ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ፍራንቸስኮስ “በምሕረት የተሞላ የኢየሱስ እይታ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ያደርጋል” አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥቅምት 03/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 19፡1-10 ላይ ተወስዶ በተነበበውና ቀረጥ ሰብሳቢ በነበረው ዘኬዎስ ታሪክ ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት አስተንትኖ እንደ ገለጹት “በምሕረት የተሞላ የኢየሱስ እይታ መንፈሳዊ ለውጥ እንድናመጣ ያደርጋል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥቅምት 23/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የዛሬ ቅዱስ ወንጌል (ሉቃ 19፡ 1-10) ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በሚሄድበት ወቅት በኢያሪኮ ቆይታ እንዳደረገ ይገልጻል። በእዚያ ስፍራ በጣም ብዙ ሕዝብ የነበረ ሲሆን  ከእነዚህም ውስጥ የሮማውያንን መንግሥት ወክሎ ግብር የሚሰበስቡ አይሁዳዊያን አለቃ የነበረ ዘኬዎስ የሚባል ሰው ይገኝበታል። እርሱ ሐብታም የነበረ ሰው ሲሆን ሐብቱን ግን ያገኘው ሀቀኛ በሆነ መንገድ ሳይሆን በሰዎች ላይ በሚጭነው ክልክ በላይ በሆነ ቀረጥ ምክንያት ሲሆን ይህም ተግባር በሕዝቡ ዘንድ እንዲጠላ አድርጎታል። ዘኬዎስ “ኢየሱስን ለማየት ይፈልግ ነበር”፣ እርሱ ኢየሱስን መገናኘት አልፈለገም፣ ግን ስለእርሱ የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ነበረው፣ ምክንያቱም እርሱ ያከናውን የነበረውን ያልተለመዱ ነገሮችን ለማየት ፈልጎ ነበር። ከፍተኛ የሆነ ጉጉት ነበረው። ቁመቱ አጭር የነበረ በመሆኑና ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ኢየሱስን ማየት ስላልቻለ ኢየሱስን በሚገባ ለማየት ፈልጎ አንድ ዛፍ ላይ ወጣ። ኢየሱስ በእዚያ አከባቢ በሚያልፍበት ወቅት ቀና ብሎ ተመለከተው።

ምንም እንኳን በጣም ብዙ በሆኑ ሰዎች ተከቦ የነበረ ቢሆንም በቅድሚያ ኢየሱስን የተመለከተው ዘኬዎስ ሳይሆን ኢየሱስ ነው፣ እናም ይህ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው። እኛ መዳን እንደ ሚያስፈልገን ከመገንዘባችን በፊት የእግዚአብሔር የምህረት እይታ በእኛ ላይ ያርፋል። እናም ከመለኮታዊው ጌታ እይታ አንፃር የኃጢያተኛው ሰው መለወጥ ተዓምር ይጀምራል። በእርግጥ ኢየሱስ በስሙ ነበር የጠራው "ዘኬዎስ ሆይ ፥ ዛሬ በአንተ ቤት መሆን ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ” በማለት ይጠራዋል። አልነቀፈውም፣ አልሰበከውምም፣ እርሱ ወደ እርሱ ቤት መሄድ እንዳለበት ብቻ ይነግረዋል፣ ምክንያቱም እሱ የአብ ፈቃድ ነው። ምንም እንኳን ሕዝቡ ያጉረመርም የነበረ ቢሆንም ቅሉ ኢየሱስ ግን በእዚህ ኃጢአተኛ ሰው ቤት ውስጥ መቆየት ፈለገ።

እኛም በእዚህ በኢየሱስ ባሕርይ ልንሰናከል እንችል ይሆናል። ነገር ግን ኃጢያተኛ የነበረውን ሰው መንቀፍ እና ከእርሱ መሸሽ እርሱ በማህበረሰቡ ላይ ይፈጽም የነበረውን ክፋት እንዲያቆም አያደርገውም። ይልቁኑ እግዚአብሔር ኃጢያትን ያወግዛል ፣ ነገር ግን ኃጢአተኛውን ሰው ፈልጎ ለማዳን ይሞክራል፣ እሱ በትክክለኛው ጎዳና ላይ ተመልሶ ይገኝ ዘንድ ወደ እርሱ ይመለከታል። የእግዚአብሔርን ምህረት የማይሻ ማንኛውም ሰው ኢየሱስ ወደ ዘኬዎስ ቀርቦ የተናገራቸውን አካላዊ መግለጫዎች እና ቃላቶች ታላቅነት ለመረዳት ይከብደዋል።

በኢየሱስ ተቀባይነት እና ትኩረቱ በማግኘቱ ይህ ሰው ከፍተኛ የሆነ አእምሮአዊ ለውጥ እንዲያመጣ አድርጎታል፣ በገንዘብ ላይ መሰረቱን ያደረገ ሕይወት ከንቱ እና ሚስኪን የሆነ ሕይወት እንደ ሆነ በቅጽበት ይገነዘባል፣  ከሌሎች ገንዘብ መስረቅ እና ያለአግባብ ገንዘብ መቀበል በሰዎች ዘንድ የሚያስንቅ ተግባር መሆኑን ይገነዘባል።  ጌታ እዚያው በቤቱ መገኘቱ ኢየሱስ እርሱን በተመለከተበት መልኩ ሁሉንም ነገር ለየት ባለ ዐይን እንዲመለከት አድርጎታል። እንዲሁም ለገንዘብ ያለው አተያይ እና የገንዘብ  አጠቃቀም ሁኔታ እንዲለወጥ አድርጉዋል፣ ለራሱ ከመሰብሰብ ለሰው ወደ መስጠት ተተክቱዋል። በእውነቱ እርሱ ለድሆች እና በተጨማሪም ገንዘብ ለነጠቃቸው ሰዎች አራት እጥፍ ለመክፈል እና ለመስጠት ወስኑዋል። ዘኬዎስ በነፃነት መውደድ እንደሚቻል ከኢየሱስ ተረዳ ፤ እስከ እዚያ ሰዓት ድረስ ግን ተንኮለኛ ሰው ነበር ፣ አሁን ለጋስ ሰው ሆነ፣ እሱ ገንዘብ የማጋበስ ዝንባሌ ነበረው፣ አሁን ደግሞ ገንዘቡን ከሌሎች ጋር በመጋራት የሚገኘውን ደስታ ተቋዳሽ ሆነ። ፍቅር በማግኘቱ የተነሳ ኃጢያቶቹ ከመስተሰረያቸው ባሻገር ሌሎችን የመውደድ ችሎታ ያገኛል፣ ይህም ገንዘብ የአንድነትና የመተባበር ምልክት እንዲሆን አደረገ።

የጠፋውን ለመፈለግ እና ለማዳን የመጣውን ኢየሱስን ለመቀበል እንዲችሉ፣ ሁልጊዜ የኢየሱስ የምሕረት ዐይኖች በእኛ ላይ መሆናቸውን የሚገልጽ ስሜት እንዲሰማን፣ “የጠፋውን ፈልጎ ለማዳን የመጣውን ኢየሱስ” መቀበል የምንችልበትን ጥንካሬ እና ጸጋው ከልጇ ዘንድ እንድታሰጥልን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት መማጸን ያስፈልጋል።

03 November 2019, 14:10