ፈልግ

ቅዱሳት መጻሕፍት፤ ቅዱሳት መጻሕፍት፤ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ልዩ የቃለ እግዚአብሔር እሑድን አጸድቀው ይፋ አደረጉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መስከረም 19/2012 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ከታላላቅ የቤተክርስቲያን በዓላት በኋላ የሚከበረው ሦስተኛ እሑድ፣ ይህም ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀተ በኋላ የሚውለው ሦስተኛ እሑድ ልዩ የቃለ እግዚአብሔርን እሑድ እንዲሆን ብለው ማጽደቃቸው ታውቋል። ይህ ሦስተኛው ዕለተ ሰንበት በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ምእመናን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ጥልቅ አንተንትኖን በማድረግ አብረው የሚያጠኑበት፣ ወደ ሌሎችም ዘንድ ለማድረስ የሚነሳሱበት እንዲሆን በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግል ተነሳሽነት በማጽደቅ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን ይፋ ያደረጉበት መስከረም 19 ቀን 2012 ዓ. ም. የላቲን ስርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሄሮኒሞስ ያረፈበት 1600ኛ ዓመት መታሰቢያ ዕለት መሆኑ ታውቋል። ቅዱስ ሄሮኒሞስ የግሪክ ቋንቋ በስፋት በሚነገርበት የሮማዊያን ዘመነ መንግሥት የኖረ እና ቋንቋውንም አጥርቶ የሚናገር ታላቅ የስነ መለኮት አዋቂ እንደነበር ሲታወቅ በግሪክ ቋንቋ ተጽፎ ከሚገኘው መጽሐፍ ቅዱስ መካከል በርካታ ቅዱሳት መጽሐፍትን ወደ ላቲን ቋንቋ ተርጉሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ ያበቃ የቤተክርስቲያን አባት መሆኑ ይታወቃል። እነዚህን ቅዱሳት መጽሐፍትን ወደ ላቲን ቋንቋ ተርጉሞ ባቀረባቸው ጊዜ እንደተናገረው “ቅዱሳት መጽሐፍትን መረዳት አለመቻል ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳለማውቅ ይቆጠራል” ማለቱ ይታወሳል።               

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት ርዕሥ በላቲን ቋንቋ “Aperuit illis” የሚል ሲሆን በግርድፉ ሲተረጎም “ግልጽ ሆነላቸው” የሚል ሲሆን ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ውስጥ (ሉቃ. 24.45)  ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ በመታየት ቅዱሳት መጻሕፍትን መረዳት የሚችሉበትን አእምሮ እንደከፈተላቸው የሚገልጽ ክፍል መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል።    

ለጥያቄዎች ምላሽን መስጠት፣

በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን የማንበብ እና የማወቅ አስፈላጊነትን በማስመልከት ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ያስቀመጣቸውን ውሳኔዎች ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግል ተነሳሽነት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልእክታቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ምዕመናን ላቀረቡት ጥያቄ መልስ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፋይዳነቱ፣

ከታላላቅ የቤተክርስቲያን በዓላት በኋላ የሚከበረው ሦስተኛ እሑድ፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ ምእመናን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ጥልቅ አንተንትኖን በማድረግ አብረው የሚያጠኑበት፣ ወደ ሌሎችም ዘንድ ለማድረስ የሚነሳሱበት እንዲሆን በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የእግዚአብሔርም ቃል እንደሚያሳስበን ሁሉ፣ ቅዱሳት መጽሐፍትን ከሚከተሉት እና ከሚያዳምጡት የክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር ያለንን እውነተኛ አንድነት ለማጠንከር ትልቅ መንፈሳዊ ሃይል የሚጨምር መሆኑን አስታውቀዋል።     

ምእመናን የሚገንኙበት ክብረ በዓል እንዲሆን፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከቶች ሥር የሚገኙት ቁምስናዎች፣ ልዩ የቃለ እግዚአብሔርን እሑድ በሕብረት ሆነው የሚያሳልፉበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል። ቅዱስነታቸው በማከል ምዕመናን ለእግዚአብሔር ቃል ትልቅ መንፈሳዊ ዋጋን እና አክብሮትን እንዲሰጡት ለማሳሰብ በክብረ በዓሉ ዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ በቤተክርስቲያን ውስጥ ምእመናን በቀላሉ ማየት በሚችሉበት ከፍታ ሥፍራ እንዲቀመጥ አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወንጌልን የምስራች ቃል ለሌሎች ማወጅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባሉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት በሚቀርቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ላይ አስተንትኖን የሚያደርጉት ካህናት በቅዱሳት ንባባት ላይ ብቻ ትኩረትን እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የቁምስናው መሪ ካህንም ዕለቱ በሚከበርበት ዕለት መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ፣ ማሰላሰል፣ የተለየ ክብርን መስጠት እና ጸሎትንም ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስን ለምእመናን በማቃበል መግለጽ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ይዳረስ፣

መጽሐፍ ቅዱስ ለተወሰኑት ሰዎች ብቻ የተሰጠ አይደለም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መልዕክቱን ለመስማት እና በቃላቸውም እንዲይዙት ለተጠሩት በሙሉ የተሰጠ ስጦታ ነው ብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በተወሰኑት ሰዎች እጅ ብቻ የሚቀመጥ እንዳልሆነ አስረድተው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕዝብ መጽሐፍ እንደሆነ ገልጸው፣ የምጽሐፍ ቅዱስን መልካም ዜና ሰምተው እና ተቀብለው ተበታተኑትነው የሚገኙት በሙሉ በአንድ ጥላ ሥር እንዲሰበሰቡ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የወንጌል አስተምህሮ ጥቅም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው የቁምስናው መሪ ካህናት ለምዕመናን በሙሉ የቅዱስት መጻሕፍትን መልዕክት በማብራራት እና በማስረዳት ሰፊ አገልግሎትን ማበርከት እንዳለበት ገልጸው፣ ካህናት የሚያቀርቡት የወንጌል ስብከት የቤተክርስቲያን ቅዱሳት ምስጢራት ያህል ክብር የሚሰጠው መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በቅዱሳት መጽሐፍት ንባባት ላይ የሚቀርቡ የአስተንትኖ ትምህርቶች መርዘም እንደሌለባቸው አሳስበው ከርዕሡም መውጣት የለባቸውም ብለዋል። በቅዱሳት መጽሐፍት ንባባት ላይ የሚቀርቡ የአስተንትኖ ትምህርቶች በርካታ ምእመናን የእግዚአብሔርን ቃል ታላቅነት የሚያውቁበት እና በዕለታዊ ኑሮም ተግባራዊ ለናድረግ ጥረት የሚያደርጉበት ብቸኛው ዕድል በመሆኑ በሚገባቸው ቋንቋ መቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በቅዱሳት መጽሐፍት እና የቤተክርስቲያን ቅዱሳት ምስጢራት፣

በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ከነበሩት ሐዋርያት ጋር መገናኘቱን ያስታወሱ ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ይህም በቅዱሳት መጽሐፍት እና በቤተክርስቲያን ቅዱሳት ምስጢራት መካከል የማያቋርጥ ግንኙነት መኖሩን ያመለክታል ብለዋል። በየትም ይሁን ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይናገራሉ ያሉት ቅዱስነታቸው የሞቱን እና የትንሳኤውን ታሪክ የሚያስታውሱን እንጂ አፈ ታሪክ አይደሉም ብለው ለሐዋርያቱም እምነት መሠረት መሆናቸውን አስረድተዋል። የቤተክርስቲያን ቅዱሳት ምስጢራት የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት ሲያገኙ እና በዚህ መልክ ማብራሪያ ሲሰጣቸው የኢየሱስ ክርስቶስን የማዳን ሥራ በእምሮአችን እና በልባችን መገንዘብ እንድንችል ያግዙናል ብለዋል።

የመንፈስ ቅዱስ ሚና፣

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ሚና መሠረታዊ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመንፈስ ቅዱስ እገዛ ካልታከለበት ቅዱሳት መጽሐፍት እንደ ጽሑፍ ብቻ ሆነው የመቅረት ዕድል ሊያጋጥም ይችላል ብለው ይህም የቅዱስት መጽሐፍትን መንፈሳዊነት በማሳነስ ወደ አክራሪነት ንባብ መንገድ ይከፍታል ብለዋል። የእግዚአብሔርን ቃል ሕያው እና በእምነትም ወደ ቅዱስ ሕዝብ እንዲደርስ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃል እንድናሳድግ ያስፈልጋል ብለው ይህን በተግባር ለማየት ከእግዚአብሔር ጋር እንዲሁም ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ሙሉ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ምሕረቱን መቀበል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ ትልቁ ፈተና የሚሆነው መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚለውን አድምጠን ከዚያም የእግዚአብሔርን ምህረት በሕይወታችን ውስጥ መለማመድ ነው ብለዋል። የእግዚአብሔር ቃል ዓይኖቻችንን ከፍተን ከግለኝነት ሕይወት ወጥተን በአዲስ መንገድ ከሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በሕብረት እንድንኖር የሚያስችል ሃይል አለው ብለዋል። የእግዚአብሔርን ቃል በልባችን እንድንቀበለው የምትረዳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቃሉን ሰምተው እና በልባቸው ይዘው የሚያገኙትን ደስታ እኛም እንድንማር ታግዘን በማለት ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

                 

01 October 2019, 17:34