ምንድነው”? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። “ለትንሳኤው በረከት የምሰጠው መልስ ምን መሆን አለበት?” በማለት እያንዳንዳችን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

ለዚህ ጥያቄ በቂ መልስ መስጠት እንድንችል ከኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚደረግልን እርዳታ፣ ዛሬ የተነበበው፣ የጌታችን ኢየሱስ ውንጌል ቅዱስ ዮሐንስ እንደጻፈው “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” (ዮሐ. 6:37)። በማቴ. 11:28 ላይ እንደተጻፈው ወደ እርሱ እንድንመጣ ይጋብዘናል። ወደ ዘለዓለማዊው ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ የምንመጣው ፍርሃትን ለማስወገድ እና ከሞት ወደ ሕይወት ለመሸጋገር ነው። “ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እንቅረብ” የሚለውን በመንፈሳዊ አስተሳሰብ መመልከት እንችላለን። ነገር ግን በተግባር ማየት ብንሞክር፣ ለምሳሌ በዕለታዊ የሥራዬ ገበታዬ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበኝን መልካም ሥራ ሠርቻለሁ ወይ? የሰዎችን ጥያቄ፣ የሰዎችን መከራ በዕለታዊ ጸሎቴ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በማቅረብ የእርሱን ድጋፍ ለምኜላቸዋለሁ ወይ? ወይስ በመልካም ነገር በመደሰት፣ በችግር ጊዜ ማማረርን እመርጣለሁ? የጉዞዬ አቅጣጫ ወዴት ነው? የሚመቸኝን የራሴን መንገድ በመምረጥ፣ ሥራዬን በምፈልገው ጊዜ እና ቦታ ብቻ ማከናወንን እመርጣለሁ ወይስ ይህን ሁሉ እንዳደርግ የሚያስችለኝን የእግዚአብሔር እገዛ እጠይቃለሁ በማለት ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።                   

“ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” የሚለው የኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር፣ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የማይመጣ አንድ ክርስቲያን ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚርቅ መሆኑን ያመለክታል። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ሁሉ ወደ እርሱ እንዳይቀርብ፣ በራሱ መንገድ እንዲጓዝ የሚያደርግ ምንም  ሌላ ምርጫ የለውም። የኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ከመኖር ሌላ ምርጫ የለውም።

ሕይወት ከእናት ማሕጸን ጀምሮ ወደ ዓለም እስከመጣንበት ጊዜ ድረስ፣ ከዚያም ከሕጻንነት እስከ ጎልማሳነት፣ ከጎልማሳነትም አልፎ ወደሚቀጥለው ሕይወት የሚናደርገው ጉዞ ነው እንጂ በዚህ ዓለም ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ዛሬ ወንድሞቻችን የሆኑትን ብጹዓን ካርዲናሎችን እና ጳጳሳትን በጸሎታችን  በምናስታውስበት ጊዜ ከዚህ ምድራዊ ሕይወት ወጥተው፣ ለመፈጠራቸው እጅግ ጠቃሚ ትርጉም የሚሰጠውን የትንሳኤ በረከት ለመቀበል መሸጋገራቸውን መዘንጋት የለብንም። የትንሳኤን በረከት ማግኘት የምንችለው ከራሳችን ወጥተን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰንን በር ስንከፍት ነው። በመሆኑም “እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የዘለዓለም ሕይወት ነህና ወደ አንተ ዘንድ መምጣት እመኛለሁ፣ የጉዞዬ መሪ አንተ እንድትሆነኝ፣ የትንሳኤን ጸጋ እንድታወርሰኝ፣ የራሴን መንገድ ከመከተል ይልቅ በአንተ መንገድ መጓዝ እንድችል እርዳኝ” በማለት የእርሱን እገዛ መጠየቅ ያስፈልጋል።

ትንሳኤን የተመለከተ ሁለተኛ ሃሳቤ፤ በመጀመሪያው የቅዱስ መጽሐፍ ንባብ፣ በሁለተኛው መጽሐፈ መቃብያን፣ በምዕ. 12:45 ላይ በሞት ያንቀላፉት ምሕረትን የሚያገኙበትን እና አስደናቂ ሽልማትም የሚጠብቃቸው መሆኑን ይናገራል። ምህረት የዘለዓለም ሕይወት መግቢያ በር ናትና። የተቸገሩትን ለማገልገል ራሳችንን ዝቅ ማድረግ ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት የምንገባበትን መንገድ ያዘጋጃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በጻፍው የመጀመሪያ መልዕክቱ “ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል” (1ቆሮ. 13:8)። ምድራዊ ሕይወትን ከሰማያዊው ሕይወት ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በሰዎች መካከል የሚደረግ የቸርነት ተግባር ነው። በዚህ የቸርነት ድልድይ ላይ ለመጓዛችን እርግጠኞች መሆን ያስፈልጋል። ለተቸገሩት መጨነቅን፣ መራራትን እና መጸለይን እንዲሁም ውለታን መክፈል የማይችሉትን፣ ረዳት የሌላቸውን ለማገዝ ልቤ ምን ያህን ዝግጁ ነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።

ትንሳኤን የተመለከተ ሦስተኛው እና የመጨረሻው ሃሳቤ የቅዱስ ኢግናሲዮስን የሕሊና ምርመራን መንገድን የተከተለ ነው። ቅዱስ ኢግናሲዮስ በሕይወት ዘመን መጨረሻ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም እንደምንጠራ መዘንጋት እንደሌለብን ያሳስበናል። ከዚህ የእግዚአብሔር ጥሪ ማምለጥ አንችልም። እያንዳንዱ የሕይወት አቅጣጫ ወደዚህ የሕይወት ጥሪ የሚያመራ ነው። መከሩ በዘሩ ብዛት እንደሚሰላ ሁሉ የሕይወት ፍጻሜም በመጨረሻው የፍርድ ቀን ይታወቃል። ቅዱስ ኢግናሲዮስ በሕሊና ምርመራ ልምምድ ቁጥር 187 እንደገለጸው አሁን ተግባራዊ የማደርጋቸው የሕይወት መመሪያዎቼ የመጨረሻውን የፍርድ ቀንን ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል። ይህ የቅዱስ ኢግናሲዮስ መንፈሳዊ የሕሊና ምርመራ በራስ ፍላጎት ወይም ምርጫ በመመካት ሳይሆን የእግዚአብሔርንም ፍላጎት ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ በመሆኑ ጠቀሜታው ሰፊ ነው። የትንሳኤን ክብር የተገነዘበ ሕይወት ዛሬ የምንኖርበትን ሕይወት ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት የሚጠብቀንን ዘለዓለማዊ ሕይወት የምናገኝበት የፍቅር ጣዕምን በትክክል ስናውቅ ነው።

ከግል ምርጫዬ በመላቀቅ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመከተል የዕለት ጉዞዬን ወደ እርሱ አቀናለሁ ወይ? የበደሉኝን ይቅር በማለት ምሕረትን የማድረግ ፍላጎት አለኝ ወይ? ወደ መጨረሻዋ የፍርድ ቀን እስክደርስ በዕለታዊ ጉዞ መልካምን እንዳደርግ የሚያግዘኝን ውሳኔ አደርጋለሁ ወይ በማለት በእነዚህ ሦስት መንገዶች ላይ ማሰብ ይኖርብናል። የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ቅዱስ ዮሐ. እንደጻፈው በምዕ. 6:39 ላይ “የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳይጠፋብኝ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣ ነው”።  የሕይወትን ትርጉም እንድናጣ ከሚያደርጉን በርካታ አስተሳሰቦች ተላቅቀን፣ ከሞት በተነሳው፣ ለዘለዓለምም በሚኖር በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ራሳችንን በማስገዛት ወደ ትንሳኤው የምንደርስበትን ሕይወት በመኖር ላይ እንገኛለን”።          

04 November 2019, 15:43