ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጉባኤው ተካፋዮች መካከል፤ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጉባኤው ተካፋዮች መካከል፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጳጳሳት ሲኖዶስ መካከል መግባባት እና የአገልግሎት ስሜት እንዲኖር አሳሰቡ

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መልካም መግባባት በመፍጠር የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦችን ማገልገል ያስፈልጋል በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማሳሰባቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ዘገባ አስታውቋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የብጹዓን ጳጳሳቱን ጉባኤ እሑድ መስከረም 25/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት የከፈቱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጉባኤው ተካፋዮች ጋር በጉባኤው አዳራሽ በተገኙበት ወቅት ባሰሙት ንግግር የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ አራት ይዘቶች እንዳሉት ገልጸው እነርሱም ሐዋርያዊ፣ ባሕላዊ፣ ማሕበራዊ እና ስነ ምሕዳራዊ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሲኖዶሱ ሐዋርያዊ ይዘት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሲኖዶሱን ሐዋርያዊ ይዘቱ ሲያብራሩ ሁሉንም ርዕሰ ጉዳይ የሚያካትት እጅግ አስፈላጊ ነው ብለው እውነተኛ ግንዛቤን ለማግኘት በክርስቲያናዊ ልብ በመታገዝ የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦችን የኑሮ እውነታን በሐዋርያዊ ዓይን መመልከት ያስፈልጋል ብለው ትርጉሙንም ማወቅ የሚቻለው ይህን መንገድ በመከተል ብቻ ነው ብለዋል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ሐዋርያዊ ይዘትም የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች የቆየ ታሪካቸውን፣ ባሕላቸውን እና የኑሮ ወጋቸውን ማክበር እንዳለብን ያሳስባል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እያንዳንዱ ሕዝብ የራሱ ጥበብ፣ የማህበራዊ ሕይወት ግንዛቤ እና አመለካከት አለው ብለዋል።

የርዕዮተ ዓለም ቅኝ ግዛት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም የርዕዮተ-ዓለም ቅኝ ግዛት ባሕልን አሳንሶ በመመልከት ወይም ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ሕዝቦች ማንነታቸውን እንዲያጡ ስለሚያደርግ ጥንቃቄን ማድረግ ያስፈልጋል በማለት የጉባኤውን ተካፋዮች አሳስበዋል። ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦች በማሕበረሰብ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ስነ ምርምሮችን በማድረግ ግንዛቤን ለማስጨበጥ ጥረት ያድርግ እንጂ ሳይመለከታቸው የሚያልፋቸው ርዕሥ ጉዳዮችም አሉ ብለው የሕዝቦችን ባሕል እና የኑሮ ስርዓትን አሳንሶ መመልከት ክፍፍልን ይፈጥራል ብለዋል።

ብልጽግና እና ኋላ ቀርነት በማለት ሁለት የሰዎችን የዕድገት ደረጃዎች እንደ ምሳሌ የተመለከቱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰዎችን እነዚህ ሁለቱ ጎራዎች በሰዎች መካካል መከፋፈልን ለመፍጠር፣ ሕዝቦችን በደረሱበት የዕድገት ደረጃ በመመደብ ግንኙነታቸውም በርቀት እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች ባቀረቡት ተጨማሪ ማሳሰቢያቸው የሰዎችን ጠቅላላ እውነታን መሠረት በማድረግ ማሰብ መወያየት እንደሚያስፈልግ አሳስበው የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ የተሰበሰበው የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ባሕልን እና እምነትን ወደ ጎን በማድረግ ለማሕበራዊ ዕድገት የሚያገለግሉ ውጥኖችን ለመዘርጋት አይደለም ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እዚህ የተገኘንበት ዓላማ የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች የሚገኙበትን ደረጃ ለማሰብ ፣ ለመረዳት እና ለማገልገል ነው ብለዋል።

የሲኖዶሱ መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው፣

በመካሄድ ላይ የሚገኝ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ይህን መምሰል ይኖርበታል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መንፈስ ቅዱስ ወደሚመራን አቅጣጫ በመመልከት በሕብረት መራመድ ያስፈልጋል ብለዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በቁጥር በርካታ መቀመጫን የያዘ ወይም የተወሰን ወገን ውሳኔ ጎልቶ የሚታይበት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ሃይል እና እገዛ የሚታይበት፣ በብጹዓን ጳጳሳቱ አማካይነት ሥራውን የሚያከናውንበት ነው ብለዋል።      

ትህትና እና ደስታ እንዲታይ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻ ላይ ለጉባኤው ተካፋዮች ባቀረቡት ማሳሰቢያቸው በጉባኤው ወቅት በጥልቅ ማሰብ እና ማስተንተን፣ በግልጽ መወያየት፣ በትህትና መደማመጥ እና በድፍረት መናገር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ እርስ በእርስ መከባበር፣ ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችን በማቅረብ፣ ማስተዋል በታከለበት አኳኋን ሃሳብን በደስታ በመግለጽ ጉባኤው በሁሉም አቅጣጫዎች ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።   

08 October 2019, 17:09