ፈልግ

“ያለመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ቤተክርስቲያን የምታደርገው ጉባኤ ስብሰባ እንጂ ጉባሄ ሊባል አይችልም”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 12/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 12/2012 ዓ.ም ባደረጉት የክፍል ዐስራ ሦስት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው ሲሆን “እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ ቤተ ክርስቲያንን በአንድነት ሰብስበው፣ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት ያደረገውን ሁሉ፣ ደግሞም ለአሕዛብ እንዴት የእምነትን በር እንደ ከፈተላቸው ተናገሩ » (ሐዋ 14፡27)  በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን  « ቤተክርስቲያን ያለመንፈስ ቅዱስ ርዳታ የምታደርገው ጉባኤ ስብሰባ እንጂ ጉባሄ ሊባል አይችልም” ማለታቸው ተገልጹዋል።

በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር ከጥቂት ጊዜ በፊት በእናንተ መካከል እኔን መርጦ፣ አሕዛብ የወንጌልን ቃል ከእኔ አንደበት ሰምተው እንዲያምኑ ማድረጉን ታውቃላችሁ። ልብን የሚያውቅ አምላክ ለእኛ እንደ ሰጠን ሁሉ፣ ለእነርሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት የተቀበላቸው መሆኑን መሰከረላቸው፤ ልባቸውንም በእምነት በማንጻት በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። እንግዲህ፣ አባቶቻችንም እኛም ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ? እኛም የዳንነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።” (ሐዋ 15፡7-11)

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥቅምት 12/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደሚናገረው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ከኢየሱስ ጋር ካደረገውና ሕይወቱን ከቀየረው ክስተት በኋላ ባርናባስ ለተጫወተው ሚና ምስጋና ይግባውና ክርስቶስን ማወጅ ጀመረ። ሆኖም፣ በአንዳንዶቹ ጥላቻ ምክንያት ከባርናባስ ጋር አብሮ የትውልድ መንደሩ ወደ ሆንቺው ጠርሴስ የእግዚኣብሔርን ቃል ለማወጅ ወደ እዚያው ለመሄድ ተገዷል። በእዚህ እኛ አሁን በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተንተርሰን በማደረግ ላይ በምንገኘው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የእግዚአብሔር ቃል ያደረገውን ረጅም ጉዞ የተጠቀሰ መጽሐፍ ነው ሊባል ይችላል፦የእግዚአብሔር ቃል መታወጅ እና በየቦታው መዳረስ አለበት። ይህ ጉዞ የሚጀምረው ከከባድ ስደት በኋላ ነው (ሐዋ. 11፣19 ይመልከቱ)፣ ነገር ግን ይህ ለስብከተ ወንጌል ስርጭት እንቅፋት ከመሆን ይልቅ መልካሙን ዘር የሚያሰራጭበትን መስክ ለማስፋት መልካም አጋጣሚ ይሆናል። ክርስቲያኖች አይፈሩም። እነሱ መሸሽ አለባቸው፣ የሚሸሹት ግን ቃሉን ይዘው ነው፣ በእዚህም ምክንያት ቃሉን በየቦታው ያሰራጫሉ።

ጳውሎስና ባርናባስ መጀመሪያ በሶሮያ ወደ ምትገኘው አንጾኪያ ደረሱ፣ ማኅበረሰቡ ሥር መሰረት እንዲኖረው ለማስተማርና ለመርዳት አንድ ዓመት ያህል በእዚያው ቆዩ (ሐዋ. 11: 26)። ለአይሁድ ማህበረሰብ ቃሉን አወጁ። ስለዚህ አንጾኪያ የወንጌል ማስፋፊያ ማዕከል ሆነች - ሁለቱ ወንጌላውያን ማለትም ጳውሎስና ባርናባስ በአንጾኪያ ለመጀመሪያ ጊዜ “ክርስቲያኖች” (የሐዋ 11፡26) ተብለው በተጠሩት የአማኞች ልብ ውስጥ ቃሉን ያቀጣጥላሉ።

የቤተክርስቲያን ባህርይ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ይቀዳል፣  እርሷም ልክ እንደ አንድ ምሽግ አይደለችም፣ ነገር ግን ቦታውን ማስፋት የሚትችል ድንኳን (ኢሳ 54፡ 2 ተመልከት) እና ለሁሉም ተደራሽ ይምትሆን ሥፍራ ትሆናለች። ቤተክርስቲያን “በጉዞ ላይ ትገኛለች” በጉዞ ላይ የማትገኛ ቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያን አይደለችም፣ ቤተክርስቲያን ሁሉም ሰው የሚገባባት ቤተክርስቲያን እንድትሆን ቦታዋን ለማስፋት ሁል ጊዜ እየሠራች ትገኛለች። ቤተክርስቲያን “ሁሌም በሮቿ ክፍት መሆን ይኖርበታል”። እዚህ ባለንበት ከተማ የሚገኙ አንዳንድ አብያተክርስቲያናት፣ ወይም እኔ በመጣሁበት ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አብያተክርስቲያናት በሮች ተዘግተው ይገኛሉ፣ ይህ መጥፎ ምልክት ነው። የቤተክርስቲያን በሮች ሁል ጊዜ ክፍት መሆን አለባቸው፣ ምክንያቱም ቤተ-ክርስቲያን ምን እንደ ሆነች የሚያሳይ ምልክት ነው- ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ክፍት ናት። ቤተክርስቲያን “ሁልጊዜ በአብ ክፍት እንደሆነች ተደርጋ ትጠራለች ፡፡ [...] ስለሆነም አንድ ሰው የመንፈስን እንቅስቃሴ ለመከታተል ቢፈልግ እና እግዚአብሔርን በመፈለግ ወደ እርሱ ቢቀርብ አንድ የተዘጋ በር ቅዝቃዜ አይሰማውም ”።

ነገር ግን እነዚህ በሮች ለማን ነው ክፍት የሚሆኑት?  ለአረማውያን ነው፣ ሐዋርያት ለአይሁድ ስብከተ ወንጌልን ከሰበኩላቸው በኋላ፣ አረማውያን በበኩላቸው የቤተክርስቲያኑን በር ማንኳኳት ጀመሩ፣  እናም ይህ ለአረማዊያን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው በር በአዲስ መልክ ክርክር ያስነሳል። አንዳንድ አይሁዶች ራሳቸውን ለማዳን እና ከዚያ ጥምቀት ለመቀበል በቅድሚያ የግርዘት ስረዓት በመፈጸም አይሁዳዊ የመሆንን አስፈላጊነት ይናገራሉ። አንዳንዶቹ እንደሚናገሩት “በሙሴ ሥርዐት መሠረት ካልተገረዛችሁ ልትድኑ አትችሉም » (ሐዋ 15፡1) በማለት ይናገራሉ፣  ይህ ማለት ደግሞ ካለተገረዙ ጥምቀት መቀበል አይችሉም ማለት ነው። በመጀመሪያ የአይሁድ ሥነ-ሥርዓት እና ከዚያም በመቀጠል ጥምቀት-የሚል አቋም ነበራቸው።እናም ጉዳዩን ለመፍታት ጳውሎስና ባርናባስ በኢየሩሳሌም የሚገኙትን ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያማከሩ ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ገላቲያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው (ገላቲያ 2፡1-10) የኢየሩሳሌም ጉባሄ በመባል የሚታወቀው ጉባሄ ይካሄዳል።

በጣም ደስ በሚል መልኩ ሥነ-መለኮታዊ ፣ መንፈሳዊ እና ሥነ-ሥርዓትን የተመለከቱ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን - ይኸውም በክርስቶስ ማመን እና የሙሴን ሕግ በመጠበቅ መካከል ያለ ግንኙነት ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል። በጉባሄው ወቅት ወሳኝ የሆኑት እናት የሆነችው ቤተክርስቲያን “ዓምዶች” በመባል የሚታወቁት የጴጥሮስ እና የያዕቆብ ንግግሮች ወሳኝ የሚባሉ ንግግሮች ነበሩ። (ሐዋ. 15፡ 7-21 ፣ ገላ 2፡9 ይመልከቱ)። እነሱ በአረማዊያን ላይ የግርዘት ስረዓትን ላለመጫን የተስማሙ ሲሆን ነገር ግን አረማዊያን የጣዖት አምልኮን እና ሁሉንም የጣዖት አምልኮ መግለጫ የሆኑ ነገሮች እንዲክዱ ብቻ ይጠይቋቸዋል። ከውይይቱ አንድ ማዕከላዊ የሆነ መንገድ ይወጣል፣ እናም ይህ ውሳኔ ጸድቆ ሐዋርያዊ መልእክት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ወደ አንጾኪያ ይላካል።

በኢየሩሳሌም የተካሄደው ጉባሄ ልዩነቶችን ለመጋፈጥና “በእውነተኛ ፍቅር” ላይ ተመስርተን እውነትን ለመፈለግ የምንጠቀምበት መንገዶች ላይ አንድ ወሳኝ ብርሃን ይፈነጥቃል (ኤፌ 4፡15)። የቤተክርስቲያን የግጭት አፈታት ዘዴ ቀርቦ እና በትዕግስት በማዳመጥ በሚደረግ ውይይት እና በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በመታገዝ በማስተዋል ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስታውሰናል። በእውነቱ ጥሩ ወደ ሆነ አንድነት እንዲደርሱ የሚያደርግ ዝግ ከመሆን በመውጣት እና ውጥረቶችን ለማሸነፍ የሚረዳ እና በልቦች ውስጥ የሚሠራ መንፈስ ነው። ጉባሄውን ካጠቃለሉ በኋላ የጻፉት ደብዳቤ በጣም አስገራሚ የሆነ ደብዳቤ ሲሆን ሐዋርያቱ ደብዳቤውን መጻፍ የጀመሩት ደግሞ  “መንፈስ ቅዱስ እና እኛ እንደዚያ ብለን እናስባለን…” በማለት ይጀምራል። መንፈስ ቅዱስ በእዚያ ስፍራ መገኘቱ ለጉባሄው ሥነ-ሥርዓት ተገቢ እና አስፈላጊ ነው፣ ካልሆነ ግን ጉባሄ ሊባል አይችልም እንዲያው የተደረገ አንድ ውይይት፣ ስብስባ ወይም በፓርላማ የተደረግ ክርክር ወዘተ ሊባል ይችል ይሆናል።

በሁሉም ክርስቲያኖች ፣ በተለይም በጳጳሳት እና በቄሳውስት ውስጥ ሕብረትን የማጠናከር ፍላጎት እና ኃላፊነት እንዲያጠናክር እና እንዲያነሳሳ ጌታን እንለምናለን። የብዙ ልጆች “ደስተኛ እናት” ተብላ በተጠራችው ቤተክርስቲያን ፍሬያማ ለማደረግ እና ፍሬዋን ለማሳየት፣ በውይይት፣ በማዳመጥ እና ርቀው ከሚገኙ ከወንድሞች ጋር በእምነት ለመገናኘት እንድንችል እንዲረዳን እንማጸነው።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
23 October 2019, 17:39