ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ተካፋዮች መልእክት ላኩ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት በኒውዮርክ ከተማ ከትናንት መስከረም 12-13/2012 ዓ. ም. በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ተካፋዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት መላካቸውን የቫቲካን ዜና አገልግሎት አስታውቋል። የቅዱስነታቸውን መልዕክት ሙሉ ይዘት ትርጉም የሚከተለው ነው፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በዘንድሮ 2012 ዓ. ም. የአየር ንብረት ስብሰባ ላይ ለተገኛችሁ በሙሉ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ።

በዘመናችን ታላቅ ስጋትን ከፈጠሩ ችግሮች መካከል አንዱ የሆነውን የአየር ለውጥ ክስተት ለአገራት እና ለመንግሥታት መሪዎች ለማሳሰብ ይህን ታላቅ ስብሰባን ላዘጋጁት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጸሐፊ ለሆኑት ለክቡር አንቶኒዮ ጉቴረዝ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በእርግጥ የአየር ለውጥ በዘመናችን ካጋጠሙን ዋና ዋና ችግሮች መካከል አንዱ ነው። ለዚህ ችግር ምላሽን ለመስጠት የሰው ልጅ ሦስት ታላላቅ ሥነ ምግባራዊ ባሕርያትን እንዲያዳብር ተጠርቷል። እነዚህም ታማኝነት፣ ሀላፊነት እና ድፍረት ናቸው።

በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ላይ፣ ታህሳስ 2/2008 ዓ. ም. በተደረሰው ስምምነት መሰረት የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ከውድመት ለመከላከል ፈጣን የጋራ ሃላፊነት መወሰድ እንዳለበት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግንዛቤን ማግኘቱ ይታወሳል። ስምምነቱ ከተደረገ ከአራት ዓመት በኋላ፣ መንግሥታቱ የወሰዱት ተነሳሽነት እጅግ ደካማ እና የተቀመጠውን ዓላማ ለማሳካት የሚኖረን ጉዞ በጣም ሩቅ መሆኑን እንመለከታለን።

ሌሎች በርካታ ጅምሮች መኖራቸው ቢታወቅም፣ መንግሥታት ብቻ ሳይሆኑ ሕዝባዊ ተቋማትም ጭምር፣ የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ላይ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ ችግር ላይ የወደቀውን የድሃውን ዓለም ሕዝብ ለመታደግ፣ የሰው ሃይል፣ የገንዘብ ድጋፍ እና የቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለማድረግ በእውነቱ የፖለቲካ ፍላጎት ታይቷል ወይ ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል።

ሁኔታዎች ጥሩ ባልሆኑበት፣ ምድራችንም በከፍተኛ ችግር ላይ በወደቀችበት ባሁኑ ወቅት ብዙ እድሎች አሁንም አሉ። እነዚህን እድሎች በሚገባ መጠቀም እንጂ እንዲያመልጡን አያስፈልግም። እነዚህን ዕድሎች ሁለገብ ሰብዓዊ እድገትን በማምጣት፣ መጪው ትውልድ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር ለማድረግ ካለን ቆራጥ ውሳኔ ጋር ተግባራዊ እናድርጋቸው። ከእንዱስትሪ እድገት በኋላ የታዩት ለውጦች በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የሃላፊነት መጓደል የታየበት ቢሆንም፣ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ የሰው ልጅ፣ ሃላፊነቶችን ተቀብሎ፣ የሚደርስበትን ችግር ለመቋቋም እጁን የሚዘረጋ ወገን እንዲኖር የሚያደርጉ ምክንያቶች መኖራቸውን በግልጽ እንመለከታለን።

በታማኝነት፣ ሃላፊነት በተሞላበት እና በድፍረት በመነሳሳት፣ እውቀታችንንም በመጠቀም፣ ጤናማ፣ ይበልጥ ሰብዓዊ፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ፣ ኤኮኖሚን ለሰው ልጅ ጥቅም የሚያውል፣ ሰላምን የሚገነባ እና አካባቢን ከጉዳት የሚከላከል ልዩ የእድገት መንገድ ወይም አቅጣጫ ሊኖር ይገባል።

የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ከሥነ ምግባር ፣ ከቅንነት እና ማህበራዊ ፍትህ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት አለው። አሁን የምናየው የአካባቢ መመናመንም በየዕለቱ ከሰብዓዊ፣ ከሥነ ምግባር እና ከማሕበራዊ ኑሮ ብልሹነት ጋር ግንኙነት አለው። ይህ ታዲያ የእኛን የፍጆታ እና የምርት ሞዴሎች ትርጉም ፣ የትምህርት እና የግንዛቤ ሂደቶችን፣ ከሰው ልጆች ክብር ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ መሥራት እንዳለብን ያሳስበናል።  ለጋራ ጥቅም የቆመ ሥልጣኔ ችግር ይታይብናል። የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ መንገዶች መኖራቸው ግልጽ ሲሆን፣ እነዚህን መንገዶች በታማኝነት፣ በድፍረት እና ሃላፊነት በተሞላ መልኩ፣ ከእያንዳንዱ ግለሰብ እና ማሕበረሰብ የኑሮ ባሕል ጋር በማዛመድ በተግባር ልናውላቸው ያስፈልጋል።

ታማኝነት፣ ድፍረት እና ሃላፊነት የሚሉ ሦስት ቃላቶችን በልባችሁ ውስጥ በመያዝ፣ የሁለት ቀን ስብሰችሁን እንድታካሂዱ በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ” በማለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት በኒውዮርክ ከተማ ከመስከረም 12-13/2012 ዓ. ም. በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ተካፋዮች መልዕክታቸውን ልከዋል።           

24 September 2019, 16:08