ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ዋና ተዋናይ ነው” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 19/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 19/2012 ዓ.ም ባደረጉት የክፍል ዐስራ ዐራት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው  “ጳውሎስም ሌሊት በራእይ አንድ የመቄዶንያ ሰው ቆሞ፣ “ወደ መቄዶንያ ተሻግረህ ርዳን” ብሎ ሲለምነው አየ። ጳውሎስ ይህን ራእይ ካየ በኋላ፣ እግዚአብሔር ወንጌልን እንድንሰብክላቸው ጠርቶናል ብለን በመወሰን ወዲያው ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ፈለግን” (ሐዋ 16፡9-10) በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን “በቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ዋና ተዋናይ ነው”  ማለታቸው ተገልጹዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥቅምት 19/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የሐዋርያትን ሥራ መጽሐፍ በምናነብበት ወቅት በቤተክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በከፍተኛ ደረጃ ተዋናይ መሆኑን እንመለከታለን፡ ወንጌላዊያን ሊከተሉት የሚገባውን መንገድ የሚያሳይ እና በእዚህ መንገድ ላይ የሚመራቸው እርሱ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ጢሮአዳ በደረሰ ጊዜ ያየው ራእይ ይህንን በግልፅ ያመለክታል። አንድ የመቄዶንያ ሰው “ወደ መቄዶንያ መጥተህ እርዳን” ሲል ለመነው (ሐዋ. 16፡ 9)። የሰሜን መቄዶንያ ሰዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውጅላቸው ጳውሎስ ወደ እነሩ አገር እንዲመጣ በመጥራታቸው ሊኮሩ ይገባል። እኔ መቄዶኒያን በጎበኘሁበት ወቅት ያ መልካም ሕዝብ ጳውሎስ የሰበከላቸውን እምነት በመያዝ ያደረገለኝን ሞቅ ያለ አቀባበል ያስታውሰኛል። ሐዋሪያው ወደኋላ አላለም ፣ እሱ የላከው እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን በማመን ወደ መቄዶንያ ሄዶ ወንጌልን ለመስበክ “የሮማውያን ቅኝ ግዛት” (ሐዋ. 16 12) ወደ ነበረቺው ፊልጵስዩስ ደረሰ። ጳውሎስ ለተወሰኑ ቀናት በእዚያ ቆየ። በእነዚህ በፊሊጲሲዮስ ውስጥ በቆየባቸው በርካታ ቀናት ውስጥ ተልዕኮውን የሚያመላክቱ ሦስት ዋና ዋና አስፈላጊ ክስተቶች ይፈጸማሉ።  ስብከተ ወንጌል ይደረጋል እናም ልድያ የምትባል አንዲት ሴት እና የቤተሰቧ መጠመቅ  2) ጳውሎስ እና ሲላስ በጥንቈላ ሥራዋ ለአሳዳሪዎችዋ ብዙ ገንዘብ ታስገኝላቸው የነበረችሁን ሴት ከመጥፎ መንፈስ ነጻ በማደረጋቸው የተነሳ መታሰራቸው 3) የእስር ቤቱ ጠባቂ እና ቤተሰቡ መለወጥ እና መጠመቅ። እነዚህን ሦስት ክፍሎች በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ እናያለን።

የወንጌሉ ኃይል በመጀመሪያ የተናገረው ለፊልጵስዩስ ሴቶች ሲሆን በተለይም ደግሞ  እግዚአብሔርን የምታመልክና ከትያጥሮን ከተማ የመጣች የቀይ ሐር ነጋዴ ለነበረችው ሴት ነበር። ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ፣ ልቧን የከፈተላት ሊዲያ የምትባል ሴት ነበረች። በእርግጥ ሊዲያ ክርስቶስን ተቀብላ ከቤተሰቧ ጋር ተጠመቀች፣ የክርስቶስ የሆኑትን ጳውሎስንና ሲላስን በቤቷ ተቀብላ አስተናግዳለች። እዚህ ላይ የክርስትና እምነት በአውሮፓ ውስጥ እንዴት እንደ ተሰበከ የሚመሰክር ሁኔታን እንመለከታለን፣ ይህ ባህል እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሎ እንደ ሚገኝ እንመለከታለን። በመቀዶኒያ በኩል እንደ ገባም እንመለከታለን።

በሊዲያ ቤት ውስጥ ከተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል በኋላ ጳውሎስ እና ሲላስ ጥንካሬ ወደ ሰጣቸው ወደ እስር ቤቱ ያመራሉ፣ ሊዲያ እና ቤተሰቧ በመለወጣቸው ካደረባቸው የመጽናናት ስሜት ወደ እስር ቤት ውደቀት ያመራሉ፣ “የጥንቆላ መንፈስ ያደረባት” እና በእዚህ የጥንቆላ ስራዋ “ለአሳዳሪዎቿ ብዙ ገቢ ታስገባ” የነበረቺውን ሴት በኢየሱስ ስም በመፈወሳቸው የተነሳ ወደ እስር ቤት ይጣላሉ። በእዚች ሴት አማካይነት አሳዳሪዎቿ በጣም ብዙ ገንዘብ ያገኙ ነበር፣ እርሷ ግን እንደ ባርያ ሆኖ በድህነት ታገለግላቸዋለች፣ እርሷ ባሪያ ሆና እነርሱ ሐብታሞች እንዲሆኑ አደረገች፣ የወደ ፊቱን ሁኔታ ትጠነቁላለለች፣ የሰዎችን እጅ ታነባለች፣ በእዚህም ምክንያት ሰዎች ገንዘብ ይከፍሉዋት ነበር። ዛሬም ቢሆን ውድ ወንድሞች እና እህቶች ፣ ለዚህ ዓይነት ነገር ክፍያ የሚከፍሉ ሰዎች አሉ። አስታውሳለሁ እኔ በነበርኩበት አገረ ስብከት ውስጥ ከ60 በላይ የሚሆኑ ጥንቆላ የሚደረግባቸው ጠረጴዛዎች የነበሩ ሲሆን ሰዎች ወደ እዚህ ስፍራ እየመጡ እጃቸውን እያሳዩ መጻይ እድል ፈንታቸው እየተነገራቸው በእዚህ የሚያሙኑ ሰዎች ነበሩ። ለእዚህም አገልግሎት ገንዘብ ይከፍላሉ። ይህ ሁኔታ  ደግሞ በቅዱስ ጳውሎስ ጊዜም ነበር። የእዚህች ሴት አሳዳሪዎች ጳውሎስን አውግዘው፣ ሐዋርያቱን ይዘው በሕዝቡ ፊት ለፍርድ አቀረቡዋቸው፣ ወደ ዳኛም ወሰዱዋቸው።

ግን ምን ሆነ? ጳውሎስ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት አንድ በጣም አስገራሚ የሆነ ሁኔታ ተከሰተ። አስፈሪ የሆነ ቦታ ውስጥ ነበሩ። ነገር ግን በሁኔታው ቅር ከመሰኘት ይልቅ ጳውሎስ እና ሲላስ  ለእግዚአብሔር ውዳሴ በማቅረብ መዘመር ይጀምራሉ፣ እናም ይህ ውዳሴ ነፃ የሚያወጣ ኃይል በመሆን ከእስር ያስለቅቃቸዋል (ሐዋ. 16፣25-26 ተመልከቱ)። በጴንጤቆስጤ በዓል ወቅት እንደ ተደረገው ፀሎት፣ በተመሳሳይ መልኩም በእስር ቤት ውስጥ የተደርገው ጸሎት ከፍተኛ የሆነ ተዐምር እንዲከሰት አደረገ።

የእስር ቤቱ ጠባቂ እስረኞቹ ወጥተው የተጠፉ ስለመሰለው ነፍሱን ለማጥፋት ተቃርቦ ነበር፣ ምክንያቱም በወቅቱ በነበረው ሕግ መሰረት አንድ የእስር ቤት ጠባቂ በተመደበበት እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ እስረኞች ካመለጡ በሞት እንደ ሚቀጣ የሚደነግግ ሕግ በመኖሩ የተነሳ ነው። ጳውሎስ ግን “ሁላችንም እዚህ አለን” በማለት ይጮኻል (ሐዋ. 16 27-28) ፡፡ ከዚያም የእስር ቤቱ ጠባቂ  “ለመዳን ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቀ (ቁ. 30)። መልሱ “በጌታ በኢየሱስ እመን አንተና ቤተሰቦችህ ትድናላችሁ” (ቁ. 31) የሚል ነበር። በዚህ ጊዜ ለውጡ ይከሰታል-በእኩለ ሌሊት የእስር ቤቱ ጠባቂ ከቤተሰቡ ጋር በመሆን የጌታን ቃል ይሰማል ፣ ሐዋርያትን ይቀበላል ፣ ቁስሎቹን ያጥባል - ምክንያቱም ድብደባ ስለተፈጸመባቸው ቆስለው ነበር - ከወላጆቹ ጋር በመሆን ይጠመቃል። በእግዚኣብሔር በማመናቸው የተነሳ ከእነርሱ ጋር ሆኖ እጅግ ተደሰተ (ቁ. 34)፣ ገበታ አዘጋጀ እና አብረዋቸው እንዲቆዩ ጳውሎስንና ሲላስን ጋበዛቸው።፡ በዚህ ስም-አልባ የእስር ቤት ውስጥ እኩለ ሌሊት ላይ የክርስቶስ ብርሃን ጨለማን ያበራል፣ ያሸንፋል - በልብ ውስጥ የነበረውን ሰንሰለቶች በመበጣጠስ በእርሱ እና በቤተሰቡ ውስጥ በጭራሽ ከእዚህ ቀደም ያልሰማ  ደስታ ይፈጥራል። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ተልእኮውን እያከናወነ ነው-ከመጀመሪያው፣ ከበዓለ ሃምሳ ቀን ጀምሮ እርሱ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ዋና ተዋናይ ነው።  መንፈስ ቅዱስ እንድንሠራ የሰጠንን ተልዕኮ በታማኝነት ማከናወን እንድንችል ይመራናል። ቅዱስ ወንጌልን እንድናሰራጭ ያግዘናል።

እኛም ዛሬ መንፈስ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ልባችንን እንድንከፍት እና እንደ ሊዲያ እንግዳ ተቀባይ እንድንሆን እንደ ጳውሎስ እና እንደ ሲላስ ጠንካራ የሆነ እምነት እንዲኖረን መንፈስ ቅዱስ እንዲረዳን፣ እንደ እስር ቤት ጠባቂው ሰው ልባችንን እንዲከፍትልን ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ እግዚኣብሔርን እንለምነው። መንፈስ ቅዱስ  እንደ ጳውሎስ እና ሲላስ ያለ ጠንካራ እምነት እንዲኖረን እንዲረዳን፣ እንዲሁም የእስር ቤቱ ጠባቂ የነበረው ሰው መንፈስ ቅዱስ ልቡን እንዲነካ እንደ ፈቀደው እኛም ልባችንን ለእርሱ ዛሬ ክፍት ማደረግ እችንል ዘንድ እንዲረዳን እንጠይቀው።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
30 October 2019, 15:12