ር.ሊ.ጳ ፍራችስኮስ “እግዚአብሔርን ማመስገን ልባችን ወጣት ሆኖ እንዲኖር ያደርገዋል” አሉ።
በሕይወት ዘመናቸው መልካሙን ግድል በመታገል በእግዚኣብሒር ኃይል እና በራሳቸው ከፍተኛ ጥረት የእዚህን ዓለምን ፈተና ድል ለመንሳት ከፍተኛ መንፈሳዊ ተጋድሎ አድርገው ላለፉ አምስት ሰዎች በጥቅምት 02/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከ50ሺህ በላይ ምዕመናን በተገኙበት የቅድስና ማዕረግ እንደ ተሰጣቸው ቀድም ሲል ባስተላለፍነው ዘገባ መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ይህንን የቅድስና ማዕረግ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሰጡበት ወቅት ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙት ስብከት በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 17፡11-19 ላይ ተወስዶ በተነበበው እና “እምነትህ አድኖሃል” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ንባብ ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “እግዚአብሔርን ማመስገን ልባችን ወጣት ሆኖ እንዲኖር ያደርገዋል” ማለታቸ ተገልጹዋል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድተከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
“እምነትህ አድኖሃል” (ሉቃስ 17፡19)። ይህ የእምነትን ጉዞ የሚያንፀባርቅ የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ማጠናቀቂያ ሐረግ ነው። በዚህ የእምነት ጉዞ ውስጥ ሦስት ደረጃዎች አሉ። በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዙትን ሰዎች ኢየሱስ ሲፈውሳቸው የሚያሳዩ እርምጃዎችን እንመለከታለን። እነርሱም ይጮኻሉ ፣ ይራመዳሉ ከእዚያም ያመሰግናሉ።
በቅድሚያ ይጮኻሉ። የሥጋ ደዌ የተያዙ በሽተኞቹ እጅግ አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ ፣ በዛሬው ጊዜም ቢሆን በስፋት እንደ ሚታየው እነዚህ ሰዎች ከያዛቸው የስጋ ደዌ በሽታ ጋር ከሚያደርጉት ትግል ባሻገር ከሕብረተሰቡ በመገለላቸው እና በመባረራቸው ጭምር በከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብተው ይገኛሉ። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ የሥጋ ደዌ በሽተኞች እንደ ርኩስ ይቆጠሩ ነበር ፣ በእዚህም የተነሳ ከሌሎች ሰዎች የተገለሉ እና ተጠልተው እንዲኖሩ ይገደዱ ነበር። ወደ ኢየሱስ በቀረቡበት ወቅት ከእርሱ ጋር የነበራቸውን ርቀት ጠብቀው መቆማቸውን እንመለከታለም (ሉቃስ 17፡12)። ምንም እንኳን ያጋጠማቸው ሁኔታ ለየት የሚያደርጋቸው ቢሆንም በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው “በታላቅ ድምጽ ጮኼው” ኢየሱስ እንዲፈውሳቸው እንደ ተማጸኑት (ሉቃስ 17፡13) ይነግረናል። በሕብረተሰቡ መጠላታቸው እና መገለላቸው ደንዝዘው እንዲቀሩ አላደረጋቸውም ነበር፣ በመሆኑም ማንንም ወደ ማያገለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። እነርሱ የነበሩበት ርቀት እንዴት እንዳጠረ፣ ብቸኝነታቸው እንዴት እንደተሸነፈ እንገነዘባለን - በራሳችን እና በራሳችን ችግሮች ተቆልፈን፣ ሌሎች በእኛ ላይ እንዴት እንደ ሚፈርዱብን በማሰብ መቆየት ሳይሆን የሚጠበቅብን፣ ነገር ግን ጌታ የእንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎችን ጩኸት ሰለሚሰማ በብቸኝነት መንፈስ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ መጮኽ ይጠበቅባቸዋል፣ ጌታም ለቅሶዋቸውን ይሰማል።
እንደ እነዚህ የሥጋ ደዌ በሽተኞች እኛም እያንዳንዳችን ፈውስ ያስፈልገናል። በራሳችን፣ በሕይወታችን ውስጥ ያለውን በራስ የመተማመን መንፈስ መፈወስ ይኖርበታል፣ ከፍርሃቶቻችን እና ተብትበው ከያዙን ፈተናዎቻችን መፈወስ ይኖርብናል፣ ከሱሶቻችን፣ ከገንዘብ ፣ ከቴሌቪዥን ፣ ከሞባይል ስልኮች ፣ እና መጥፎ ድርጊቶች መፈወስ አለብን። ጌታ ልባችንን ነፃ ያወጣል ይህንንም የሚያደርገው እና የሚፈውሰው እኛ ከጠየቅነው ብቻ ነው የሚፈውሰን፣ “ጌታ ሆይ ፣ ልትፈውሰኝ እንደምትችል አምናለሁ፣ ውድ ኢየሱስ ሆይ ፣ በእራሴ እንዳልያዝ ፈውሰኝ፣ ከክፉ ነገሮች እና ከፍርሀት አድነኝ ” ብለን ልንማጸነው የገባል። ከክፉ ነገሮች እና ከፍርሀት አድነኝ”። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢየሱስን ስም የጠሩት ሰዎች የሥጋ ደዌ በሽተኞች ናቸው። ከእዚያም በመቀጠል አንድ ዓይነ ስውር የነበረ ሰው እና በመስረቁ የተነሳ የተሰቀለው ሰው ይገኝበታል፣ የተቸገሩ ሰዎች ሁሉ የኢየሱስን ስም ይጠራሉ፣ ምክንያቱም “እግዚኣብሔር እንደ ሚያድን” ስለሚያምኑ ነው። በቀጥታ እና በስሙ እግዚአብሔርን ይጠራሉ። አንድን ሰው በስም መጥራት በራስ በሰውየው መተማመናችንን የሚያሳይ ምልክት ነው፣ በስሙ ስንጠራው ጌታን ያስደስተዋል። በእዚህም ሁኔታ እና ዓይነት በመተማመን እና በጸሎት እምነት የሚያድገው። ሥቃያችንን ለመሸፈን ሳንሞክር በተከፈተ ልብ ወደ እግዚኣብሔር እና ወደ ኢየሱስ የሚቀርብ ጸሎት ፍሬያማ ጸሎት ነው። በየቀኑ “እግዚአብሔር ያድናል” የሚለውን የኢየሱስን ስም በመጥራት በልበ ሙሉነት እንጠይቅ። ደግመን እንበለው፣ ኢየሱስ ማለት በራሱ “ጸሎት” ማለት ነው፣ እናም ጸሎት አስፈላጊ ነው! በእርግጥም ጸሎት የእምነት በር ነው ፡፡ ጸሎት ለልብ መድኃኒት ነው።
ሁለተኛው ቃል መራመድ የሚለው ነው። ይህም ሁለተኛው ደረጃ ነው። በዛሬው አጭር የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ ብዙ እንቅስቃሴዎችን የሚያመለክቱ ግሶች አሉ። በጣም የሚያስደንቀው የሥጋ ደዌ በሽተኞቹ በኢየሱስ ፊት ሲቆሙ አለመፈወሳቸው ነው፣ ፈውስ የመጣው እነርሱ መራመድ ከጀመሩ በኋላ ነው፣ ቅዱስ ወንጌሉ የሚለን “እነርሱም ወደዚያው በመሄድ ላይ ሳሉ ነጹ” (ሉቃስ 17፡14) በማለት ቅዱስ ወንጌል የሚነግረን። ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ በጀመሩበት ወቅት ማለትም ወደ ተራራው ላይ በመውጣት ላይ በነበሩበት ወቅት ነበር የተፈወሱት። በሕይወት ጎዳና ላይ መንፃት የሚከናወነው በእዚያው ጎዳና ላይ ስንጓዝ ብቻ ነው፣ ወደ ላይ የሚወደን መመገድ ሁሉ ወደ ንጽህና የሚወስደን የከፍታ መንገድ ነው። እምነት ከእራሳችን “የመውጣት” ጉዞን ይጠይቃል፣ እናም ደህንነቶቻችንን እና ምቹ ጎጆዎቻችንን ትተን የምንሄድ ከሆነ በሕይወታችን ተዐምር እንደ ሚፈጸም እርግጠኞች ለመሆን እንችላለን። እምነት የሚጨምረው በመስጠት ነው፣ የሚያድገው ደግሞ አደገኛ ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ ስንጥር ነው። በአስተማማኝ ሁኔታ በእግዚአብሔር ላይ በመታመን መንገዳችንን ስናከናውን እምነት ያድጋል። እንደ የለምጽ በሽታ እንደ ነበራቸው ሰዎች ወይም በዮርዳኖስ ወንዝ ለመታጠብ እንደ ወረዱት ሰዎች እምነት በትህትና እና ተግባራዊ በሆነ መልኩ በምንወስዳቸው እርምጃዎች ይሻሻላል (2 ነገሥት 5: 14-17) ፡፡ ለእኛም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ትሕትናን እና ተግባራዊ ፍቅርን በማሳየታችን፣ በየእለቱ ትዕግሥት በማሳየት ጉዞአችንን ወደ ፊት በምናደርግበት ጊዜ በእምነት ወደ ፊት እንፀናለን።
የሥጋ ደዌ በሽተኞችን ጉዞ በተመለከተ ሌላ አስደሳች ገጽታ አለ፤ አብረው ይራመዳሉ። ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚናግረው እነርሱ “ሲሄዱ ፣ ይነጻሉ” (ሉቃስ 17፡14) ይለናል። ግሱ የተገለጸ በብዙ ቁጥር ነው። እምነት ማለት አብሮ መጓዝ ማለት ነው። እነዚህ የለምጽ በሽታ የነበራቸው ሰዎች ከበሽታቸው ከተፈወሱ በኋላ ግን ዘጠኙም በእየራሳቸው መንገድ ነበር ወደ መጡበት የተመለሱት፣ አንዱ ብቻ ምስጋና ለማቅረብ ወደ ኋላ ይመለሳል። ከዚያም ኢየሱስ በእርሱ መደነቁን ገልጻል። “ሌሎቹ ዘጠኙ ወደ የት ሄዱ?” (ሉቃስ 17፡ 17) በማለት ይጠይቀዋል። እሱ ለሌላው ዘጠኝ ወክሎ የመጣ ይመስል ነበር። መንገዳቸውን ያቆሙትን ፣ መንገዳቸውን የሳቱትን ለመንከባከብ እና ለማሰብ ነው የምስጋና መስዋዕት የሆነውን ቅዱስ ቁርባንን የምንታደመው። እኛ ከመንገድ የወጡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችን ጠባቂ እንድንሆን ተጠርተናል! ለእነሱ ምልጃ ማቅረብ አለብን። ለእነሱ ተጠያቂዎች ነን። በእምነት ማደግ ይፈልጋሉ? እናንተ ዛሬ እዚህ የምትገኙ ሰዎች ሁላችሁ በእመንት ማደግ ትፈላጋላችሁን? እንግዲያውስ ከመንገድ የወጡትን ሰዎች፣ ከመንገድ የራቁትን ሰዎችን ተንከባከቡ።
መጮህ፣ መራመድ እና ማመስገን። የመጨረሻው እርምጃ ይህ ነው ፡፡ ኢየሱስ “እምነትህ አድኖሃል” ያለው ላመሰገነው ሰው ብቻ ነው (ሉቃስ 17፡19)። ደህና እና ጤናማ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህ የምንረዳው ደግሞ ዋነኛው ግብ ጤና ወይም ደኅንነት ሳይሆን ነገር ግን ከኢየሱስ ጋር መገናኘቱ ነው። ድህንነትን ማግኘት ማለት ምንጭ ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ መቅረብ ማለት ነው። ከክፉ ነገሮች ነፃ የሚያደርገንና ልባችንን የሚፈውስ እርሱ ብቻ ነው። ከእሱ ጋር የሚደረግ ግንኙነት ብቻ ነው የሚያድነን፣ ሕይወት ሙሉ እና የሚያምር ሊያደርገው የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው። ኢየሱስን በምንገናኝበት ጊዜ “ምስጋና” የሚለው ቃል ወዲያው ወደ አፋችን ይመጣል ፣ ምክንያቱም በህይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ነገር አግኝተናልና ፣ ይህም ጸጋን ለመቀበል ወይም ችግርን ለመፍታት ሳይሆን የሕይወትን ጌታን ለመቀበል ነው።፡ እናም በህይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊው ነገር ይህ ነው-የሕይወትን ጌታ መቀበል።
ከለምጽ የነጻው ሳምራዊው ሰው በጠቅላላው ፍፁም ደስታውን ሲገልፅ ማየት አስደናቂ ነው- በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ያመሰግናዋል ፣ ሰገደ ፣ በአጠቃላይ ከፍተኝ የሆነ ምስጋን ያቀርባል። የእምነት ጉዞ መኖር ማለት የምስጋና ሕይወት መኖር ማለት ነው። እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ-እንደ እምነት ተከታዮች እምነት በየቀኑ እንደ ሸክም ሆኖብን ነው የምንኖረው ወይስ በምስጋና እና በውዳሴ ነው? ሌላ በረከትን ለመጠየቅ በመጠባበቅ ላይ ሆነን እራሳችንን ዘግተናል፣ ወይስ ምስጋና በመስጠት ደስታችንን እናገኛለን? አመስጋኝነታችንን በምንገልጽበት ጊዜ ፣ የአብ ልብ ይነካል እናም መንፈስ ቅዱስን በእኛ ላይ ያፈሳል። ምስጋና ማቅረብ የመልካም ምግባር ወይም የስነ-ምግባር ጥያቄ አይደለም ፣ ይህ የእምነት ጥያቄ ነው። አመስጋኝ ልብ ሁሌም ወጣት የሆነ ልብ ሆኖ ይዘልቃል። ቀኑን ሙሉ ከእንቅልፋችን ስንነሳ እና ከመተኛታችን በፊት “ጌታ ሆይ አመሰግናለሁ” ማለት - ልባችን ወጣት ሆኖ እንዲቆይ ያደርገዋል። ምክንያቱም ምስጋና ማቅረብ ስናቆም ልባችን ያረጃል።