ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በታይላንድ እና በጃፓን ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተዘጋጀ አርማ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በታይላንድ እና በጃፓን ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተዘጋጀ አርማ፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በታይላንድ እና በጃፓን የሚያደርጉ መሆናቸው ተገለጸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከህዳር 9 – 16/2012 ዓ. ም. ድረስ ወደ ሁለቱ የእሲያ አገሮች ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉ መሆናቸው ተገለጸ። ቅዱስነታቸው ወደ እነዚህ ሁለቱ አገሮች መጥተው ሐዋርያዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ የሁለቱም አገሮች መንግሥታት እና ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ግብዣ ማቅረባቸውን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ዛሬ ይፋ ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ ሁለት አገሮች ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ከቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በኋላ ሁለተኛ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ፣ ኢዛቤላ ፒሮ የላከችልን ዘገባ እንደሚያመለክተው ታይላንድ እና ጃፓን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመቀበል ዝግጅት ላይ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከህዳር 10 – 13/2012 ዓ. ም. በታይላንድ የሚያደርጉ ሲሆን ቀጥለውም ከህዳር 13 – 16 ድረስ በጃፓን የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በጃፓን በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ቶኪዮን፣ ናጋሳኪን እና ሂሮሺማን የሚጎበኙ መሆናቸውን ዘገባው አክሎ አስታውቋል።

ታይላንድ፣ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እና ልኡካን፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በታይላንድ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ቃል አድረገው የመረጡት “የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እና ልኡካን” የሚል ሲሆን ይህም በታይላንድ፣ ሲያም በተባለ አካባቢ ከ350 ዓመት በፊት ልዩ ሐዋርያዊ አስተዳደር የተመሠረተበትን ዕለት ለማስታወስ የታሰበ መሆኑ ታውቋል። በታይላንድ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተዘጋጀው አርማ፣ ቅዱስነታቸው የታይላንድን ሕዝብ ሲባርኩ፣ በአርማው የተካተተው ሌላው ምስልም የወንጌል አገልግሎት ስርጭትን እና የቅድስት ስላሴን እገዛን ለመግለጽ፣ ሶስት በነፋስ የሚገፉ ጨርቆችን የያዘ፣ የዛፍ ምልክት ያለበት ጀልባ ሲሆን ሌላው ለወንጌል ስርጭት የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ድጋፍ መኖሩን የሚያሳይ የእጅ ምስል የተካተተበት መሆኑ ተመልክቷል። በተጨማሪም የታይላንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለተቀሩት የእስያ አገሮች የወንጌልን መልካም ዜና የምትመሠክር አገር መሆኗን የሚገልጽ የመስቀል ምልክት መኖሩ ተመልክቷል።

እሲያ ሰፊ እና የብዙ አገሮች አህጉር ናት፣

የእስያን አህጉር ስፋት፣ የባሕሎች እና ሕዝቦች ብዝሃነት የሚታይባት መሆኑን በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አምና በጥር ወር ላይ ለእሲያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት በላኩት መልዕክት መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን በውቅቱ በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ በተካሄደው የካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ላይ ለመገኘት ከቅድስት መንበር የእምነት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት የልኡካን ቡድን ወደ ባንኮክ መሄዱ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባንኮክ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ለተገኙት የእስያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በላኩት መልዕክታቸው በሐይማኖት፣ በቋንቋ እና በባሕል ልዩነት በስፋት የሚታወቅ የእስያ ካቶሊካዊ ምዕመናን በሕብረት ሆነው ካቶሊካዊ እምነታቸውን ለመጋራት የሚያስችላቸውን ዘዴዎች በመጠቀም በዛሬው ዓለማችን የወንጌል ምስክርነትን እንዲያቀርቡ አደራ ማለታቸው ይታወሳል።

ጃፓን፣ ለእያንዳንዱን ሕይወት ከጥቃት ይከላከል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ጃፓን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የጋራ መኖሪያ በሆነች ምድራችን የሚገኙትን ፍጥረታት የመንከባከብ እና የመጠበቅ ሃላፊነትን የሚመለከ መሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ጃፓን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ በምድራችን ለሚገኝ እያንዳንዱ ፍጥረት አስፈላጊው እንክብካቤን በማድረግ ከጥፋት ለመከላከል፣ ክርስቲያኖች ከፍጥረት ጋር በጸሎት እንዲገናኙ በማለት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል። በእርግጥም የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት በሰው ልጅ ክብር ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በኒውክሌር መሣሪያ ምርቷ ጃፓን ልታስከትል የምትችለውንም ጥፋት ያገናዘበ መሆኑ ታውቋል።  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በጃፓን ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተዘጋጀው አርማ ጃፓን የቤተክርስቲያን ምስረታ ወቅት መስዋዕትነትን የከፈሉ ሰማዕታትን የሚያስታውስ ሲሆን ዓርማው የተሳለባቸው ቀለማት እነዚህም የሰማያዊ ቀለም ነበልባል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መላውን የሰው ልጆች እንደምታቅፍ የሚያሳይ፣ የአረንጓዴ ቀለም ነበልባልም የጃፓን የተፈጥሮ ሃብትን የሚያመላክት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በጃፓን የሚደረገው የተስፋ ወንጌል ብስራትን የሚያመለክት መሆኑ ታውቋል። በቀይ ቀለም በጸሐይ ቅርጽ የተመለከተውም እያንዳንዱን ፍጥረት የሚያካትት የፍቅር ምልክት ሲያመላክት በተጨማሪም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ሲሰጡ የሚያሳይ ምስል ያለበት መሆኑ ተመልክቷል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልካም ምኞት፣

በጎርጎሮሳዊው መስከረም 12 ቀን 2018 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከ20 ዓመት በፊት በጃፓን ከተቋቋመ ድርጅት አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት፣ ማንቾ ኢቶ የተባለ ጃፓናዊ ወጣት በኢየሱሳዊያን ማሕበር አባላት እገዛ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1500 ዓ. ም. ወደ አውሮጳ መምጣቱ የተነገራቸው ሲሆን ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግርም ጃፓንን ለመጎብኘት ያላቸውን ምኞት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው “ጊዜውም ሩቅ አይሆንም” ማለታቸው ይታወሳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 September 2019, 16:50