ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ የሚያደርግት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ የሚያደርግት ሐዋርያዊ ጉብኝት አርማ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ አፍሪቃ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የአንድነት ምልክት መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሦስቱ የአፍርቃ አገሮች የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመጀመራቸው አንድ ቀን አስቀድሞ በቫቲካን ጋዜጠዊ መግለጫ ይፋ መሆኑ ታውቋል። የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ከቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ መካከል የሰላም ጥረት፣ ከክርስቲያን ማሕበረሰብ ጋር መገናኘት፣ በሞዛምቢክ እርቅ፣ እና ለተፈጥሮ የሚሰጥ  እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚሉት ቅድሚያ የሚሰጥባቸው እንደሆነ መናገራቸውን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ፣ ቤነዴታ ካፔሊ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 31ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ሦስት የአፍሪቃ አገሮች እንደሚሄዱ ባለፉት ዘገባዎቻችን መግለጻችን ይታወሳል። ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉባቸው ሦስቱ የአፍሪቃ አገሮች፣ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ መሆናቸውን የሐዋርያዊ ጉዞአቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።  ከዚህ በፊት፣ እ. አ. አ በ2015 ዓ. ም ወደ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማደረጋቸው ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከ1980 እስከ 1988 ዓ. ም. ድረስ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተለያዩ የአፍሪቃ አገሮችን የጎበኙ መሆናቸው ይታወሳል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደስታ እና ምስጋና፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በርካታ ለውጦች እንደሚያገኙ የተንገሩት አቶ ማቴዎ ብሩኒ፣ ቅዱስነታቸው የሚጎበኟቸው አገራት የጥሪ መገኛ በስፋት ከገጠራማው አካባቢ እንደሆነ አስታውሰው ዛሬ ግን በእነዚህ አካባቢዎች አዳዲስ የድህነት ምልክቶች ይመዘገብባቸዋል ብለዋል። የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ በተዘጋጁበት ባሁኑ ወቅት፣ ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ስኬታማነት የቻሉትን በማድረግ ላይ ለሚገኙት ሁሉ ምሳጋናቸው በደስታ መግለጻቸውን ገልጸው፣ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የሕዝቦች ብዝሃነት እና ሰብዓዊ ማንነት በሚታይበት ሕዝብ መካከል በመሆኑ፣ በዚህ ሕዝብ መካከል የሚቀርብ የወንጌል ምስክርነት ውጤታማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ብለዋል። አቶ ማቴዎ ብሩኒ በማከልም ቅዱስነታቸው ውብ የሆነች የአፍሪቃን ምድር ለመርገጥ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ደስታ በተሞላበት የቪዲዮ መልዕክታቸው ገልጸዋል ብለዋል።

ወደ አፍሪቃ ከሚጓዙት መካከል አንዲት ነርስ ትገኛለች፣

የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ወደ አፍሪቃ ከሚጓዙት እና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ከሚሳተፉት መካከል፣ አንዲት የቫቲካን ጤና አገልግሎት መስጫ ተቋም ባልደረባ ነርስ የምትገኝ መሆኗን ገልጸዋል። አክለውም ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሚያደርጉባቸው አገሮች ከሚያቀርቧቸው ንግግሮች መካከል አምስቱ   በሞዛምቢክ ውስጥ በፖርቱጊስ ቋንቋ የሚቀርቡት፣ በማዳጋስካር እና በሞሪሼስ የሚያደርጓቸውን አስር ንግግሮችን በጣሊያንኛ ቋንቋ የሚያቀርቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሞዛምቢክ በቅርቡ የታየው ሰላም፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሂደት አንድ በአንድ የተመለከቱት የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፣ በቅርቡ በሞዛምቢክ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አስታውሰው ለዚህ የሰላም ስምምነት፣ ተስፋን ሳይቆርጡ ከረጅም ዓመታት ወዲህ ልዩ ልዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መሪዎችን በማደራደር ትልቅ ሚናን የተጫወቱትን እና በቅርቡ ለካርዲናልነት ማዕረግ የታጩትን የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር የበላይ ተንከባካቢ እና በኢጣሊያ የቦሎኛ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ማቴዎ ዙፒን አመስግነዋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ዜና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሞዛንቢክ የሚያደርጉትን ጉብኝት በተመለከተ ከሬዲዮ ቫቲካን ጋር ቆይታ ያደረጉት አባ ጆርጅ አጉስቶ እንደ ገለጹት ለበርካታ ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትሰቃይ ለነበርች ለሞዛንቢክ፣ ቅዱስነታቸው የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቷ ሕዝቦች መካከል የእርቅ እና የይቅርታን መንፈስ እንደሚፈጥር ገልጽዋል። በሞዛንቢክ ላለፉት 15 ዓመታት ያህል የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ በርካቶቹን ለአካል ጉዳት የዳረገ፣ ለዚህ አደጋ ከተዳረጉት መካከል ብዛት ያላቸው ሕጻናት፣ አረጋዊያን እና ሴቶች የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል። በዚህ ጦርነት ምክንያት ከ4 ሚልዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸው፣ ቤት ንብረታቸውን ያጡበት እና በአጠቃላይ አውዳሚ እና ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ መሆኑ ታውቋል። ይህ የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቂያን ያገኝ ዘንድ፣ ሙሉ እርቅ እና ሰላም ይወርድ ዘንድ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት አዎንታዊ ገጽታ እንደሚኖረው፣ መላው የአገሩ ሕዝብ ታላቅ ተስፋን አድርጎ የሚጠባበቅ መሆኑ ክቡር አባ ጆርጅ አጉስቶ መግለጻቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በቤይራ ከተማ ከምዕመናን ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት፣

የሞዛምቢክ ሁለተኛዋ እና ሰፊ ከተማ የሆነች የቤይራን ከተማን ቅዱስነታቸው መጎብኘት ቢፈልጉም ከወራት በፊት ከደረሰባት የውቅያኖስ መናወጥ አደጋ ለማገገም የመልሶ ማቋቋም ሥራ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ማቴዎ ብሩኒ ቅዱስነታቸው የቤይራ ከተማን እና የአካባቢው ምዕመናንን፣ ጉብኝታቸውን በሚያካሂዱባቸው በሌሎች አካባቢዎች የሚያገኟቸው መሆኑን ገልጸዋል። በሌላ ወገን ቅዱስነታቸው ከቦይነስ አይረስ ጋር ወዳጅነትን እንዲመሰርቱ ካገዙት በሞዛምቢክ የክሳይ ክሳይ ከተማ ተወካዮች ጋር በማፑቱ በሚገኝ የቅድስት መንበር ኤምባሲ ውስጥ የሚገናኙ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአደጋው ከተረፉት ቤተሰቦች ጋር የሚደረግ ግንኙነት፣

ማዳጋስካር ካለፈው መጋቢት ወር 2010 ዓ. ም. እስከ ዘንድሮ መጋቢት ወር 2011 ዓ. ም. ድረስ አልፍ አልፎ በተከሰተው የውቅያኖስ መናወጥ አደጋ፣ 1, 200 ሰዎች የሞቱባት መሆኑ ሲነገር፣ ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከዚህ አደጋ የተረፉ የቤተስብ አባላትን በአንታናናሪቮ ከተማ በሚገኝ የቀርሜሎሳዊያት ገዳም ውስጥ የሚያገኟቸው መሆኑን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪቃ የሚያደርጉት የአሁኑ ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ በሰላም እና በቸርነት፣ መጽናናትንም በሚሰጡ መልዕክቶች የታገዙ መሆናችውን፣ የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫቸው አስታውቀዋል። 

03 September 2019, 16:07