ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጥቅምት ወር የጸሎት ሃሳባቸውን ወደ ምእመናን ዘንድ ልከዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለጥቅምት ወር እንዲሆን ብለው ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ምእመናን በወንጌል ማዳረስ አገልግሎት ላይ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት እና ትንሳኤውን ለመመስከር በዓለም ተሰማርተው የሚገኙትን የወንጌል ልኡካን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለውናል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው የቤተክርስቲያንን የወንጌል መልዕክተኛነት እና የሐዋርያዊነት አገልግሎት ሕይወቷን በማስታወስ፣ ለቤተክርስቲያን ፍሬያማነት እና በሐዋርያዊ የወንጌል አገልግሎት ላይ ተሰማርተው ለሚገኙት በሙሉ ድጋፍ የሚሆኑትን ጸጋዎችን በጸሎት የምንጠይቅበት ወቅት እንደሆነም አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ለተቀሩት የቤተክርስቲያን አገልግሎቶች ቀዳሚ ምሳሌ ነው” ያለው መልዕክታቸው ባሁኑ ወቅት በብዙ አካባቢዎች የክርስትና እምነት እየተወለደ እና እያደገ በመሆኑ ልዩ ትኩረትን መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑ ተገልጿል። በአሁኑ ጊዜ በአፍሪቃ፣ በእስያ፣ በኦሼኒያ ደሴቶች እና በላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ 1,109 አዳዲስ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎቶች የተጀመሩባቸው አካባቢዎች መኖራቸው ታውቋል። በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ 37 ከመቶ የሚሆነው አገልግሎት በወንጌል ልኡካን የሚታገዝ መሆኑ ታውቋል። የቤተክርስቲያን ሁለ ገብ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በእነዚህ አዲስ በተመሠረቱት ተጨማሪ ማሕበራዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በኩል የአካባቢው ነዋሪዎች ፍላጎትን ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት ከፍ የምታደርግ መሆኑ ታምኖበታል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቤተክርስቲያኒቱ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች እና ትምህርት መስጫ ተቋማት የሚመሩት ወይም የሚታገዙት በሚሲዮናዊያን መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው እንዳሳሰቡት በዓለማችን ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰብዓዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታው መዋቅሮች ወንጌል ያልተሰበከባቸው መሆኑን አስታውሰው ወደ እነዚህ ሥፍራዎች የወንጌልን መልካም ዜና መውሰድ ሁሉን አቀፍ ጥሪ መሆኑንም አስገንዝበዋል። ይህ የወንጌል ተልዕኮ ስዎች የያዙትን የእምነት መንገድ ለቀው ወደ ሌላ እምነት እንዲሄዱ የሚያደርግ አለመሆኑን አስረድተው ዓላማው የእግዚአብሔርን ዘለዓለማዊ ሕይወት፣ በምህረት የተሞላውን ፍቅሩን እና ቅድስናውንም ለመንገር እና ለመመስከር መሆኑን ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው አስረድተዋል።

ለዚህ የወንጌል አገልግሎት የሚያሰማራን፣ አብሮን በመጓዝ የሚመራን እና ጥበብን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ክሁሉም በፊት የዚህ ሐዋርያዊ አገልግሎት መጀመሪያ የሆነው ከወንጌል የሚገኝ ደስታ ነው ብለው በመሆኑም አገልግሎቱ የሕዝቦችን ባሕል እና የኑሮ ወግን ያከበረ እንዲሁም የእያንዳንዱን ሰው መብት እና ክብር ያከበረ መሆን ይጠበቅበታል ብለው ለወንጌል ተልዕኮ የዘወትር ሃይል እና አጋዥ ጸሎት ነው ብለዋል።

በካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል እና የዚህ ዓለም አቀፍ የምዕመናን ጸሎት ሕብረት አስተባባሪ እና የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ እንዳስገነዘቡት በወንጌል ተልዕኮ ብዙ ጉልበትን በማፍሰስ ብዙ መሥራት እንችላለን፤ ነገር ግን በጸሎት በኩል የምናገኘው ሃይል ካልታከለበት፣ በመንፈስ ቅዱስም ተመከተን ሳይሆን በራሳችን እውቀት የምናደርግ ከሆነ እውነተኛ ፍሬን ማግኘት አንችልም ብለዋል። ያለፈ ልምዳችንም እንደሚያመለክተን ለአገልግሎት የሚያበቃንን፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ሕብረትን በመፍጠር፣ ለማቅረብ የምንመኘውን የወንጌል አገልግሎት በአካባቢያችንም ሆነ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት በሙሉ እንድናበረክት ያደረገን ጸሎት ነው ብለዋል።  የወንጌል ተልዕኮ ግዴታ ያለበት የሥራ ዘርፍ ሳይሆን በጥምቀት የተቀበልነው የደስታ ሙላት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን የአዲስ ሕይወት ውጤት በመሆኑ ለሌሎችም ማዳረስ ያስፈልጋል ብለዋል።

በዚህ ለወንጌል መልዕክተኞች በሚደረግ የጸሎት ሃሳባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የጥምቀትን ጸጋ ተቀብለው ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠረታት እና ከጥንትም ጀምሮ የወንጌልን መልካም ዜና ለዓለም እንድታዳርስ አደራ የተሰጣት ቤተክርስቲያን አባል የሆኑትን በሙሉ መንፈስ ቅዱስ እንዲያግዛቸው ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 October 2019, 17:36