ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለወንጌል አገልግሎት ዘልቆ መሄድ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ.ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ አብሮአቸው በመሆን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎትን ለማቅረብ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች፣ በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀደም ብሎ ጠዋት በተደረገው የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ ከመስከረም 25 - ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መጠናቀቁን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዕለቱ በቀረበው የመጀመሪያ ንባብ፣ ከመጽሐፈ ሲራቅ ምዕ. 35:15-17 ፣ 20-22 ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉዞ መነሻን የስታውሰናል ብለው በመጽሕፉ ላይ እንደተገለጸው “ወደ ደመና ላይ በሚደርሰው የድሃው ጸሎት” አማካይነት “እግዚአብሔር የተበደለውን ሰው ጸሎት ይሰማል” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በአስተንትኖአቸው እንዳስረዱት፣ የድሆች ጩሄት ከምድሪቱ ጩሄት ጋር በመዳመር ከአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች በኩል ይሰማል ብለዋል። ለሦስት ሳምንታት ሲደመጥ ከቆየው የአማዞን አካባቢ አገሮች ሕዝቦች የስቃይ ድምጽ በኋላ ምንም እንዳልሰማ መሆን አንችልም ብለው በብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ላይ ከሐዋርያዊ አባቶች፣ ከወጣቶች እና  ከምሁራን ዘንድ የሚወጡ መልዕክቶችን ካዳመጡ በኋላ አስፈላጊውን እርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ ማለት የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እርምጃውም ለስነ ምሕዳር እና ለሰው ልጅ በሙሉ የሚገባውን ክብር እና እንክብካቤ መስጠት እንደሆነ ገልጸው በጊዜ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ ሲኖዶስን ትርጉም ያስረዱ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን አባቶች ከእግዚአብሔር በሚሰጣቸው ሃይል በመታገዝ እና ድፍረትን በማግኘት አንድ ላይ ሆነው የሚያደረጉት የሕብረት ጉዞ ነው ብለዋል። ከመስከረም 25 - ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ የተካሄደውን የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ግልጽነት በተሞላበት አካሄድ፣ በሕብረት የመጓዝን እና የማገልገልን መልካምነትን እየተመለከትን፣ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሄዎችን በጋራ የመፈለግ አጋጣሚ የነበረበት እንደነበር ተናግረዋል። በእለቱ በቀረበው ሁለተኛ ንባብ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው ሁለተኛ መልዕክቱ በምዕ. 4፡6-8 እና 16-18 ላይ ተወስዶ በቀረበው ንባብ ላይ “ለመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል” በማለት የተናገረውን አስታውሰው፣ በቁ. 17 ላይም “ዳሩ ግን የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም አሕዛብም ሁሉ እንዲሰሙት፥ ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ” ያለውን አስታውሰዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ጢሞቴዎስ በላከው ሁለተኛ መልዕክቱ የተናገረው የአገልግሎት ሂደት ራሱን ወይም ወገኖቹን ለመጥቀም ሳይሆን ለቅዱስ ወንጌል ክብር መሆኑን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

በቫቲካን ሲካሄድ የሰነበተውን የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቅዱስ ወንጌልን በስፋት ለማዳረስ በሚያግዙ ተጨማሪ የአገልግሎት መንገዶች ላይ መወያየቱን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ወንጌልን ለዓለም መመስከር ያለብን በሕይወት ምስክርነት መሆን አለበት ብለው ይህን ማድረግ የምንችለው የምቾት ሕይወት ምርጫን በመተው መንፈስ ቅዱስ በሚያሳየን መንገድ በመጓዝ የወንጌል አገልግሎትን ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።        

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያቀረቡትን አስተንትኖ ሲያጠቃልሉ የአማዞን አካባቢ አገሮች እናት ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበው፣ በእናትነት ፍቅሯ ልጆቿን እና ምድራችንን ከሚደርስባቸው አደጋ እና ከስቃይ እንድትታደጋቸው በማለት የእርሷን እገዛ ተማጽነዋል።  

28 October 2019, 18:40