ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ፣ አልባኖ ከተማ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ጀመሩ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ ውስጥ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች መካከል አንዱ በሆነው በአልባኖ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው መስከረም 10/2012 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በላሲዮ ክፍለ ሀገር፣ አልባኖ ሀገረ ስብከት የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ምክንያት በማድረግ፣ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ሲደረጉ የቆዩ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ከሀገረ ስብከቱ የደረሱን ዘጋባዎች አመልክተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አልባኖ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መሠረት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ያተኮረ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ክቡር አባ ጓልቴሮ ኢሳቂ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ክቡር አባ ጓልቴሮ እንዳስታወቁት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት ምክንያት በማደረግ በከተማው በርካታ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ገልጸው ከእነዚህም መካከል በድምቀት የሚታየው እና ለጋራ መኖሪያ ለሆነች ምድራችን የሚደረገውን ጥበቃ እና እንክብካቤን የሚገልጽ የግድግዳ ላይ ስዕል መሆኑን ገልጸዋል። ይህ በሀገረ ስብከቱ ሕንጻ ግድግዳ ላይ የተሳለው ስዕል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በማስመሰል፣ በቆሻሻ አየር የተበከለው ሰማይ ሲጸዳ የሚያሳይ ስዕል መሆኑን አስረድተዋል። ስፋት ባለው ግድግዳ ላይ የተሳለው ይህ ስዕል ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩት ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ከሚያቀርቡበት፣ ከፒያ አደባባይ ላይ በግልጽ የሚታይ መሆኑን አስረድተዋል። ይህን የግድግዳ ላይ ስዕል የከተማው ከንቲባ የሆኑት ክቡር አቶ ኒኮላ ማሪኒ ለቅዱስነታቸው ከፍተው የሚያሳዩ መሆኑ ታውቋል።

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ መልዕክትን የሚያስታውስ የግድግዳ ላይ ስዕል፣

እውቁ የግድግዳ ላይ ሰዓሊ አርቲስት ማውሮ ፓሎታ፣ ይህን ስዕል ለመሳል መነሻ የሆነው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት መሆኑን አስረድቷል። ሰዓሊ ማውሮ ስለ ስዕሉ ሲያስረዳ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንጹሕ አየርን በሚበክል ጪስ የተሸፈንች ጸሐይን አጽድተው ብርሃን እንዲወጣ ሲያደርጉ ያሳያል ብለዋል። የስዕሉ ዋና መልዕክትም ስነ ምሕዳርን አስመልክተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያስተላልፉት መልዕክት እና አስተምህሮ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን መላው ዓለም እንዲገነዘብው ለማድረግ መሆኑን ሰዓሊ ማውሮ ፓሎታ አስታውቋል።      

21 September 2019, 17:21