ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሲኖዶሱ የመዝጊያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሲኖዶሱ የመዝጊያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመዝጊያ ንግግር አደረጉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 25 - ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. የተካሄደው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መዚጊያ ላይ ለተገኝተ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ንግግር ማድረጋቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ  ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጉባኤው ወቅት ለታየው መደማመጥ፣ ለተከናወኑ በርካታ ሥራዎች እና ገንቢ ውይይቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ሕዝቦች እና ስነ ምሕዳርን መንከባከብ በተመለከተ የቀረበው ርዕሠ ጉዳይ ሰፊ እና በአንድ ጊዜ የሚከናወን አለመሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ ወደ መልካም ደረጃ ላይ መድረሱን እና ውይይቱ ቀጣይነት ያለው መሆኑን አስታውሰዋል። በሕብረት እየተጓዙ የጋራ ውይይቶችን ማድረግ፣ መደማመጥ እና በጥበብ በማስተዋል የቤተክርስቲያንን ውድ የሆኑ ባሕሎችን ለመጋራት ይጠቅማል ብለዋል። ባሕል መጪው ጊዜን ያማረ ለማድረግ የሚጠቅሙ አንዳንድ ጠቃሚ ሃሳቦች የሚገኝበት እንደሆነ ያስረዱት ቅዱስነታቸው እነዚህን የቀድሞ አባቶች ሃሳቦችን እና ምክሮችን ተቀብሎ በሥራ ፍሬያማ መሆን የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሲኖዶሱ አባቶች ሰፊ ውይይቶችን ያደረጉባቸው ሦስት ርዕሠ ጉዳዮችን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጀመሪያው ወደ ፊት ሊዋቀር የታሰበው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሲሆን ይህን በተመለከተ የደረሱበት ውሳኔ አለመኖሩን አስረድተው አሁን ሥራውን ብማከናወን ላይ ያለው የአማዞን አካባቢ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በርካታ ሥራዎችን እንዳካሄደ እና በማካሄድም ላይ እንደሚገኝ አስታውሰው፣ ሲኖዶሱ እስካሁን ላከናወኗቸው መልካም ተግባራት በሙሉ ብጹዓን ጳጳሳቱን አመስግነዋቸዋል።

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶድስ በጉባኤው ማግስት ያወጣውን ሰነድ በጽሞና መመልከት ቀላል እና መልካም ይሆናል ያሉት ቅዱስነታቸው ብጹዓን ጳጳሳቱ የጉባኤውን የመጨረሻ ሰነድ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ. ም. ድረስ በጥንቃቄ እዲመለከቱት ጠይቀው እርሳቸውም በበኩላቸው ሰነዱን ለመመልከት ጊዜ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ጉባኤውን ከመስከረም 25 - ጥቅምት 16/2012 ዓ. ም. ያካሄደው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በቆይታው በአራት ቀዳሚ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጉን የገለጹት ቅዱስነታቸው የመጀመሪያው ባሕል የተመለከተ ሲሆን በዚህም መሠረት ለአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ሕዝቦች ባሕል ከፍተኛ እውቅናን በመስጠት እስካሁን የአካባቢውን አገሮች ሕዝቦች ለማቀራረብ የተወሰዱ እርምጃዎች ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለተኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመወያያ ርዕሥ ሥነ ምህዳርን የተመለከተ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ስነ ምሕዳርን በማስመልከት ገንቢ ሃሳባቸውን ላካፈሉት የቁንስጥንጢንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊን ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።  ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርቶሎሜዎስ ቀዳማዊን ሥነ ምህዳርን አስመልክተው ገንቢ ሃሳባቸውን ካቀረቡት መካከል የመጀመሪያው መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ስነ ምሕዳርን በማስመልከት በፓሪስ ከተማ ከተደረገው ጉባኤ በተጨማር በሌሎች  ውይይቶች በመገኘት ሃሳባቸውን ያካፈሉ መኖራቸውን ገልጸው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክታቸውም የርካታ የስነ ምሕዳር፣ የሰነ መለኮት እና የሐዋርያዊ አባቶች አስተያየት ውጤት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተው በእነዚህ ጉባኤዎች መካከል የተነሱት አስተያየቶችም በአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ሕዝቦች እና በምድራቸው ላይ የሚደርሰው ውድመት መከላከል ጊዜ የማይሰጠው ቀዳሚ ጉዳይ ሆኖ መቅረቡን አስረድተዋል። ስነ ምሕዳርን አስመልክተው ከተደርጉት የአካባቢ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥ እና የመብት ተሟጋች ስዊድናዊቷ ታዳጊ፣ ግሬታ ተንበርግን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ወጣቶች “መጭው ጊዜ የእኛ ነው” የሚል መፈክር ይዘው በመውጣት ድምጻቸውን ማሰማታቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። በስነ ምሕዳር ላይ የደረሰው ቀውስ በአማዞን ደናማው አካባቢ አገሮች ብቻ እንዳለሆን ሌሎች የዓለማችን አካባቢዎችም ተገንዝበዋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮንጎ ሕዝባዊ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ እና የትውልድ አገራቸው አርጀቲናም በስነ ምሕዳር ላይ አደጋ ከደረሰባቸው አገሮቹ መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ሦስተኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመወያያ ርዕሥ ማሕበረሰብን የተመለከተ መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለጥፋት፣ ለብዝበዛ እና ለአደጋ የተጋለጠው የጋራ መኖሪያ ምድራችን ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ላይ፣ በሕዝቦች ማንነት እና ባሕል ላይም አደጋ መድረሱን አስታውሰዋል። ስነ ምሕዳርን ጨምሮ በሰዎች ላይም የፈጸሙ በደሎችን መዋጋት እንደሚያስፈልግ  የሚያሳስቡ መልዕክቶች በየአውሮፕላን ጣቢያዎችም ሳይቀር ለሃገር ጎብኚዎች እንደሚቀርብ የገለጹት ቅዱስነታቸው በበርካታ አገሮች በብልሹ የመንግሥት አስተዳድ ሙስና መበራከቱ ሰዎችን ለስቃይ እንደዳረጋቸው የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት በመጨረሻ ሰነዳቸው በሚገባ ማካተታቸውን አስታውሰዋል።

አራተኛው እና ሌሎች ርዕሦችን አንድ ላይ አድርጎ የሚይዝ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመወያያ ርዕሠ ጉዳይ ለአማዞን አካባቢ አገሮች ምዕመናን የሚቀርብ ሐዋርያዊ አገልግሎት እንደሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የወንጌልን መልካም ዜና ማዳረስ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። የወንጌል አገልግሎት የአካባቢውን ሕዝብ ባሕል ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል በማለት ንግግራቸውን ያሰሙት ቅዱስነታቸው ለምዕመናን የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በተመለከተ ሕዝበ ምዕመናንን፣ ካህናትን፣ ቋሚ ዲያቆናትን፣ ገዳማዊያን ኣና ገዳማዊያትን አስመልክቶ የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በስፋት የተወያየበት መሆኑን አስታውሰው በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከምዕመናን መካከል የተወጣጡ እና በአዳዲስ የአገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት አገልግሎት ማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ የሚገልጽ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ሰነድን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ምእመናን እነዚህን አገልግሎቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ በምን መልኩ ማከናወን እንደሚችሉ ውይይቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል። ከማዞን ደናማው አካባቢ ቀደምት ሕዝቦች መካከል ሐዋርያዊ አገልግሎትን ማበርከት የሚችሉ ምዕመናንን ማዘጋጀት አስመልክቶ ሰፊ ውይይት መደረጉን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ለአማዞን ደናማው አካባቢ ሕዝቦች ማሕበራዊ ፍትሕን ለማስገኘት እና ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን የሚያዳሱ የምዕመናን ወገንን ለማዘጋጀት የሚያግዙ መንገዶችን በማሳየት ለሲኖዶሱ አባቶች ገንቢ ሃሳባቸውን  ያካፈሉትን ብጹዕ ካርዲናል ኦ ማሊን ቅዱስነታቸው አመስግነዋል።

ጥንታዊው የክርስቲያን ባሕልን በመከተል በቋሚ የድቁና ማዕረግ ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ ምዕመናንን ማዘጋጀት አስመልክቶ በሲኖዶሱ አባቶች ውይይት መደረጉን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ይህን የቤተክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፍ በአካባቢው አገሮች ለመጀመር የሚያስችል ጥናት እንዲድረግ ለደናግል ማሕበራቱ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸው ጥያቄው የደረሳቸው ከአማዞን አካባቢ አገሮች የደናግል ማሕበራት ሕብረት መሆኑን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ይህን የቤተክርስቲያን አገልግሎት በአማዞን አካባቢ አገሮች ዘንድ ለማስተዋወቅ የሚቻልበትን መንገድ በቅድስት መንበር እምነተ አንቀጽን ከሚመለከት ጳጳሳዊ ምክር ቤት ጋር የሚወያዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያን በማደግ ላይ እንደምትገኝ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚታየውን የካህናት እጥረት ማቃለል የቤተክርስቲያን ሃላፊነት ነው ብለው የካህናት እጥረት በአማዞን አካባቢ አገሮች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የዓለማችን ክፍሎች የሚታይ ችግር በመሆኑ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በሐዋርያዊ አስተዳደሮቻቸው ውስጥ የሚታይ የካህናት እጥረት ካለ በመረዳት ምላሽ የመስጠት ሃላፊነት አለበት ብለዋል። ሐዋርያዊ አገልጎሎትን ለማበርከት በወጣት ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት መካከል ከፍተኛ ተነሳሽነት መኖሩ በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የተገለጸ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰው የወጣቶችን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማሳደግ በቂ እገዛ እና ስለጠና ሊሰጥ ይገባል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በቅድስት መንበር እንደራሴዎችን ውስጥ የአንድ ዓመት አገልግሎታቸውን የሚያበረክቱ ወጣት ካህናት በዲፕሎማስያዊ አገልግሎት ብቻ ሳይገደቡ ከሚኖሩበት አካባቢ ወጥተው ወደ ቁምስናዎች በመሄድ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎታቸውን ማበርከት ጠቃሚ መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተው ይህ ዕቅድም ጥናት የሚያስፈልገው መሆኑን ተናግረዋል። በወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት የተሰማሩ በርካታ ካህናት በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮጳ አገሮች የሚገኙ መሆናቸውን ቅዱስነታቸው ተናግረው ከዚህ በተቃራኒው በአማዞን አካባቢ አገሮች የካህናት እጥረት መታየቱን አስታውሰዋል። ለትምህርት በሄዱበት አገር የክህነት አገልግሎታቸውን እያበረክቱ የሚቀሩ ካህናት መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እነዚህን ካህናት ለአገልግሎታቸው አመስግነው ነገር ግን የክህነት አገልግሎታቸውን በሕጋዊ መንገድ የሚያበርክቱ ካህናትን የመመደብ ስርዓት ቤተክርስቲያን “ፊዴይ ዶኑም” በተባለ የቤተክርስቲያን ተቋም ያላት መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ የቤተክርስቲያን ተቋም በኩል የተላኩ በርካታ የአፍሪቃ እና የላቲን አሜሪካ ካህናት በአውሮጳ ተሰማርተው አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የአገልጋይ ካህናትን ምድብን በጥንቃቄ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረደዋል።

ሴቶችን በሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማሰማራትን የተመለከተ ሃስብ በሰነዱ ላይ የተጠቀሰ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሴቶች እምነትን በመመስከር እና ባሕልን በማቆየት ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፣ ሴቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ሊያቀርቡ የሚችሉት የአገልግሎት ዘርፎች ምን ምን እንደሆኑ ማሰቡ ጥሩ ቢሆንም ከዚህ በበለጠ ሁኔታ በምዕመናን ምክር ቤት ውስጥ አባል በመሆን ድምጿን ማሰማት እድል ሊሰጣት ይገባል ብለዋ ሴቶች ሊሰማሩ በሚችሉባቸው የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ሰፊ ጥናት የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳስት ሲኖዶድ ሰነድ ውስጥ ከተጠቀሱት ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ከብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ጋር ተባብረው የሚሰሩ መለስተኛ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎችን ማቋቋም ያስታወሱ ሲሆን ይህ መንገድ በኢጣሊያ ውስጥ በሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በተግባር የተገለጸ እና አገልግሎትን በማበርከት ላይ የሚገኝ የአገልግሎት መንገድ እንደሆነ አስረድተው በአማዞን አካባቢ አገሮችም ተቋቁመው አገልግሎታቸውን በሚገባ የሚያቀርቡ ከሆኑ ውጤታማ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በጠቅላላ ሰነዱ ውስጥ ስርዓተ አምልኮን የሚመለከት ርዕሠ ጉዳይን ያካተተ መሆኑን የገለጹት ቅዱስነታቸው በአካባቢው አገሮች ውስጥ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በተገባር ሲገለጽ የቆየ የአምልኮ ስርዓት መኖሩን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በአካባቢው አገሮች በሚገኙ፣ ቁጥራቸው 23 ከሚሆኑ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የራሳቸውን ስርዓተ አምልኮ ሂደትን ሲለማመዱ የቆዩ የራሳቸው ሐዋርያዊ አስተዳደር ያላቸው ወደ 19 የሚጠጉ አብያተ ክርስቲያናት መኖራቸውን ገልጸው እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት እምነታቸውን እስከ ፍጻሜ የሚያደርሱትን ሃይል እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው በማለት ብርታትን ተመኝተውላቸዋል። አክለውም የራሳቸውን የእምነት መንገዶችን የሚከተሉ የሐይማኖት ተቋማትን መፍራት እንደማያስፈልግ አስረድተው ምዕመናንን ዘወትር የምትረዳን የሁላችን እናት ቅድስት ቤተክርስቲያ ከጎናችን በመሆን ትመራናለች ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው መጨረሻ በአማዞን አካባቢ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የተካፈሉትን ብጹዓን ካርዲናሎችን፣ ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያትን፣ የስነ ምሕዳር ጠበብትን፣ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡ የስነ መለኮት ጠበብትን፣ ምዕመናንን እና በጉባኤው ላይ በቀረቡ አራቱ ቀዳሚ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ያበረከቱትን በሙሉ አመስግነው፣ በአማዞን አካባቢ አገሮች ላይ የደረሰውን እና በመድረስ ያለውን የስነ ምሕዳርን፣ የባሕሎችን እና የሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ቀውስ ለማስወገድ የተጀመረው ወይይት በዚህ የሚያበቃ አለመሆኑን አስረድተው፣ ለእግዚአብሔር እና ለፍጥረታቱ የሚገባውን ፍቅር መስጠት እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው በመጠየቅ ንግግራቸውን ደምድመዋል።   

28 October 2019, 19:36