ፈልግ

ለዕለት ምግብነት የሚሆን ዳቦ፣ ለዕለት ምግብነት የሚሆን ዳቦ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ለድሆች መሆን የሚችል እንጀራን ሰብስበን መልሰን እናባክናለን”።

ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ. ም. የተከበረውን የዓለም የምግብ ቀን ምክንያት በማድረግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት ባልደረባ በነዴታ ካፔሊ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ለተራቡት ሰዎች ሊሆን የሚችል በርካታ ምግብ በከንቱ የሚባክን እና የሚጣል፣ በተወሰኑት አገሮች ውስጥ ተከማችቶ እንደሚገኝ አስረድተው፣ የሰዎች የአኗኗር ልማድ ስርዓትን የተከተለ፣ ከራሳችን፣ ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር እንዲሁም ከአካባቢያችን ጋርም መልካም ግንኙነትን የሚያሳድግ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም ዘንድሮ የተከበረውን የዓለም የምግብ ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት በረሃብ እና በተመጣጣኝ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚያሰሙትን ድምጽ እንድናዳምጥ ይጋብዘናል ብለዋል።

ክቡራን እና ክቡራት አንባቢዎቻችን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥቅምት 5/2012 ዓ. ም. የተከበረውን የዓለም የምግብ ቀን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ ክቡር አቶ ሹ ዶንኝዩ፣ 

ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ጥረቶች ቢደረጉም እስከ 2022 ዓ. ም. ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ የተያዘው የዘላቂ ልማት እቅድ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች በገሃድ እየታየ አይደለም። ረሃብ የተወገደበት ጤናማ እና ተመጣጣኝ ምግብ አቅርቦት በዓለማችን በሚል መርህ የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ጥያቄ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት በምግብ እና በአመጋገብ መካከል የተዛባ ግንኙነት መኖሩን ያመለክታል።

ምግብ ለሕይወት የሚሰጠው ጥቅም እያነሰ በመምጣት ግለሰቦችን ወደ ጥፋት እየመራቸው ይገኛል።  ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን 820 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። በሌላ ወገን 700 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ባልተስተካከለ የአመጋገብ ልማድ ከመጠን ባለፈ ክብደት ጨምረው ይታያሉ። ይህ ችግር ከፍተኛ የምግብ መጠን ባላቸው በበለጸጉ አገሮች ብቻ ሳይሆን በማደግ ላይ ባሉ ደሃ አገሮችም የሚታይ ችግር ነው። ለዚህ ችግር ዋናው ምክንያት በማደግ ላይ ያሉት አገሮች የአመጋገብ ልማዳቸውን ከበለጸጉት አገሮች ስለሚወስዱ ነው። ያልተመጣጠነ የአመጋገብ ልማድ ለተለያዩ በሽታዎች የሚያጋልጥ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ብዙውን ጊዜ የስኳር በሽታ፣ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች እና ለነርቭ መቃወስ ምክንያት ይሆናል። ያልተመጣጠነ የአመጋገብ ልማድም እንደዚሁ ሞትን ለሚያስከትሉ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

 እነዚህ ምልክቶች ተዳምረው የኑሮ ስርዓታችንን እንድናስተካከል ከማሳሰብ በተጨማሪ የተስተካከለ የአመጋገብ ስርዓታች በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ስፍራ እንደሚይዝ ያስገነዝቡናል። ሕይወታችን የሚመካው ከምድራችን በምናገኘው ፍሬ ነው (መዝ. 65: 10-14፤ 104:27-28)። በመሆኑም ይህ የምድራችን ፍሬያማነት በግድ የለሽ እና ሃላፊነት በጎደለው የአጠቃቀም ስርዓት መቃወስ የለበትም። የአመጋገብ ስርዓት ችግሮች ሊወገዱ የሚችሉት፣ ከምድራችን ለምናገኘው ስጦታ ምስጋናን ስናቀርብ፣ ከተስተካከለ የአየር ንብረት፣ ልክን ካከበረ የኑሮ ወግ፣ ጎጂ ከሆኑ የአመጋገብ ልማድ ራስን ከመቆጠብ እና በሕዝቦች መካከል ማሕበራዊ አንድነትን በማሳደግ ነው። የሰውን ዘር ታሪክ የተከተሉ እነዚህ በጎ ተግባራት ይበልጥ ቀላል እና ጤናማ ህይወትን እንድንኖር እና በዙሪያችን የሚገኙት በሙሉ የሚጠይቁንን ፍላጎቶች እንድናሟላላቸው ያሳስቡናል። እንዲህ ዓይነቱን የአኗኗር ስርዓትን በመከተል፣ ማሕበራዊ ጥቅሞችን በማምጣት በወንማማችነት ፍቅር አብረን የምናድግበትን፣ ረሃብን እና ማሕበራዊ ሕይወት አለመመጣጠንን የሚያስከትል የግለኝነትን ሕይወት ማስወገድ እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱ የአኗኗር ስርዓት ከራሳችን ፣ ከወንድሞቻችን እና ከእህቶቻችን ጋር እንዲሁም በምንኖርበት አካባቢ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረን ያስችለናል።

በዚህ የኑሮ ስርዓት መካከል ቤተሰብ ቀዳሚ ሚናን ይጫወታል። ይህን በሚገባ በመገንዘብ የዓለም የእርሻ ድርጅትም በገጠራማው አካባቢ ለሚኖሩ ቤተሰቦች አስፈላውን ጥበቃን በማድረግ የቤተሰብ እርሻ ስርዓትን በማሳደግ ላይ ይገኛል። በቤተሰብ መካከልም ሴት እህቶቻችን እና እናቶች፣ ምድራችን የምትሰጠንን ፍሬ በከንቱ ሳናባክን በክብር እንድንጠቀም የሚያደርገንን ጥበብ በማስተማራቸው ምስጋናን እናቀርባለን። ቤተሰብ ለግልም ሆነ ለማሕበራዊ ጥቅም ክብርን በመስጠት፣ የተስተካከለ የአኗኗር ዘይቤዎችን ለማስፋፋት የሚረዳ መሆኑንም ተገንዝበናል።

በመንግሥታት መካከል እያደገ የመጣው የመደጋገፍ አዝማሚያ ልዩ ፍላጎቶችን ለማስቀረት በሕዝቦች መካከል መተማመን እና ወዳጅነት እንዲያድግ በማድረግ ላይ ይገኛል (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮ 482)። ዘንድሮ ለሚከበረው የዓለም የምግብ ቀን መሪ ቃል ሆኖ የተመረጠው ርዕስ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች የሚታየው የአመጋገብ ስርዓት ያልተስተካከለ መሆኑን እንደሚያስገነዝበን ተስፋ አደርጋለሁ። ለዓለማችን ሕዝብ የሚበቃ ምግብ አለ ተብሎ በሚታመንበት ባሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች በረሃብ ሲሰቃዩ መመልከት፣ በበርካታ አካባቢዎችም ምግብ ሲጣል እና ሲባክን ማየት፣ ብዙዎች ደግሞ ከሚበቃቸው በላይ በመመገብ ክብደታቸው መጠኑን አልፎ ማየት ፍትሃዊነት የጎደለው ነው። ከዚህ ችግር ለመራቅ መደበኛ የሆኑ እና ተደራሽነት ያላቸውን መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለድሃው ማሕበረሰብ የሚያሟሉ ኤኮኖሚያዊ ተቋማትን እና ማሕበራዊ ጥረቶችን ማድረግ ያስፈልጋል (ውዳሴ ላንተ ይሁን 109)።

ለሰዎች ባሕል እና ለማሕበራዊ ሕይወትን ዝቅተኛ ትኩረትን የሰጠ፣ ነገር ግን በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ ትርፍን ለማሳደግ ብቻ የቆመ የገበያ ሥርዓት ረሃብ እና ያልተመጣጠነ የምግብ ስርዓትን ለማስወገድ ምንም አስተዋጽዖን ሊያበረክት አይችልም። ቅድሚያን መስጠት ያለብን ለሰብዓዊ ፍጥረት፣ ወንዶች እና ሴቶች እንዲሁም ሕጻናት፣ በተለይም የዕለት እንጀራን አጥተው በረሃብ የሚሰቃዩን፣ ቤተሰብን ማስተዳደር፣ ማሕበራዊ ግንኙነትን ለማሳደግ አቅም የሚያንሳቸውን በርካታ ሰዎች ማስብ ያስፈልጋል (ውዳሴ ላንተ ይሁን 112-113)። ለሰው ልጅ ቅድሚያ በሚሰጥበት ጊዜ ለሰዎች የሚደረጉ የዕርዳታ አቅርቦቶች፣ የልማት እቅዶች በሙሉ መልካም ውጤቶችን ሊያስገኙ ይችላሉ። በየጎተራዎቻችን የምናከማቻቸው እህሎች እና የምንወረውራቸው ምግቦች ለድሆች የዕለት እንጀራ ሊሆኑ እንደሚችሉ መረዳት ያስፈልጋል።

የተከበሩ የድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ ዘንድሮ ለተከበረው የዓለም የምግብ ቀን ይህን ሃሳብ በማካፍልበት ጊዜ ከዓለም የእርሻ እና የምግብ ድርጅት ጋር በሕብረት የሚሰሩትን በሙሉ፣ ለመላው የሰው ዘር እውነተኛ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ለማምጣት፣ ሰላምንም ለማስፈን የምታደርጉትን ጥረቶቻችሁን በሙሉ እግዚአብሔር ይባርከው”።

ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ከዚህ በላይ የሰማችሁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጥቅምት 5/2012 ዓ. ም. ተከብሮ የዋለውን የዓለም የምግብ ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት ነበር ስላዳመጣችሁን እናመሰግናለን።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
16 October 2019, 15:14