ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የእግዚአብሔርን መንጋ በፍቅር አገልግሉ”!

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መስከረም 23/2012 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት፣ ለአራት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የጵጵስናን ማዕረግ ሰጥተዋል። ቅዱስነታቸው በስነ ስርዓቱ ላይ ባሰሙት ስብከት ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት ለሚያበረክቱላቸው የእግዚአብሔር ሕዝብ ፍቅርን እንዲያሳዩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አራቱ ብጹዓን ጳጳሳት በሚሰማሩበት የቤተክርስቲያን ሃላፊነቶች ላይ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃላፊነቶቹ ከመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ዘመን አንስቶ ሲሰጡ የመጡ ሐዋርያዊ የአገልግሎት ሃላፊነት ናቸው ብለዋል።

ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው፣

“እጆቻቸውን በመጫን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ወደ እነርሱ አስተላለፉ”
“እጆቻቸውን በመጫን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ወደ እነርሱ አስተላለፉ”

“አስራ ሁለቱ ተባባሪዎች በአንድነት ተሰበሰቡ” እጆቻቸውን በመጫን “ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ወደ እነርሱ አስተላለፉ” በማለት የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህ የጵጵስና ማዕረግ አሰጣጥ ስርዓት ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ሲከናወን የቆየ የቤተክርስቲያን ባሕል ነው ብለው ቀዳሚ ዓላማውም የአዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት በሰው ልጅ ታሪክ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው ብለዋል።

በጳጳሳት በኩል የሚናገረን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣

በቤተክርስቲያን አባቶች በኩል የመዳን ቃሉን የሚናገረን፣ በቅዱሳት የእምነት ምስጢራት በኩል በእርሱ ያመኑትን ሁሉ የሚቀድስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አስረድተዋል። ለጳጳሳት ጥበብን እና ማስተዋልን በመስጠት የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ ዘለዓለማዊ ደስታ የሚያደርጉትን ምድራዊ ጉዞ እንዲረዱ ሃይልን የሚሰጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለዋል።

በእግዚአብሔር የተመረጡ ናቸው፣

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የተከናወነ የስመተ ጵጵስና ስነ ስርዓት፤
በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የተከናወነ የስመተ ጵጵስና ስነ ስርዓት፤

አዲስ ለተሰየሙት ብጹዓን ጳጳሳት ምክራቸውን ሲሰጡ፥ ለዚህ አገልግሎታ የሾማቸው እግዚአብሔር ነው ብለዋል። ጵጵስና የአገልግሎት ስያሜ እንጂ ክብር አይደለም። ስለዚህ አንድ ጳጳስ ከሁሉ በላይ ትኩርትን ማድረግ ያለበት በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ላይ ነው ብለው አዲስ የተሾሙት ብጹዓን ጳጳሳት በሚያገኙት አጋጣሚዎች፣ ሲመቻቸውም ሳይመቻቸውም የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና እንዲያበስሩ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እየመከሩ እና እየገሰጹ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮን እንዲያካፍሉ አደራ ብለዋል።

ታማኝ ባለ አደራዎች ሁኑ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለብጽዓን ጳጳሳቱ ባካፈሉት ምክራቸው የቤተክርስቲያን ታማኝ ባለ አደራዎች፣ የክርስቶስን ምስጢራት ወደ ሌሎች የሚያዳርሱ፣ መንጋቸውን በሚገባ የሚያውቁ እና እነሱም የሚያውቋቸው፣ ለመንጋቸው ሕይወታቸውን እንኳ አሳልፈው ለመስጠት ወደ ኋላ የማይሉ፣ የመልካም እረኛ ምሳሌ እንዲሆኑ ጠይቀዋቸዋል።

ለጥቃት የተጋለጡትን ውደዱ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በማከልም ጳጳሳት ከእግዚአብሔር ዘንድ አደራ የተጣለባቸውን በሙሉ እንዲወዱ አሳስበው በተለይም አገልጋይ ካህናቶቻቸውን፣ ዲያቆኖቻቸውን፣ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ድሆችን እና ተከላካይ የሌላቸውን በሙሉ ፍቅርን እና ቸርነትን እንዲያሳዩ አደራ ብለዋል።

መንጋዎቻችሁን ጠብቁ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ብጹዓን ጳጳሳቱ አምሳልነቱን በምትገልጹት በእግዚአብሔር አብ ስም፣ ካህን እና እረኛ ባደረጋችሁ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ ለቤተክርስቲያኑ ሕይወትን እና ብርታትን በሚሰጥ በመንፈስ ቅዱስ ስም ምዕመናኖቻቸውን እንዲወዱ እና እንዲጠብቁ አደራ ብለዋል።           

05 October 2019, 17:07