ፈልግ

ቅዱስነታቸው የጦር ሠራዊት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪዎችጋር በተገናኙበት ወቅት፣ ቅዱስነታቸው የጦር ሠራዊት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪዎችጋር በተገናኙበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጦር ምርኮኞች ሰብዓዊ መብት መከበር እንዳለበት አሳሰቡ።

ጥቅምት 20/2012 ዓ. ም. አምስተኛውን ዙር ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ስልጠናን ለተከታተሉት የጦር ሠራዊት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ካህናት ንግግር ማድረጋቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ካህናቱ የተሳተፉበት ስልጠና ርዕስ “ግጭቶች እና አመጾች በሚቀሰቀሱበት ወቅት የግለሰቦች መብት እና ነጻነት ሲገፈፍ የሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ካህን ሚና” የሚል መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ወቅት ስልጠናውን ያስተባበሩትን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑትን ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰንን እና ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎን በቅድስት መንበር የብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት አስተባባሪን አመስግነዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከተጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረውን የጦር ሠራዊት ሐዋርያዊ አገልግሎት ስልጠናን በማስታወስ ንግግራቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው በአራተኛው ዙር ስልጠና ወቅት በሕብረተሰቡ መካከል አመጽ በሚቀሰቀስበት ወቅት ሌላው ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ መሆኑን በመዘንጋት እንደ ጠላት መመልከቱ ተገቢ እንዳልሆነ መናገራቸውን፣ ጦርነትም ይሁን ማንኛውም አመጽ በሚቀሰቀስበት ወቅት እያንዳድንዱ የሰው ልጅ እጅግ የተቀደሰ ፍጡር መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

በዛሬው መልዕክታቸውም ጦርነት እና አመጽ በሚቀሰቀስበት ጊዜ መብታቸውን የሚገፈፉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን በማስታወስ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በጦርነት ወቅት ተማርከው በእስር ቤት የሚሰቃዩ ሰዎች መብት ማስከበር ተግባር ወደ ከፋ ደረጃ መድረሱን አስታውስዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ተማርከው እስር ቤት በተወረወሩ ሰዎች ላይ የሚፈጸም የጭካኔ ተግባር አስታውሰው መሠረታዊ መብታቸውን ተነፍገው ጥቃት ፣ አመፅ ፣ የተለያዩ ኢ-ሰብአዊ የሆኑ የማሰቃየት እና የጭካኔ ተግባራት የሚፈጸምባቸው መሆኑን አስታውሰዋል።

ለእገታ፣ የደረሱበት የማይታወቅ እና ለግድያ የሚጋለጡ በርካቶች መሆናቸውን የተናገሩት ቅዱስነታቸው ከእነዚህም መካከል ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ እያሉ ተይዘው የመታሠር፣ የመሰወር እና የግድያ ወንጀል የሚፈጸምባቸው በርካታ ሚሲዮናዊያን፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ እግዚአብሔርን እና ሕዝብን ለማገልገል የገቡበትን ሕይወት ለመስዋዕትነት የሚያቀርቡ በርካታ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች መኖራቸውን ገልጸው ለእነዚህ ነፍሳት በሙሉ ለቤተሰቦቻቸውም ጭምር ተስፋን ሳይቆርጡ በድፍረት ወደ ፊት እንዲጓዙ በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል።

የምርኮኞችን ሰብዓዊ መብት የሚያስከብሩ በርካታ ዓለም አቀፍ ሕጎች መኖራቸውን የስታወሱት ቅዱስነታቸው በተለይም በጦር መሣሪያ በታገዙ አመጾች የሚጠቁ ሰዎች መብት እንዲከበር የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ደንቦች መኖራቸውን ተናግረዋል። የእነዚህ ደንቦች መሠረታዊ ዓላማ እና አስፈላጊነት ስነ ምግባርን በተከተለ መንገድ፣ በጦርነት አደጋ የሚወድቁት ሰዎች ክብርን ማስጠበቅ እና በተግባርም እንዲገልጽ ማድረግ ነው ብለዋል። ይህ ዓለም አቀፍ ሕግ የጦርነት አደጋ ለሚደርስባቸው ተጠቂዎች ብቻ ሳይሆን በጦርነት ወቅት ተማርከው በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ለሚወድቁትም ጭምር ሊያገለግል ይገባል ብለዋል። የሰውን ልጅ ክብር ማስጠበቅ ማለት የታዘዘውን ብቻ አድርጎ መገኘት ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው እና ባለስልጣን ተግባራዊ ለማድረግ የተጠራበት የሞራል ግዴታ ነው ብለዋል።

በዚህ አምስተኛ ዙር የቀረበውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ስልጠናን የተከታተሉት የጦር ሠራዊት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ካህናት ዋነኛ ተልዕኮዋቸው ወደ ጦር ሠራዊቱ አባላት ዘንድ በሚመለሱበት ጊዜ እያንዳንዱ የሠራዊቱን አባል ዓለም አቀፍ ሕጎችን ጠንቅቆ እንዲያውቅ ማድረግ እና በዚህም የተሰጣቸውን የሐዋርያዊ አገልግሎት ግዴታን በአግባቡ መፈጸም እና ማስፈጸም መሆኑን ቅዱስነታቸው አስገንዝበዋል። ለዚህ ሐዋርያዊ አገልግሎት መመሪያ እንዲሆንላቸው በማለት ከማቴዎስ ወንጌል የሚከተለውን ጥቅስ አሰምተዋል፥ “ታስሬ ጎብኝታችሁኛል” (የማቴ. 25፡36)።

እነዚያን በጦርነት ወይም በአመጽ ውስጥ ለወደቁት የእግዚአብሔር ሕዝብ ሊደረግ የሚገባውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ይመለከታል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰልጣኞቹ ባደረጉት ንግግር የተሰጣቸው ሐዋርያዊ ሃላፊነት ሁሉንም ሰው የሚያገናኝ የጋራ ቅርስ፣ ከመጀመሪያውም አንስቶ የነበረ በዘመናት መካከል በሰዎች መካከል ግንኙነት እንዲኖር ታስቦ ቀድሞውኑ የተቀመጠ የተፈጥሮ ሕግ ነው ብለዋል። በጦር ሠራዊቱ ዓለም ተሰማርተው ሐዋርያዊ ግዳጃቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋዮች፣  አገልግሎታቸው ለሰው ልጆች ከሚቀርቡ እና መሠረታዊ መብቱንም ከማስጠበቅ አልግሎቶች መካከል አንዱ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ከሰልጣኞቹ መካከል ስንቶቻቸው ከእነዚያ በጦርነት አውድማ ላይ የሚገኙ የጦር ሠራዊት አባላት ቸርነትን እንዲያሳዩ በማበረታታት እና ምክርን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የጠየቁት ቅዱስነታቸው፣ ዘርን፣ ዜግነትን፣ ባሕልን እና እምነትን ያላገናዘበ ቸርነት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያቀራርብ ሁለንተናዊ ልግስና መሆኑን አስረድተዋል።

የህን የልግስና ሕይወትን ከመጀመር አስቀድሞ ከወላጆቻችን እና ከክርስቲያን ማሕበረሰብ የወረስናቸውን መልካም አስተዳደጎች የተሟሉ ለማድረግ ስልጠናን እና ትምህርቶችን መከታተል አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የርህራሄን፣ የወንድማማችነት፣ የይቅርታን፣ የመልካምነት እና የሰው አክባሪነትን ባሕሪይ ለሁሉም ሰው ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው ወጣቶች የባሕሎቻቸውን እና የሕዝቦቻቸውን መልካም እሴቶች ሳይዘነጉ ዓለማቀፋዊ ማንነትን በማሳደግ በሰዎች መካከል የቤተሰባዊነት ባሕል እንዲያድግ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ በአገር ደህንነት አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን አስመልክቶ የተናገረውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው “በአገር ደህንነት አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት የጦር ሠራዊት አባላት የሕዝብ የደህንነት እና የነጻነት አስከባሪዎች” መሆናቸውን አስረድተዋል።

“ደስታ እና ተስፋ” የሚል ሐዋርያዊ መልዕክት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ስልጠናን የተከታተሉት የጦር ሠራዊት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ካህናት፣ ጦርነት ክርስቲያናው እና በመልካም ስነ ምግባር የታነጹ ሰብዓዊ አሳሰብን የሚያስረሳ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ተስፋን ሳይቆርጡ፣ ምን ጊዜም ቢሆን  ሰብዓዊ ክብር ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ቅድስት መንበር፣ ብሔራዊ የቤተሰብ አንድነት እንዲያድግ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የምታበረክተውን እገዛ እንደምትቀጥልበት አስታውቀው፣ የምሕረት እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ማርያም በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው እንድታግዛቸው በጸሎት የሚረዱ መሆናቸውን ገልጸው ለስልጠና ተካፋዮች በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን በመስጠት ንግግራቸውን ደምድመዋል። በመጨረሻም ሰልጣኞቹ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።     

31 October 2019, 15:44