ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንስችስኮስ፥ “እግዚአብሔር ለወንጌል ምስክርነት ይጠራናል”።

የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት የሚታወስበትን እና እንደ ጎርጎሮርሳዊው አቆጣጠር ትናንት መስከረም 20/2012 የተጀመረውን የጥቅምት ወርን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነስርዓት መፈጸማቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በጸሎት ስነ ስርዓቱ ላይ ባሰሙት ስብከተ ወንጌል የወንጌል ተልዕኮ አደራን ተቀብላ በማከናወን ላይ ካለች ቤተክርስቲያን ጋር ሆነን የወንጌልን መልካም ዜና መመስከር ይኖርብናል ብለዋል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎርጎሮሳዊውያኑ አቆጣጠር መስከረም 20/2012 የተጀመረው የጥቅምት ወር የሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅ የሆነች ቅድስት ተሬዛ በዓል መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ የቀርሜሎሳዊያን ማሕበር አባል የሆነች ቅድስት ተሬዛ ምንም እንኳን ከምትኖርበት ገዳም ወጥታ የወንጌል ተልዕኮን የፈጸመች ባትሆንም ከቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪየር ጋር በካቶሊካዊት ቤተ ውስጥ የዓለም አቀፋዊ የወንጌል ተልዕኮ ባልደረባ መሆኗን ገልጸዋል።

ሦስቱ የወንጌል ልኡካን ሞዴሎች፣

በስብከተ ወንጌላቸው እነዚህን ሁለቱን ቅዱሳን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቅድስት ተሬዛ ለቤተክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ ጸሎትን እንደ ብርሃን በማድረግ ዘወትር ጸሎት ስታቀርብ የኖረች መሆኗን አስረድተው፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቬርም እንደዚሁ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ምናልባትም ከቅዱስ ጳውሎስ ቀጥሎ ታላቅ የወንጌል ልኡክ እንደነበር አስረድተዋል። ጳጳሳዊ የወንጌል ልኡካን ማሕበር መስራች የሆነችውን ፈረንሳዊ ተወላጅ ፖሊን ጀሪኮን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እነዚህ ሦስቱ የቤተክርስቲያን ልጆች ከምኖርበት የተደላደለ እና የተመቻቸ ሕይወት ወጥተን ለወንጌል አገልግሎት ራሳችንን እንድናቀርብ ያደርጉናል ብለዋል።

ተሰጥኦአችንን ሳናባክን እንጠቀምበት፣

ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ በጻፈው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ በምዕ. 25 ከቁ. 14 ጀምሮ የተጠቀሰውን የሦስቱ አገልጋዮች ምሳሌን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ከስጦታዎች ሁሉ በላይ በሆነ ስጦታ እንደባረከን ገልጸው ስጦታዎቹም የራሳችን እና የሌሎች ሰዎች ሕይወት መሆናቸውን አስረድተው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጡንን ተሰጥኦች ያለ ፍርሃት ተጠቅመን ፍሬያማ እናድርጋቸው ብለዋል። ይህ ልዩ የወንጌል ተልዕኮ የሚታወስበት የጥቅምት ወር መልካም ሥራን ለማበርከት የሚያነሳሳን፣ እምነታችንን ለራሳችን ብቻ ይዘን የምንቆይ ሳንሆን ፣ በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት አማካይነት ለሌሎችም እንድንመሰክር የሚያደርገን መሆን አለበት ብለዋል።

የወንጌል ምስክሮች መሆን፣

የወንጌል ልኡክ መሆን ማለት ምስክር መሆን ማለት ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰማዕትነት ጋር ተመሳሳይነት አለው ብለዋል። ሰማዕታት ሰላምን እና ደስታን በመስበክ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ጠላቶቻቸውንም ያፈቀሩ መሆናቸውንም አስታውሰው እኛም በዚህ በሕይወት ምስክርነታችን ምን ያህል ብርቱዎች ነን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት መተው የለበትም፣

በማቴ. ወንጌል በምዕ. 25 ላይ የተጠቀሰውን የሦስቱ አገልጋዮች ምሳሌ መልሰው ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፍርሃት በመያዙ የተነሳ በተሰጠው ሃብት ምንም ያላተረፈውን አገልጋይ ኢየሱስ “አንተ ክፉ እና ሰነፍ አገልጋይ” እንዳለው ገልጸው ምንም ትርፍ ባለማምጣቱ እና የተሰጠውን ሥራ ማከናወን ሲገባው ወደ ጎን በማድረጉ ምክንያት እንደ በደለኛ መቆጠሩን አስረድተው፣ የቀረበልንን ጥሪ ወደ ጎን ማድረግ የወንጌል አገልግሎት ተልዕኮን ይቃረናል ብለዋል።

በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት በደልን መፈጸም፣

የወንጌልን ደስታ ወደ ሌሎች ዘንድ ሳናደርስ ስንቀር፣ በሰዎች መካከል የተጠላን እና ተቀባይነትንም ያጣን አድረገን ብንቆጥር፣ በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ላይ በደልን የምንፈጽም መሆናችንን አስረድተዋል። በቤተክርስቲያን የአገልግሎት ሕይወት፣ በዓለም አካባቢም ነገሮች ወደ ከፋ ደረጃ እየሄዱ ናቸው ብለን በማማረር የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎታችን የምናቋርጥ ከሆነ፣ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎትን እንበድለዋልን ብለዋል። ሕይወትን እንደ ውድ የእግዚአብሔር ስጦታ አድርገን የማንቀበል ከሆነ፣ ለፍርሃት የምንገዛ ከሆነ፣ በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት የእኛን ድጋፍ ለሚጠይቁት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ቅድሚያን የማንሰጠ ከሆነ፣ በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ላይ በደልን እንፈጽማለን ብለዋል።

በጉዞ ላይ የምትገኝ ቤተክርስቲያን፣

አደራ የተጣለባትን የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት በትክክል የማትፈጽም ቤተክስቲያን እንደ ቤተክርስቲያን ልትቆጠር አትችልም ያሉት ቅዱስነታቸው የሚያጋጥሟትን በርካታ እንቅፋቶች በመቋቋም፣ እሾሃማ መንገዶችን፣ ሰላም የሌለበት አስጨናቂ መንገዶችን በማቋረጥ  የምትጓዝ ቤተክርስቲያን፣ የምድር ጨው እና የዓለም እርሾ ሆና የምትገኝ ቤተክርስቲያን እርሷ በእርግጥ ቤተክርስቲያን ተብላ ልትጠራ ይገባታል ብለዋል።

ሁላችንም ለወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ተጠርተናል፣

በዚህን ወቅት በተለያዩ የመንግሥት እና የግል ሥራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙትን አባቶች፣ እናቶች እና ወጣቶች፣ ታመው በሆስፒታል ውስጥ የሚገኙትንም ሳይቀር፣ በምንኖርበት አካባቢ ሁሉ፣ እንደ ማንነታችን ቀርበን የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎትን እንድናበረክት እግዚአብሔር የጠራን መሆኑን ተናግረዋል። እግዚአብሔር ሕይወትን እንድንኖር ብቻ ሳይሆን ሕይወትን እስከ መስጠት እንዳለብን ይጠቃል ያሉት ቅዱስነታቸው ለሕይወታችን የምንጨነቅ ሳንሆን በጭንቀት ውስጥ ካሉት ጋር ስቃያቸውን እንድንጋራ ይፈልጋል ብለዋል። በመጨረሻም እግዚአብሔር በወንጌል ምስክርነት አገልግሎታችን ብቻችንን አይተወንም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መንፈስ ቅዱስ መንገዳችንን እያቀና መሪ ስለሚሆነን መበርታት ያስፈልጋል ብለዋል።

02 October 2019, 18:10