ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ብቻ ዘላቂነትን ያገኛል”።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ በቫቲካን ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የሚያቀርቡ መሆኑ ይታወቃል። በእዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት መስከረም 7/2012 ዓ. ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቅርበዋል። በዛሬው ዕለት ያደረጉት አስተንትኖ ከዚህ በፊት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ ተንተርሰው ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ያቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ ክፍል ስምንተኛው እና በሐዋ. 5፤ 34-35/38-39 መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል።

“ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤ ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል። ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው፤ አትንኳቸው፤ ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል” (በሐዋ. 5፤ 34-35/38-39) በሚለው ላይ ተንተርሰው “ማንኛውም የሰው ልጅ እቅድ የመፍረስ አደጋ ሊደርስበት ይችላል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣ ብቻ ዘላቂነት አለው” ማለታቸው ተገልጿል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዕለት መስከረም 7/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከዚህ በፊት ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በመውሰድ የጀመርነውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችንን ብበመቀጠል በዛሬው ዕለትም የምናየው ይሆናል። በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ በማለት ከሸንጎው በኩል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ እና ሌሎችም ሐዋርያት፣ ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ቢነገራቸውም ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም ሁሉ መመስከርን የሚያግድ ምንም ሃይል አይኖርም በማለት በድፍረት ተናገሩ።

እነዚህ አስራ ሁለቱ ሐዋርያት በእምነት አማካይነት በሚገኘው መታዘዝ ሰዎችን  ወደ ኢየሱስ ለመጥራት ጸጋንና የሐዋርያነትን አገልግሎት ተቀበሉ። ሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስ በላያቸው ላይ ከወረደበት ጊዜ አንስቶ ብቻቸውን እንዳልሆኑ ያውቁ ነበር። በውስጣቸው ያደረው የመንፈስ ቅዱስ ሃይል የተጠሩበትን አገልግሎት እንዲለማመዱ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም ሕብረት መፍጠራቸውን እንዲመሰክሩ ይገፋፋቸው ነበር (የሐዋ. 5፤32)። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሕብረት እንዳላቸው ከመናገር ውጭ ሌላ ምንም ስሜት አልነበራቸውም። በመካከላቸው ጠንካራ አንድነትን በመፍጠር ራሳቸውን ከማስፈራሪያ ይከላከሉ ነበር። ያላቸው ድፍረት አስገራሚ ነበር። ደፍረው የቆሙት እነዚህ ሐዋርያት አስቀድሞ ፈሪዎች፣ ኢየሱስ በወታደሮች እጅ ሲያዝ ጥለው የሸሹ እና ያመለጡ ነበሩ። ከዚያ ፍራቻ ወጥተው ዛሬ ደፋር ሊሆኑ የበቁት ለምንድነው? ድፍረትን ያገኙት መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው ስላለ ነው። እኛም ብንሆን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ካለ ደፋሮች እንሆናለን፤ ጉዟችንን በድፍረት እንጓዛለን። አሸናፊዎች እንሆናለ። የምናሸንፈውም በራሳችን ሃይል ሳይሆን በውስጣችን ባለው በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ነው። ሐዋርያት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤን ከመመስከር ወደ ኋላ አላሉም። እስከ ሰማዕትነትም ደርሰዋል። ሰማዕታት ሕይወታቸውን ሳይቀር ለሞት አሳልፈው ይሰጣሉ፣ ክርስቲያንነታቸውንም ሳይደብቁ በድፍረት ይመሰክራሉ። ከአራት ዓመት በፊት በሊቢያ ውስጥ የተሰው  የኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን እናስታውሳለን። አንገታቸው ስቆረጥ ያሰሙት ጩሄት ኢየሱስ፣ ኢየሱስ የሚል ነበር። እምነታቸውን አልካዱም ወይም በሌላ ነገር አልለወጡትም። ለዚህ መስዋዕትነት የበቁትም መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው ስላለ ነው። የዘመናችን ሰማዕታት ናቸው። እነዚህን የመሰሉ ደፋር ክርስቲያኖች ዛሬ በዘመናችንም አሉ። ሐዋርያት ከሞት በተነሳው በኢየሱስ ክርስቶስ የተላኩት የመንፈስ ቅዱስ መልዕክተኞች ናቸው።

ይህ የክርስትያን አይሁዶች ወይም የሐዋርያት ቆራጥ ምስክርነት፣ ለሞት ቅጣት የሚዳርግ፣ አመጽንም የሚያስከትል ነው። በክርስቲያኖች ላይ የሚደርስ መከራ ሁል ጊዜ ተመሳሳይ ነው። የክርስትናን እምነት በሚቃወሙት መካከል ቁጣን በመቀስቀስ ክርስቲያኖችን ለሞት ያጋልጣቸዋል።

ነገር ግን በዚህ የሐዋርያት ታሪክ ውስጥ የራሱን አቋም በመውሰድ ምላሽን መስጠት የሚመርጥ፣ የሕግ አዋቂ፣ በሕዝቡ ዘንድም የተከበረ አንድ ፈሪሳዊ፣ ስሙም ገማልያል የሚባል ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ የአባቶችን ሕግ የተማረው በገማልያል ትምህርት ቤት ገብቶ ነበር። ገማልያል ከወትሮው የተለዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው፣ የማስተዋል ጥበብን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ለወንድሞቹ ያሳይ ነበር። እርሱ፣ እንደ መሲሕ የሚመጡትን አንዳንድ ገጸ-ባህሪያትን በመጥቀስ ፣ እያንዳንዱ የሰው ልጅ የሚያጋጥመን ሁሉ በምስጋና በመቀበል እና ከላይ ከእግዚአብሔር ሚመጣውን ሁሉ የሚቀበልበት እና የሚሸከምበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናገራቸው። የሰው ልጅ እቅድ በጊዜ የተወሰነ እና ጊዜው ሲደርስም የሚፈርስ መሆኑ አይቀርም። በርካታ የፖለቲካ ውጥኖችን ተመልከቷቸው፣ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ምን ያህል ልዩነት እንዳላቸው እናውቃለን። ትላልቅ የዓለማችን ነገሥታትን፣ ያለፈው ዘመን ጨቋኝ መንግሥታትን እናስታውስ። ገናናነት የሚሰማቸው እና ዓለምንም የሚገዙ ይመስላቸው ነበር። ነገር ግን መጨረሻቸው ሲደርስ ሁሉም ፈርሰው ቀሩ። የዘመናችን ገናና ነገስታትን ተመልከቷቸው፤ እነርሱም እግዚአብሔር አብሯቸው ካልሆነ የሚፈርሱ ናቸው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ሃይል እና ስልጣን ዘላቂነት የለውም። ዘለዓለማዊነት ያለው የእግዚአብሔር ሃይል ብቻ ነው። በመጨረሻዎቹ ሁለት ዘመናት የሆነውን የክርስቲያኖች ወይም የቤተክርስቲያንን ታሪክ የተመለከትን እንደሆነ፣ ብዙ ሐጢአቶች አልተፈጸሙም፣ ብዙ አስነዋሪ ሥራዎች አልተሰሩም? ታዲያ ለምንድር ነው ያልፈረሱት? ያልፈረሱበት ምክንያት እግዚአብሔር በመካከላቸው ስለሚገኝ ነው። ሐጢአትን ሰርተናል፣ በድለናልም። ነገ ግን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሆነ በምሕረቱ ብዛት ቆመን እንሄዳለን። ቀድሞ ምሕረቱን የሚልክልን እና የሚያድነን እኛን ነው። እርሱ አዳኛችን እና የምሕረት አባታችን ነው፣ ሃይላችንም እርሱ ነው።  

ገማልያል፣ የሰዎች እቅድ እድሜ ሳይኖራቸው እንዲሁ ፈርሰው እንደሚቀሩ የተናገረው፣ በሌላ ወገን መሲሕ ሆነው የሚመጡትን አንዳንድ ገጸ-ባህሪያትን በመጥቀስ የተናገረው ለዚህ ነው። ለተማሪዎቹ ያደረገውን ንግግር ሲፈጽም “አንዳንድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሐሰተኛ መምሕራን የሰሙትን በማመናቸው ተበታትነው ቀሩ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚመጣ የሚተማመኑትን ልትገቷቸው አትችሉም” በማለት መክሯቸዋል።  ይህን በመናገሩ እኛም እንድናስተውል እና በጥበብ እንድናሰላስለው ያስተምረናል።

እነዚህ የክርስትናን መገድን በአዲስ ብርሃን ለመጓዝ የሚያስችሉትን መስፈርቶች ከወንጌል ውስጥ በማቅረብ የሚመክሩን ናቸው። ምንያቱም አንድን ዛፍ ማወቅ የምንችለው በፍሬው ነውና (ማቴ. 7፤16)። በዚህ ዓይነት የክርስትና መንገድ የሚጓዙ ተስፋ ያደረጉትን ሲያገኙ ፣ በራሳቸው ባሻቸው መንገድ የሚጓዙት የሞትን መንገድ በመጓዝ ሐዋርያትን ሳይቀር ለመግደል ይነሳሉ።

መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን እንዲገኝ፣ በግልም ሆነ በጋራ የማስተዋልን ጥበብ እንዲሰጠን ወደ መንፈስ ቅዱስ ጸሎታችንን እናቅርብ። በዘመናት መካከል የተፈጸሙትን የእግዚአብሔር የድነት ሥራ ታሪክ እንድንመለከት፣ ዛሬ በዘመናችንም የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ የሚመሰክሩ ሰዎችን መመልከት እንድንችል ጸሎታችንን ወድ መንፈስ ቅዱስ እናቅርብ። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የሕያው እግዚአብሔር መልዕክተኞች ናቸውና፤ አመሰግናለሁ”!                                                     

18 September 2019, 17:32