ፈልግ

የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የፍርሃትና የጭንቀት ባሮች ሆነው መቀጠል አይችሉም!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 07/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 21፡5-19 ላይ ተወስዶ በተነበበውና በመጨረሻው ቀን ስለሚከሰቱ ምልክቶች በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ባደርገው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደ ገለጹት “የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የፍርሃትና የጭንቀት ባሮች ሆነው መቀጠል አይችሉም” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኅዳር 07/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በእዚህ የዓመቱ ስርዓተ-አምልኮ ማብቂያ እለተ ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል (ሉቃስ 21፡5-19) ውስጥ ኢየሱስ በመጨረሻው ጊዜ ስለሚከናወኑ ነገሮች ይገልጻል። ኢየሱስ ይህንን የተናገረው በትልቅነቱ እና በግርማ ሞገሱ በሚታወቀው በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት ሆኖ ነበር። እርሱም ይህ በጣም ውብ የሆነው ቤተመቅደስ እንዲህ እንዳማረበት እንደ ማይቀር በመተንበይ “ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደ ተካበ የማይቀርበት ጊዜ ይመጣል” (ሉቃስ 21፡6) በማለት ይናገራል። ኢየሱስ ስለ ቤተመቅደሱ የተናገረው ነገር የጥፋት ታሪክ መጨረሻ ክስተት ሳይሆን በታሪክ መጨረሻ ላይ የሚከሰቱ ነገሮች ምስል ነው። በእርግጥ ፣ እነዚህ ምልክቶች እንዴት እና መቼ እንደሚከሰቱ ለማወቅ በሚፈልጉ አድማጮች ፊት ፣ ኢየሱስ በተለምዶ የመጽሐፍ ቅዱስን ቋንቋን በመጠቀም ምላሽ ይሰጣል።

ሁለት በግልፅ የሚጋጩ ምስሎችን ይጠቀማል፣ የመጀመሪያው በተከታታይ ስለሚከሰቱ አስፈሪ የሆኑ፣ የጥፋት፣ የጦርነት ፣ የረሃብ ፣ የሁከት እና የስደት  ክስተቶች ይናገራል፣ ሁለተኛው ክስተት ደግሞ ማረጋገጫ የሆነ ክስተት ሲሆን ይህ ሁሉ በሚከሰትበት ወቅት “ከራስህ ጠጉራችሁ አንድ እንኳ አይጠፋም” (ቁ 18) በማለት መተማመኛ ይሰጠናል። በመጀመሪያ ታሪካዊ የሆነ ጥፋት፣ እንዲሁም የእዚህ ጥፋት ምልክት ተደረገው የተቆጠሩ ምልክቶች፣ ፍጥረትን የሚጎዱ ክስተቶች፣ የጋራ መኖሪያችን እና በእዚያም ውስጥ የሚኖሩትን ሰብዓዊው ቤተሰብ እና የክርስቲያን ማህበረሰብ የሚጎዱ ክስተቶች እንደ ሚፈጠሩ ይገልጻል። እስቲ ዛሬ እየተከሰቱ የሚገኙትን ጦርነቶች፣ ብዙ ስቃዮችን እና ብዙ መቅሰፍቶችን እናስብ።  ሁለተኛው ምስል ደግሞ ኢየሱስ የሚሰጠን ማረጋገጫ ነው፣  ክርስትያኖች በግፍ እና በመከራ የተሞላው ታሪክ ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደ ሚገባ ይናገራል።

የክርስቲያን አመለካከትስ ምንድን ነው? በአሳዛኝ ክስተቶች ምክንያት እንዳንሸነፍ የሚረዳን  በእግዚአብሔር ላይ ያለን የተስፋ አስተሳሰብ ነው። በእርግጥ እነዚህ ክስተቶች “ለእርሱ ምስክርነት የምንሰጥበት መልካም አጋጣሚ ናቸው”። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የፍርሃትና የጭንቀት ባሮች ሆነው መቀጠል አይችሉም ፣ እነሱ በመልካም ስራ በታገዘ መልኩ ከእርሱ ጋር ሁልጊዜ እንዲጓዙ በእዚህ መልኩ እና ሁኔታ ታሪክን እንዲኖሩ እርግጠኞች እንዲሆኑ እና አጥፊ የሆነውን ክፉ የሆነ ኃይል እንዲያስወግዱ ተጠርተዋል። የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እኛ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ምልክት ሲሆን ይህም ዓለም እግዚኣብሔር በሚፈልገው መልኩ መኖር እንዳለበት እውነታውን የሚገልጽ ምልክት ነው። እርሱ ጌታ ነው ፣ እርሱም ሕይወታችንን የሚመራ እና የነገሮች እና ክስተቶች የመጨረሻ ግብ ያውቃል።

ከእርሱ ጋር በመሆን፣ ለወደፊቱ ሰላም እና ተስፋን በመፍጠር በታሪክ ግንባታ ውስጥ ተካፋይ እንሆን ዘንድ ጌታ ይጠራናል። እምነት በእዚህ ምድር ላይ በጣም ስቃይ በሚበዛባቸው መንገዶች ላይ ሳይቀር ከኢየሱስ ጋር ሆነን እንድንራመድ ይረዳንል። ፍቅር የሁሉም ነገር የበላይ ነው፣ ምክንያቱም ፍቅር እግዚኣብሔር ራሱ ስለሆነ ነው። የክርስትና እምነት ሰማዕታት ምሳሌዎች የሆኑ ሰዎች አሉ፣ ሰማዕታቶቻችን ቀደም ሲል ከነበሩ ሰማዕታት በቁጥር የበረከቱ ሰማዕታት በእኛ ዘመን አሉ። እነዚህ በተለያዩ ምክንያቶች ስደት እየደረሰባቸው የሚገኙ ወንዶች እና ሴቶች የሰላም መሣሪያዎች ናቸው።  ልንጠብቀው የሚገባ እና እኛም ልንላበሰው የሚገባንን ምሳሌ በቅርስ መልክ አውርሰውናል፣ ይህም የፍቅር እና የምሕረት ወንጌል ነው። ይህ ለእኛ የተሰጠን እጅግ ውድ የሆነ ሀብት እና ለዘመናችን ሰዎች ልንሰጠው የሚገባን እጅግ በጣም ውጤታማ ምስክርነት ሲሆን ለጥላቻ በፍቅር ምላሽ በመስጠት፣ በደልን በይቅርታ ማለፍ ማለት ነው። በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እንኳን: በደል ሲደርስብን ህመም ይሰማናል፣ ነገር ግን ከልብ ይቅር ማለት አለብን። የጥላቻ ስሜት ሲሰማን ለሚጠላን ሰው በፍቅር እንጸልይ። ታሪክን የሚመራውን ጌታን ለመከተል እንድንችል፣ በእለት ተዕለት በእመነት በምናደርገው ጉዞ እንድትደግፈን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናትነት አማላጅነቷ  እንድትረዳን እንማጸናት።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
17 November 2019, 15:37