ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የብዙዎችን መከራ እየተመለከትን ችላ ማለት የለብንም”።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እሁድ መስከረም 18/2012 ዓ. ም. 105ኛው ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ በኢጣሊያ ውስጥ የሚገኙ በርካታ የተለያዩ አገሮች ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ የስደተኞች መጠለያ ማዕከላት ሠራተኞች፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሃገር ጎብኝዎች መገኘታቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ባቀረቡት መልዕክታቸው “ባልንጀራን መውደድ ማለት የሚደርስላቸውን አጥተው በየመንገዱ ወድቀው ችግር ላይ ለሚገኙት በሙሉ የእርዳታ እጆቻችንን መዘርጋት እንደ ሆነ አስረድተዋል። 105ኛ ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ምክንያት በማድረግ ቅዱስነታቸው ትናንት እሑድ መስከረም 18/2012 ዓ. ም. ያደረጉት ንግግር ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የዛሬው የዳዊት መዝሙር፣ የምዕመናን የመልስ ጸሎት፣ እግዚአብሔር ድሃ ዐደጎችንና መበለቶችን የሚደግፍ፣ የተዋረዱትን ከፍ የሚያድረግ፣ ስደተኞችን የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን ያስታውሰናል። ዘማሪው ዳዊት በተለየ መልኩ በተለይ እነዚያ የተረሱትን፣ ረዳት የሌላቸውን እና ለብዝበዛ የተጋለጡትን እንድናስታውስ ይጋብዘናል። እግዚአብሔር ለተሰደዱት፣ ለተፈናቀሉት፣ በመከራ ለወደቁ እናቶች እና ሕጻናት፣ መብታቸውን ለተገፈፉት እና ለተናቁት የተለየ ጥበቃን እና ድጋፍ ያደርግላቸዋል። ለእነዚህ በችግር ላይ ለወደቁት ሕዝቦች የተለየ ድጋፍን እንዲያደርጉላቸው እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ በሙሉ ያሳስባቸዋል።

በኦሪት ዘጸዓት መጽሐፍ በምዕ. 22፡23 ላይ፣ “ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ” በማለት እግዚአብሔር ችግር ላይ በወደቁት በመበለቶች እና አሳዳጊ በሌላቸው ሕጻናት ላይ ምንም ዓይነት በደል እንዳያደርሱባቸው የእስራኤልን ሕዝብ ያስጠነቅቃቸዋል። በኦሪት ዘዳግምም እንደዚሁ በምዕ. 24:17 እና በምዕ. 27:19 ላይ ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ፤ “በመጻተኛው፣ አባት በሌለውና በመበለቲቱ ላይ ፍትሕ የሚያዛባ የተረገመ ይሁን።” ተብሎ ተጽፏል። እግዚአብሔር ይህን ማስጠንቀቂያ የሰጠበት ምክንያት በእነዚህ መጽሐፍት ላይ በግልጽ ተጠቅሷል። የእስራኤል አምላክ አባት እና እናት ለሌላቸው ሕጻናት፣ ለመበለቶችም የሚራራ እና የሚጨነቅ፣ የሚበሉትን እና የሚለብሱትን በማቅረብ ፍቅሩንም የሚገልጽ አምላክ መሆኑ በኦሪት ዘዳ. ምዕ. 10፡18 ላይ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። ለተናቁት፣ ለተበደሉት እና በችግር ላይ ለወደቁት የሚደረግ ድጋፍ፣ እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ያለው አባታዊ ቸርነት የተገለጠበት እና የእስራኤል ሕዝብም የእግዚአብሔርን ምሳሌ እንዲከተሉ የሚያደርግ የሞራል ግዴታ መኖሩን ይገልጻል።

እኛም በመካከላችን በችግር ላይ ለሚገኙት ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች፣ ረዳት ለሌላቸው እናቶች፣ ተንከባካቢ ወይም አሳዳጊ ለሌላቸው ሕጻናት ልዩ ትኩረትን እንድንሰጠ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። መስከረም 18/2012 ዓ. ም. በተከበረው 105ኛ ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን ላይ ‘ስለ ስደተኞች ብቻ አይደለም’ በማለት ተደጋግሞ የተገጸው መሪ ቃልም ይህን መልዕክት የሚያሳስብ ነው። በእርግጥም ዘንድሮ የተከበረው ዓለም አቀፍ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቀን፣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ከቄያቸው ተፈናቅለው፣ ከአገራቸው ተሰድደው በችግር ውስጥ የሚገኙትን ብቻ ሳይሆን ከእነርሱም ጋር በማሕበረሰቡ መካከል እንዲናቁ እና እንዲገለሉ የሚያደርግ ባሕል ሰለባ የሆኑትንም የሚያጠቃልል ነው። ለእነዚህ ሰዎች በሙሉ የቸርነት እጆቻችንን እንድንዘረጋላቸው እግዚአብሔር ይጠይቀናል። ማንንም ወደ ጎን ሳንል፣  ልዩነትንም ሳናደርግ፣ የመላው ሰብዓዊ ፍጡር ክብርን መልሰን መገንባት ያስፈልጋል።

ከዚህ የቸርነት ተግባር ጋር ሳንዘነጋው ማስታወስ ያለብን ሌላው ተግባር፣ በሰዎች መካከል መለያየትን በመፍጠር፣ ጥቂት ሰዎች የራሳቸውን ዝና፣ ሃብት እና ክብር ብቻ ለማስከበር የሚያደርጉትን የፍትህ መዛባትን እና መጓደል ነው። የዛሬው ዓለም ከማሕበረሰብ መካከል በተገለሉት እና በደሄዩት ሰዎች ላይ ይበልጥ ጨካኝ እየሆነ መጥቷል። በማደግ ላይ የሚገኙ የደሃ አገሮች ሕዝቦች የአገራቸውን የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት እንዳይሆኑ፣ የተፈጥሮ ሃብቶቻቸውን ብቻ ሳይሆን የሰው ጉልበትንም ለጥቂት ሰዎች ጥቅም ሲባል እየተበዘበዙ ይገኛሉ። ጦርነት በተወሰኑ አገሮች ብቻ ይካሄዳል፤ ነገር ግን ለጦርነቱ የጦር መሣሪያዎችን በማምረት  የሚደጉሙ አገሮች በጦርነቱ ምክንያት የሚፈናቀሉትን እና የሚሰደዱትን ችግረኞች ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኞች ሆነው አልተገኙም። የጦርነቱ አደጋ ገፈት ቀማሾች፣ የአደጋው ተጠቂዎች ሁል ጊዜ አቅመ ደካሞች፣ ሕጻናት እና እናቶች፣ በድህነት ሕይወት የሚሰቃዩት እና የሃብታሞች ማዕድ ትርፍራፊ እንኳን እንዳይበሉ የሚከለከሉ ናቸው። 

ዛሬ ከትንቢተ አሞ. 6፡ 1 እና 4-7 ተውስዶ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ ላይ “በጽዮን ተዘልላችሁ የምትቀመጡ፣ በሰማርያ ተራራ ያለ ሥጋት የምትኖሩ፣ የእስራኤልም ሕዝብ ለርዳታ ወደ እናንተ የሚመጡባችሁ፣ እናንት የአሕዛብ አለቆች ሆይ፤ ወዮላችሁ! በዝሆን ጥርስ ባጌጠ ዐልጋ ላይ ለምትተኙ፤ በድንክ ዐልጋችሁ ላይ ለምትዝናኑ፣ ከበጎች መንጋ ጠቦትን፣ ከጋጣም ጥጃን ለምትበሉ፤ ባልተቃኘ በገና ለምትዘፍኑ፣ በሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ለምትሹ፣ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፣ ምርጥ ሽቱም ለምትቀቡ፣ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ወዮላችሁ! ስለዚህ እናንተ በመጀመሪያ በምርኮ ከሚወሰዱት መካከል ናቸሁ፤ መፈንጠዛችሁና መዝናናታችሁም ያበቃል” የሚለው መታወስ ይኖርበታል። በጽዮን በደስታ እና በፈንጠዚያ ላይ ያላችሁ ወየውላችሁ! በስውርም ቢሆን የእግዚአብሔርን ሕዝብ የምታስጨንቁ ወየውላችሁ ይላል። እነዚያ አስጨናዎች ለመብላቸው እና መጠጣቸው ከማሰብ በቀር ሌላ ምንም አያሳስባቸውም። ከሁለት ሺህ ስምንት መቶ ዓመታት በኋላ ዛሬም ቢሆን ይህ የእግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ በድጋሚ አዲስ ሆኖ መቅረቡ የሚደንቅ ነው። ዛሬም ቢሆን የምቾት ባሕል ተጠናውቶን፣ የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን የስቃይ ጩሄት ወደ ጎን በማድረግ በሰዎች መካከል ልዩነትን በመፍጠር፣ ልዩነቱም እንድጎላ በሚያደርግ የግሎባላይዜሽን ሥርዓት ውስጥ ገብተን እንገኛለን።

በሉቃ. ወንጌል ውስጥ እንደተቀሰው ሐብታም ሰው ሆነን የመቅረት አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል።  በዚህ የወንጌል ክፍል የተጠቀሰው ታሪክ እንደሚከተለው ይነበባል፥ “መላ ሰውነቱ በቊስል የተወረረ አንድ አልዓዛር የሚባል ድኻ በዚህ ሀብታም ሰው ደጃፍ ይተኛ ነበር፤ ከሀብታሙ ሰው ማእድ የወደቀውን ፍርፋሪ እንኳ ሊመገብ ይመኝ ነበር፤ ውሾችም ሳይቀሩ መጥተው ቊስሉን ይልሱ ነበር። “ይህም ድኻ ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም ዕቅፍ ወሰዱት። ሀብታሙም ሰው ደግሞ ሞቶ ተቀበረ” (ሉቃ. 16:20-21) ውድ የሆኑ ልብሶችን ለራሱ ይገዛ የነበረ፣ ቤቱንም በውድ ዕቃ ያስጌጥ የነበረ ሃብታም ሰው የአልዕዛርን ስቃይ ማየት ፈጽሞ አይፈልጉም ነበር። የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ስቃይ የማንመለከት ከሆነ የራሳችንን ድሎት እና ምቾት ብቻ የምንመለከት ከሆነ እንደ ሃብታሙ ሰው ሆነናል ማለት ነው።

ክርስቲያን እንደ መሆናችን መጠን በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እየተመለከትን፣ በዘመናዊ መንገድ የሚፈጸመውን የባርነት ሕይወት፣ የልዩነት እና የመከፋፈል አዝማሚያዎችን እየተመለከትን በዝምታ ማለፍ አንችልም። በበርካታ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሱ መከራዎችን እየተመለከትን ልባችንን አደንድነን መቀመጥ አንችልም። ከሚሰቃዩት ጋር መሰቃየትን፣ ለደረሰባቸው ችግሮች ተገቢውን ምላሽ መስጠት መዘንጋት የለብንም፣

የእግዚአብሔር ሕዝቦች መሆን ከፈለግን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ፣ በምዕ. 6:14 ላይ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ፣ ይህን ትእዛዝ ያለ ዕድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ እንድትጠብቅ” የሚለውን ትዕዛዝ መጠበቅ ይኖርብናል። ትዕዛዙም እግዚአብሔርን እና ጎረቤትህን ውደድ የሚል ሲሆን እነዚህ ሁለቱ ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም። ጎረቤቶቻችንን እንደራሳችን መውደድ ማለት ደግሞ እድገትን እና ብልጽግናን ለማምጣት የሚያግዝ የምድራችንን ፍሬ ለእያንዳንዱ ሰው እና ቤተሰብ በማዳረስ ፍትሃዊ ዓለምን መገንባት እና መሠረታዊው የሰው ልጅ መብት እና ክብር ማረጋገጥ ማለት ነው።

ጎረቤቶቻችንን መውደድ ማለት በስቃይ እና በመከራ ውስጥ ለሚገኙት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መራራት፣ ወደ እነርሱ ቀርቦ ታሪካቸውን መጋራት፣ ቁስሎቻቸውንም በመንካት የሕመማቸው ተካፋይ መሆን እና በእውነቱ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር መግለጽ ማለት ነው።  ይህ ማለት ደግሞ የፍትህ ለተጓደለባቸው በሙሉ፣ በዓለም ዙሪያ በየመንገዱ ተበታትነው የሚገኙትን፣ የቁስላቸውን ሕመም በማስታገስ፣ ለእለታዊ ኑሮ የሚያስፈልጋቸውን እርዳት ማግኘት ወደሚችሉበት መጠለያ መሰብሰብ ማለት ነው።

እግዚአብሔር ይህን የተቀደሰ ትዕዛዝ ለሕዝቡ በሙሉ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም በኩል አጽንቶ የሰጠው ለሰው ልጅ በሙሉ መቀደስ እንዲሆን በማለት ነው። በመሆኑም በእርሱ ቀዳሚ ትዕዛዝ መሠረት የመረዳዳትን እና የርህራሄን ልብ በሰብዓዊ ቤተሰብ መላከከል እንዲነግሥ በማድረግ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የተገለጠው የእግዚአብሔር እቅድ፣ ይህም ወንድሞች እና እህቶች የሆኑት በሙሉ የአንድ እግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የመላው ዓለም ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ከወደቁትም ጋር፣ ተመሳሳይ የመከራን መንገድ ለመጓዝ ከመረጡት ጋር በመሆን የመልካም መንገድ እናት ወደ ሆነችው፣ ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ ፍቅር ጸሎታችንን ዛሬ በሕብረት እናቀርባለን”።

30 September 2019, 17:14