ፈልግ

ቅዱስነታቸው ከማርኬ አውራጃ ካፑቺን ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ጋር፤ ቅዱስነታቸው ከማርኬ አውራጃ ካፑቺን ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ጋር፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ትሑት እና ድሃ የወንጌል አገልጋይ ልትሆኑ ይገባል”!

ቅዱስነታቸው በኢጣሊያ ውስጥ የማርኬ አውራጃ ካፑቺን ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞችን በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ጊዜ  እንደገለጹት ወንድሞቹ በሕይወታቸው ትሑት እና ድሃ የወንጌል አገልጋዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል። መስከረም 29/2012 ዓ. ም. ወደ ቫቲካን ለመጡት 73 ካፑቺን ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክታቸው ጥሪን፣ የድህነት ሕይወትን፣ ምሕረትን እና የወንጌል አገልግሎትን በማስመልከት ንግግር ማድረጋቸውን “ኦዜርቫቶሬ” የተሰኘ የቅድስት መንበር ጋዜጣ በእትሙ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽን መስጠት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለፍራንችስካዊያን ወንድሞች ባቀረቡት ንግግር እግዚአብሔር ሰዎችን በተለያዩ መንገዶች  እንደሚጠራቸው፣ ለሕይወት መለወጥም እንደሚጋብዛቸው አስታውሰዋል። በማከልም ይህ ምርጫ የቅድስና ህይወትን ለመኖር የወሰነ ሰው በዘለዓለማዊ ሕይወት ጎዳና እንዲጓዝ የሚያደርግ ነው ብለዋል። በዚህ ጎዳና እንዳይጓዝ ከሚያደርጉት መሰላክሎች መካከል አንዱ የእግዚአብሔርን ግብዣ ለመቀበል ወደ ኋላ ማለት ነው ብለው ይህም ከውስጣችን ደስታን የሚያስወግድ የመንፈሳዊነት ጠንቅ ነው ብለዋል።

የቅድስናን ሕይወት የመረጡት ሰዎች ስለ ፍትህ ማውራትን ይመርጣሉ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህ ሰዎች ብዙን ጊዜ በራሳቸው ላይ ጉዳት እንደሚደረሰባቸው በማሰብ ዘወትር ሲያንገራግሩ ይታያሉ ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ የሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅ፣ ቅድስት ተሬዛ በራስ ላይ የፍትህ መጓደል እንደደረሰ አድርጎ ከሚያስቆጥር ፈተና መራቅ እንደሚያስፈልግ ማሳሰቧን አስታውሰው ዘወትር ማንገራገርን ማስወገድ የሚቻለው የሕይወት መለወጥን በማምጣት ነው ብለዋል። በማሕበር መኖር ማለት ወደ ትህትና ሕይወት የሚመራ የማያቋርጥ የዕለተ ዕለት የሕይወት መለወጥ ነው ብለዋል።

በገርነት እና በድህነት ስለ ክርስቶስ መመሥከር፣

በግልጽ መናገር እንደሚያስፈልግ ለፍራንችስካዊያን ወንድሞች ያስረዱት ቅዱስነታቸው፣ እንደ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሕይወት የመረጥነው ሕይወት የምስክርነት ሕይወት ነው ብለው በመሆኑም ሕይወታችን የወንጌል ሕይወት አገልግሎት ነው ብለዋል። ለቅድስና ሕይወት እንደመጠራታችን ጭንቀታችን ለገዛ ሕይወታችን ሳይሆን ለወንጌል ምስክርነት ሊሆን ይገባል ብለዋል። ቅዱስ ፍራንችስኮስ ራሱ እንደተናገረው የወንጌል ምስክርነታችን የቃል ከመሆን ይልቅ የሕይወት ምስክርነት መሆን አለበት ያለውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ጥረታችን ሰዎች ሐይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ ሳይሆን በሕይወት ምስክርነታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስበክ መሆን አለበት ብለዋል።

ቅድስት ማዜር ተሬዛን ጨምሮ የዘመናችን ቅዱሳን በሚያምኑት እና በማያምኑት ሰዎች ዘንድ ሊከበሩ እና ሊወደዱ የበቁት በሕይወት ምስክርነታቸው መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካፑቺን ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞችም የሕይወት ምስክርነታቸው ገርነት ያለበት፣ ከሁሉም በላይ በድህነት ኑሮ የተመሰከረ መሆን አለበት ብለው ይህን ሕይወት የሚያደናቅፍ ሌላ ሕይወት ሊኖር አይገባም ብለዋል።

ዓለማዊ መንፈስ ቤተክርስቲያንን ሊጎዳት ይችላል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከማርኬ አውራጃ ለመጡት የካፑቺን ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞች ባደረጉት ንግግር የዓለማዊነት መንፈስ ቤተክርስቲያን ሊያታልላት እንደሚችል ተናግረውል። ይህ መንፈስ ቤተክርስቲያንን ሊጎዳት እንደሚችል አስረድተው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ዘንድ ባቀረበው ጸሎቱ ከዓለም ለመራቅ ሳይሆን ሊያጠቃን ከሚችል ከዓለማዊ መንፈስ መራቅ እንደሚያስፈልግ መጠየቁን አስታውሰዋል። ይህን አጥፊ መንፈስ ለመዋጋት የትህትና ሕይወት መኖር ያስፈልጋል ብለዋል።

ሌላው የቤተክርስቲያን ፈተና ቤተ ክህነትን ከቤተክርስቲያን አገልጋይነት ወደ ጌትነት ባሕሪያ እንዲያዘነብሉ የሚያደርግ ፈተና ነው ብለዋል። ከዚህ ፈተና መውጣት የሚቻለው በቤተክህነት ውስጥ የሚገኙትን ልዩ ልዩ የአገልግሎት መዋቅሮችን ለይቶ በማወቅ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም ፍራንችስካዊያን ወንድሞቹ የማህበራቸውን ደንብ እና መመሪያን በተግባር እንዲኖሩበት፣ ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር ተከባብረው እንዲኖሩ አሳስበዋል። በወንድማማችነት አብሮ መኖር ተፈጥሮአዊ ነው ብለው ይቅርታን በመደራረግ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያድግ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ነው ብለዋል።

ለአውሮጳ የወንጌል ምስክርነት ያስፈልጋታል፣

በአውሮጳ ውስጥ የወንጌል አገልግሎትን ማበርከት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማደግ ላይ የሚገኙ ቤተክርስቲያናት የእምነት ምስክርነታቸውን ወደ አውሮጳም ማዳረስ ይኖርባቸዋል ብለዋል። ለዚህም ባደጉት አገሮች በሥራ ተሰማርተው የሚገኙ የፊሊፒን አገር ሴቶች ክርስቲያናዊ ምስክርነት እንደ ጥሩ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል ብለዋል። ከሕጻናት ጋር በሚያደርጉት ውይይቶች  መልካም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ይሆናሉ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከማርኬ አውራጃ ከመጡት የካፑቺን ፍራንችስካዊያን ታናናሽ ወንድሞችን ጋር በቫቲካን ውስጥ ያደረጉትን ቆይታ ከማብቃታቸው በፊት ባሰሙት ንግግር ፍራንችስካዊያን ወንድሞች፣ በፍራንችስካዊ ሕይወት ለተማረኩት በርካታ ወጣቶች የሕይወት ምስክርነታቸውን ማሳየት እንዲጀምሩ እና ለዘመናት ሲታይ የቆየውን የቅዱስ ፍራንችስኮስ የደስታን እና የታናሽነትን አርዕያ መመስከር እንዳለባቸው አደራ ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

                

11 October 2019, 17:07