ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት መሪያችን መንፈስ ቅዱስ ነው”።

ዛሬ መስከረም 21 ቀን 2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በርካታ ምእመናን፣ ነጋዲያንና ሀገር ጎብኝዎች ቅዱስነታቸው የተለመደውን ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ማቅረባቸው ተመልክቷል። በአስተምህሮአቸውም የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት መሪያችን መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ በፊት በጀመሩት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ትኩረት በማድረግ ባቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ ከእስጢፋኖስ ሰማዕትነት በኋላ የኢየሩሳሌም ክርስቲያኖችን ስደት እና መከራ የደረሰባቸው መሆኑን አስታውሰዋል። ዛሬ ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህረት ክርስቶስ አስተምህሮአቸው በፊሊጶስ እና በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ላይ በማትኮር ከእግዚአብሔር በሚገኝ አዲስ ሕይወት ለመኖር ቃሉን እና የቤተክርስቲያን ምስጢራትን በሚገባ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ያለ መንፈስ ቅዱስ እገዛ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎትን ማከናወን የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ባቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ ከእስጢፋኖስ ሰማዕትነት በኋላ በኢየሩሳሌም ቤተክርስቲያን ውስጥ ስደት እና መከራ በመድረሱ ክርስቲያኖች ወደ ገሊላ፣ ሰማሪያ እና ሌሎችም አካባቢዎች መሰደዳቸውን አስታውሰዋል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው በሐዋርያት እና በኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ ስቃይ እና ስደት የተደጋገመ ይሁን እንጂ የወንጌል ምስክርነትን እሳት ሊያጠፋ የማይችል መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአስተምህሮአቸው አስረድተው እንዲያውም የበለጠ እንዲቀጣጠል አድርጓል ብለዋል። በዚህ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ሌላ ታሪክ እናገኛለን ያሉት ቅዱስነታቸው ዲያቆን ፊሊጶስ በሰማሪያ ከተማ ተገኝቶ የወንጌል ምስክርነትን መስጠት መጀመሩንም አስታውሰዋል።

ፊሊጶስ ወደ ሰማሪያ ከተማ ወርዶ ምስክርነትን እየሰጠ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተማር ጀመረ። ወደ እርሱ የቀረበው ሕዝብም ለምስክርነቱ ትኩረትን በመስጠት ያደምጡት ነበር። በእርሱ በኩል ይደረጉ የነበሩ ተዓምራትንም ይመለከቱ ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም በታላቅ ድምጽ እየጮሁ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበር፤ ብዙ ሽባዎች እና አንካሶችም ይድኑ ነበር፤ ስለዚህ በዚያች ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ (የሐዋ. 8፤5-8)።

 

ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ብቻውን በቂ አይደለም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተምህሮአቸውን በመቀጠል በሰማሪያ ከተማ ዲያቆን ፊሊጶስ አንድ የውጭ አገር ዜጋ እንዳገኘ አስታውሰው፣ ልቡንም ወደ እግዚአብሔር በመክፈት፣ በኢትዮጵያ ንግሥት ዘንድ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊነት ከነበረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ጋር መገናኘቱን አስታውሰዋል። በዚህን ወቅት ፊሊጶስ የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ማስረዳት እንዲችል የእግዚአብሔርን እርዳታ መጠየቁንም ገልጸዋል።                     

በፊሊጳስ እና በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ መካከል ከተደረገው ውይይት መረዳት የምንችለው ቃሉን ማንበብ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ለሚነበበው ጽሑፍ መሠረታዊ መልዕክት የቱጋ እንዳለ ለመረዳት የመንፈስ ቅዱስ እገዛ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማስመልከት ለብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ባደረጉት ንግግር፣ “እውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ንባብ፣ የንባብ ዜይቤ ስምረት ብቻ ሳይሆን የራስን ማንነት በሚገባ መረዳት እና በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ራስን በማስገባት፣ ቃሉን እንዳንረዳ ከሚያደርጉን እንቅፋቶች በመውጣት፣ የእግዚአብሔር ሕያው ቃል ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስን ጋር መገናኘት መቻል ያስፈልጋል” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

የወንጌል ምስክርነት እና መንፈስ ቅዱስ፣

ከፊሊጶስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት እንደቻለ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ፊሊጶስም፣ ቤተክርስቲያንም እስከ ዛሬ ድረስ የምትሰብከው እና የምትመሰክረው ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሆነ አስረድተዋል። ይህን ምስክርነት ለመስጠት በጥምቀት የተቀበልነውን እና በኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን እምነታች መመስከር ያስፈልጋል ብለዋል። “ወደ በረሃ በመሄድ ይህን ሰው እንዲያገኘው ፊሊጶስን የገፋፋው ማን ነው?” በማለት የጠየቁት ቅዱስነታቸው፣ “የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት መሪ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው” ብለው ያለ መንፈስ ቅዱስ እገዛ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎትን ማከናወን የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው ሳምንታዊውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባጠቃለሉበት ወቅት እንዳስረዱት ለወንጌል ምስክርነታችን፣ ለምንከፍለው ሰማዕትነት እና ቃሉ ፍሬያማ እንዲሆን ለሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ አደራ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። በተጠመቁት ሰዎች፣ በወንዶች እና በሴቶች አማካይነት ሰዎችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥራት እንዲችሉ፣ ለእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እድልን መስጠት የሚያውቁበትን፣ ሌሎችን በጌታ ፊት ነፃ ማድረግን እንዲያውቁ ለመንፈስ ቅዱስ አደራ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። 

02 October 2019, 17:55