ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ሰማዕታት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ፍሬያማነት ያመላክታሉ”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ረቡዕ በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የሚያቀርቡ መሆኑ ሲታወቅ፣ ዛሬ መስከረም 14/2012 ዓ. ም. የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ከዚህ በፊት በጀመሩት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ በማድረግ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል።

ክቡራን እና ክቡራት አንባቢዎቻችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስከረም 14 ቀን ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የጀመርነውን ጉዞ በማቀጠል ቅዱስ ወንጌል በዓለም ዙሪያ የሚያደርገውን ጉዞ እንመለከታለን። ቅዱስ ሉቃስ ሕይወቱን በሚያሳይ ታላቅ ጥበብ በመታገዝ የዚህ ጉዞ ፍሬያማነት እና በክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል የተከሰቱ አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን ያሳያል። ከመጀመሪያ አንስቶ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ በመካከላቸው የተፈጠሩት ችግሮች መለያየትን ሳያስከትሉ እንዴት መጓዝ ይቻላል የሚለውን መመልከት እና ማጤን ያስፈልጋል።

በወቅቱ በነበረው የክርስቲያን ማሕበረሰብ መካከል ከአይሁዶች በተጨማሪ ከሌሎች አገሮች የመጡም የአይሁድ ወገን ያልሆኑም ነበሩበት። እነዚህ ታዲያ የራሳቸው ሐይማኖት፣ ወግ እና ባሕል ያላቸው፣ ዛሬ እኛ አረመኔዎች ብለን የምንጠራቸው ናቸው። በመካከላቸው እነዚህም ይስተናገዱ ነበር። ይህ አብሮ መኖር በቁጥር የማይመጣጠን በመሆኑ ልዩ ልዩ ጎራዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። ለአንድ ማሕበረሰብ መበታተን ዋና ምክንያት ምንድር ነው ? ቢባል ቀዳሚው ምክንያት አባላቱ በጎራ መከፋፈል ሲጀምሩ ነው። የማጉረምረም እና የሐሜት ጎራ አንዱ ነበር። ግሪኮች በማህበረሰቡ መካከል ለመበለቶቻቸው ግድየለሽ በመሆናቸው ምክንያት ያጉረመርሙ ነበር። ሐዋርያት ታዲያ በክርስቲያን ማሕበረሰብ መካከል ልዩ ልዩ ጎራዎች መፈጠራቸውን በተገነዘቡ ጊዜ በጋራ በመመካከር ምፍትሄን ለማግኘት ጥረት ያደርጉ ነበር። የአገልግሎት ድርሻን ተከፋፍለው በመውሰድ፣ የወንጌል ስርጭትን የሚያደናቅፉ እንቅፋቶችን እያስወገዱ፣ በድሕነት ሕይወት ለተጎሳቆሉ ክርስቲያኖችም አስፈላጊን እንክብካቤ ያደርጉላቸው ነበር።

ሐዋርያት የተጠሩበት ቀዳሚ ተልዕኮ ጸሎትን ማቅረብ እና የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ማብሰር መሆኑን በሚገባ ይበልጥ ያውቁ ነበር። ጸሎት እና ወንጌልን መስበክ፤ ከዚህ በተጨማሪ ከክርስቲያኖቹ መካከል መልካም ስም ያላቸውን፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉትን እና ጥበብም ያላቸውን ሰባቱ ሰው በመምረጥ ችግሮች እንዲቃለሉ ያደርጉ ነበር።  « ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህን ኀላፊነት ለእነርሱ እንሰጣለን፤ » (ሐዋ. 6፡3) ከዚህ በኋላ እጆቻቸውን ጭነውባቸው ሃላፊነትን ከሰጧቸው በኋላ ለክርስትያኖች ምግብን በማከፋፈል አገልግሎት ተሰማርተዋል። እነዚህ ሰባቱ ሰዎችም ለዚህ አገልግሎት የተጠሩ ዲያቆናት ናቸው። አንድ ዲያቆን በቤተክርስቲያን ውስጥ እንደ ካህን በመንበረ ታቦት የሚቆም ሳይሆን የራሱ የአገልግሎት ዘርፍ ያለው ሰው ነው። በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚቀርቡ አገልግሎቶችን የሚከታተል ነው። ከዚህ አገልግሎቱ ውጭ አንድ ዲያቆን ወደ መንበረ ታቦት ሄዶ የመቆም ፍላጎት የሚያድርበት ከሆነ ተሳስቷል ማለት ነው። ምክንያቱም የተጠራው ለዚህ አገልግሎት ባለመሆኑ። እነዚህ ሁለት ዓይነት የአገልግሎት መንገዶች ማለትም ወንጌልን የማስተማር እና ለምዕመናን የቸርነት አገልግሎትን ማቅረብ ለቤተክርስቲያን እድገት ትልቅ አስተዋጽዖን ያበረክታሉ።

ሐዋርያት ከምዕመናኑ መካከል መርጠው ለአገልግሎት ካበቋቸው ሰባት ዲያቆናት መካከል የሁለቱ ማለትም የእስጢፋኖስ እና የፊሊጶስ የድቁና አገልግሎት በልዩ መልክ ይታይ ነበር። የእስጢፋኖስ የወንጌል አገልግሎት በሃይል የተሞላ እና ቃላቶቹም ብዙን ጊዜ ተቃውሞን ያስነሳ ነበር። ተቃዋሚዎቹ ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው ምን አደረጉ ?

እርሱን ከአገልግሎቱ ለማስወገድ ብለው ጥቃቅን ምክንያቶችን በመምረጥ ፣ ስሙን ማጥፋት ወይም የሐሰት ክስን ይመሰርቱበት ነበር። ስምን ማጥፋት ሁል ጊዜ እንደሚገድል በሚገባ እናውቃለን። ይህ የግለ ሰብን መልካም ስም በማጉደፍ ወደ ጥፋት የሚያደርስ ክፉ ተግባር ከሰውየው አልፎ ቤተክርስቲያንንም ሊጎዳ የሚችል፣ የራሳቸውን ስህተት ለመሸፈን የሚደርግ የጥቂት ሰዎች ክፉ ተግባር ነው።

ተቃዋሚዎቹ በእስጢፋኖስ ላይ ክስን በመመስረት የሐሰት ምስክር ጠርተው ወደ ሸንጎ ፊት እንዲቀርብ አደረጉ። ልክ በኢየሱስ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ በሌሎችም ሰማዕታት ላይ ተመሳሳይ መንገድን ይጠቀሙ ነበር። እስጢፋኖስም ወደ ሸንጎ ፊት በቀረበ ጊዜ እራሱን ለመከላከል እንዲችል በክርስቶስ ላይ የተደረገውን ታሪክ ከቅዱስ መጽሐፍ እየጠቀሰ ማስረዳት ጀመረ። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ እነዚህን የመሳሰሉ ታሪኮችን ለማስታወስ መሠርታዊ መንገድ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በእስጢፋኖስ ልብ ውስጥ የነበረው መለኮታዊ ሃይል፣ ነቢያት እና ክርስቶስ ራሱ የተያዙበትን ግብዝነት በድፍረት እንዲያወግዝ ብርታት ሆኖታል። «ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም»። (ሐዋ. 7፡52) በማለት ግልጽ ቃላትን ተናገረ። ይህ ንግግሩ ሸንጎን በማስቆጣቱ እስጢፋኖስን ለሞት ቅጣት ፍርድ አበቃው። ለዚህ በመብቃቱ የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታይ ለመሆን በቃ። ለማምለጥም አልሞከረም ወይም ከዚህ የሞት ቅጣት ፍርድ የሚያድኑ ሰዎች እርዳታንም አልፈለገም። የሕይወቱን አደራ በእግዚአብሔር እጅ ላይ በማኖር አስገራሚ ጸሎት አቀረበ፥ ተንበርክኮ፤ በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ! ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ ጮኸ፤ ይህን ካለ በኋላም አንቀላፋ። (ሐዋ. 7:60)

እነዚህ የእስጢፋኖስ ቃላት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ከመግለጽ ይልቅ ሕይወታችንን በእግዚአብሔር እጅ ማድረግን እና የበደሉን ይቅር በማለት የእምነታችንን ትርጉም ጠንቅቀን እንድናውቅ ያግዙናል። በዘመናችን ከምን ጊዜም በላይ በርካታ ሰማዕታት በዓለም ዙሪያ አሉ። የዛሬይቱ ቤተክርስቲያን በቁጥር በርካታ ሰማዕታት አሏት። በእነርሱ ደምም በመታጠር አዳዲስ ክርስቲያኖችን በማፍራት የእግዚአብሔር ሕዝብ እድገት በገሃድ እያስመሰከረች ትገኛልለች።  ሰማዕታት፣ ዮሐንስ በራእው እንደተናገረው፣ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው ፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል (ዮሐ. ራእይ 7:14)።

እኛም የጥንቶችን እና የዛሬዎችን ሰማዕታትን በመመልከት፣ ሙሉ ሕይወት መኖር የምንችልበትን መንገድ መማር እንድንችል፣ በየዕለቱ ለወንጌል ሰማዕትነት እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ መሆን እንድንችል እግዚአብሔርን በጸሎታችን እንጠይቅ” ብለዋል።   

25 September 2019, 17:56