ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ስብከተ ወንጌል ልብ ከእግ/ር ጋር እንዲገናኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ማለት ነው”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 05/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥቅምት 05/2012 ዓ.ም ባደረጉት የክፍል ዐስራ ሁለት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደረገው በሐዋርያት ሥራ 10፡34 ላይ በተጠቀሰውና እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በርግጥ ተረድቻለሁ፣ እግዚአብሔር ንጹሕ ያደርገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቁጠረው” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ትኩረቱን ያደረገ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “ስብከተ ወንጌል ልብ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ማለት ነው” ማለታቸው ተገልጹዋል።

በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በርግጥ ተረድቻለሁ፤ ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል። እግዚአብሔር፣ የሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የላከውም የሰላም የምሥራች መልእክት ይኸው ነው (የሐ. ሥራ 10፡34-36)።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥቅምት 05/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደ ጠቀሰው ቅዱስ ወንጌል በዓለም ውስጥ ያደርገው ጉዞ በሚያስደንቅ ሁኔታ እራሱን በሚገልጸው የእግዚአብሔር ታላቅ ፈጠራ ጋር አብሮ ሲጓዝ እንመለከታለን። ልጆቹ እያንዳንዱን ተጋላጭ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በመሻገር ሁለንተናዊ ለሆነ ደህንነት ራሳቸን ክፍት እንዲያደርጉ ይፈልጋል። ከውሃ እና ከመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሁሉ ከእራሳቸው እንዲወጡ እና ራሳቸውን ለሌሎች እንዲከፍቱ፣ ለሌሎች ቅርበት እንዲኖራቸው፣ አብሮ የመኖር ዘይቤን እንዲለማመዱ እና እያንዳንዱ ሰው በግለሰብ ደረጃ የሚያደርገው ግንኙነት ወደ ወንድማማችነት የመቀየር ልምድ እንዲኖራቸው ተጠርተዋል።

መንፈስ ቅዱስ በታሪክ ሂደት ውስጥ ሊያነሳሳው የሚፈልገውን የዚህን “የወንድማማችነት” ምስክርነት ሐዋርያው ጴጥሮስ እና ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ዋና ገጸ ባህርይ በመሆን መስክረውታል። በበዓለ ሃምሳ በጴንጤቆስጤ ዕለት በደቀ-መዛሙርቱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ እና የጌታን ስም በሚጠሩ ሰዎች ሁሉ ላይ ካረፈ በኋላ (ሐዋ. 2፡17.21 ፤ ገላቲያ 3፡1.5) ጴጥሮስ ለሕልውናው አስፈላጊ የሆነ ለውጥ ያገኘበትን ሁኔታ የሚያመላክት ክስተት ተፈጠረ። እርሱ በሚፀልይበት ጊዜ በእርሱ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማነሳሳት የሚችል መለኮታዊ ኃይል ሆኖ የሚያገለግል ራእይ ይቀበላል። ሰማይ ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱ ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ። በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበሩ አዕዋፍ ነበሩበት። የእነዚያን እንስሳት ሥጋ እንዲበላ የሚጋብዝ አንድ ድምጽ ሰማ። እንደ እርሱ ያለ አንድ ጥሩ አይሁዳዊ፣ በጌታ ሕግ የተከለከለውን ርኩስ የሆነ ነገር በጭራሽ እንደ ማይመገብ በመግለጽ ምላሽ ይሰጣል (ሐዋ 10፡11)። ከእዚያን በመቀጠል “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኵስ አትቍጠረው” የሚል ጠንከር ያለ ድምጽ ይሰማል።

ጌታ ጴጥሮስን ከእንግዲህ ንጹህ እና ንጹህ ባልሆኑ መስፈርቶች ላይ ተመሥርቶ ሁኔታዎችን እና ሰዎችን መገምገም አስፈላጊ እናዳልሆነ፣ ይልቁኑ የበለጠ ሰዎችን ለመረዳት ያስችለው ዘንድ፣ የሰዎችን እና የእነርሱን የልቡ መሻት መመልከት እንደ ሚገባው ይናገራል። ይህም ማለት ደግሞ በእርግጥ ሰውን የሚያረክሰው ወደ ውስጥ የሚገባ ነገር ሳይሆን ከሰው ልጅ ልቡ ውስጥ የሚወጣ ነገር ነው (ማር 7፡21)።

ከዚያ ራእይ በኋላ እግዚአብሔር ጴጥሮስን ለሕዝቡ ምጽዋት የሚሰጥ እና ሁል ጊዜም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ወደ ነበረው የግርዘት ስረዐት ያልፈጸመ፣ የባዕድ አገር ሰው ወደ ሆነው “የኢጣሊያ ክፍለ ጦር’ በሚባለው ሰራዊት ውስጥ የመቶ አለቃ ወደ ነበረው ቆርኔሌዎስ (የሐዋ 10፡1-2) ዘንድ ይልከዋል። ቀደም ሲል ካየው ራእይ እና መለኮታዊ ትምህርት ቀደም ብሎ ከተዘጋጀ በኋላ ጴጥሮስ “ለአይሁድ ያልተፈቀደውን” (ሐዋ 10፡28) ማለትም የመገረዝ ስነ-ስረዓት ያልፈጸሙ ሰዎች ቤት ገብቶ ከእነርሱ ጋር ለመመገብ ተስማማ። እርሱ እንዲሁ ከመልካም ምኞት በመነሳት ያደርገው ጉብኝት ሳይሆን፣ ነገር ግን ገና የማዳን ኃይል ያለውን ቃል ላልሰሙ ሰዎች ቃሉን ለማሰማት ነው።

በዚያ አረማውያን ቤት ውስጥ፣ ጴጥሮስ የተሰቀለውን እና ከሙታን የተነሳውን ክርስቶስን እና በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ የኃጢያት ስርየት መደረጉን መስበክ ይጀምራል። ጴጥሮስ እየተናገረ ሳለ በቆርኔሌዎስና በቤተሰቡ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ጴጥሮስም በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም አጠመቃቸው (ሐዋ 10፡48)።

ይህ እውነታ በኢየሩሳሌም በመታወቁ ጴጥሮስ በፈጸመው ተግባር የተደናገጡት ወንድሞች በሁኔታው በመሰናከላቸው የተነሳ ጴጥሮስን ክፉኛ ገሠጹት (ሐዋ 11፡1-3)። ጸሎት ያስገኘው ውጤት በወንጌላዊው ልብ ውስጥ ብቅ የሚለው በዚህ ጊዜ ነው-“አንድ ወንጌላዊ ከጸሎት ሲወጣ ልቡ የበለጠ ለጋስ ይሆናል፣ ራሱን ገለልተኛ ካደረገው ሕሊና ነፃ አውጥቷል እናም መልካም ለማድረግ እና ለመሥራት ይጓጓል፣ ከሌሎች ጋር ሕይወቱን ይጋራል”። በመሠረቱ፣ ጴጥሮስ ከቆርኔሌዎስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ፣ ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ጋር ህብረት በማድረግ ከእራሱ በመውጣት ይበልጡኑ ነጻ ሆነ። ስለሆነም የእስራኤል ሕዝብ መመረጡ በጎ የሆነ ሽልማት አለመሆኑን በመረዳት፣ ነገር ግን በነጻ የሚሰጥ የጥሪ ምልክት በመሆን በአረማውያን ሕዝቦች መካከል የመለኮታዊ ሽምግልና ምልክት መሆን ተረዳ።

ውድ ወንድሞች፣ ከሐዋርያት መርህ በመነሳት አንድ ወንጌላዊ እግዚአብሔር ለሚያከናውናቸው አዳዲስ ተግባራት እንቅፋት መሆን እንደማይችል እንማራለን፣ ይህም “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ” ነው (1ጢሞ 2፡4፣) የሰዎችን ልብ ከጌታ ጋር ማገናኘት ነው። ከወንድሞቻችን በተለይም ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች የምናሳየው ባህሪይ ምን ይመስላል? ከአብ ጋር እንዳይገናኙ እናግዳለን ወይስ ግንኙነቱ እንዲከናወን እናመቻቻለን?

ዛሬ እግዚአብሔር በእርሱ ድንቅ ሥራዎች መደሰት እንችል ዘንድ እንዲፈቅድልን፣ የእርሱን አዳዲስ ሥራዎች ለማደናቀፍ ሳይሆን፣ ከሞት የተነሳውን የክርስቶስ መንፈስ ወደ ዓለም የሚፈስበት እና ራሱን “የሁሉም ጌታ” አድርጎ በማቅረብ የሰዎችን ልብ  ወደ እርሱ መሳብ የሚችል ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን እንጠይቀው።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
16 October 2019, 14:29