ፈልግ

በባሕር ላይ ከባድ ክብደት ያላቸውን ሸቀጦች የማጓጓዝ ተግባር፣ በባሕር ላይ ከባድ ክብደት ያላቸውን ሸቀጦች የማጓጓዝ ተግባር፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለዓለም አቀፉ ክርስቲያናዊ የባሕር ላይ ሠራተኞች ማህበር መልዕክት አስተላለፉ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በታይዋን፣ ካዎሲዩንግ ከተማ ከጥቅምት 10-14/2012 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ በሚገኝ ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ሠራተኞች ክርስቲያናዊ ማሕበር ስብሰባ ተካፋዮች ሰላምን እና መልካምን የተመኙላቸውን መልዕክት መላካቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። 11ኛውን ዓለም አቀፍ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ለሚገኙ የማሕበሩ አባላት በላኩት መልዕክታቸው፣ ማሕበሩ የተመሠረተበትን 15ኛ ዓመት አስታውሰው፣ ማሕበሩ ለመርከበኞች፣ ለባሕር ላይ ተጓዦች እና በባሕር ላይ የተለያዩ አገልግሎቶች በማበርከት ላይ ለሚገኙት የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበው ለክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፣ የማሕበሩ አባላት አሁን በማካሄድ ላይ በሚገኙት ዓለም አቀፍ ጉባኤ መካከል በሚነሱት ገንቢ ሃሳቦች አማካይነት ለባሕር ላይ ተጓዦች፣ ለዓሣ አጥማጆች እና ለቤተሰቦቻቸው በሙሉ የሚበጀውን እገዛ ለማድረግ የሚያግዙ መንገዶችን ለይተው እንደሚያውቁ ያላቸውን እርግጠኝነት ገልጸዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው በ1989 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ስቴላ ማሪስ” በማለት የጻፉትን ሐዋርያዊ መልዕክ አስታውሰው፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል የባሕር ላይ ተጓዦች እና ሠራተኞች፣ ዓሣ አጥማጆች እና ቤተሰቦቻቸው የቅድስና ሕይወትን መኖር እንዲችሉ የሚያግዟቸውን  ሐዋርያዊ አገልግሎት አቅርቦትን አስመልክተው መሰረታዊ ደንቦችን ማስቀመጣቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጉባኤው ላይ ለተገኙት እና የተለያዩ ክርስቲያናዊ ባሕሎችን ለሚከተሉ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በላኩት መልዕክታቸው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ለባሕር ላይ ተጓዦች፣ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው የላኩትን ሐዋርያዊ መልዕክት በማደስ፣ መርከበኞች፣ የባሕር ላይ ሰራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቁ እና በትምህርቶቹ መሠረት እርስ በእርስ በመከባበር እና በመቻቻል በጋራ እንዲኖሩ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተልዕኮዋቸው መካከል የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በአሸናፊነት እንዲወጡ፣ ክርስቲያናዊ አንድነታቸውንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ የሚችሉበትን ጸጋ ተመኝተውላቸው፣ በታይዋን፣ ካዎሲዩንግ ከተማ ከጥቅምት 10-14/2012 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ሠራተኞች ክርስቲያናዊ ማሕበር ስብሰባ ተካፋዮችን በጸሎታቸው የሚያስታውሱ መሆናቸውን ገልጸው፣ ጉባኤያቸው መልካም ፍሬ የሚገኝበት እንዲሆን፣ በዚህ አጋጣሚ ለባሕር ላይ ሠራተኞች ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ የሚገኙትንም በማሰብ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ልከውላቸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
22 October 2019, 16:45