ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሞዛምቢክ የታየው ሰላም እንክብካቤ የሚያሻው መሆኑን አስገነዘቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ፣ ለከፍተኛ የአገር ውስጥ ባለስልጣናት፣  ለውጭ አገራት ዲፕሎማቲክ አካላት እና ለሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች ባሰሙት ንግግር፣ ሰላም እንክባካቤ ካልተደርገለት በቀላሉ ሊጠፋ የሚችል መሆኑ አስረድተዋል። ሞዛምቢክን እንድዲጎበኙ ከአገሩ ፕሬዚደንት በኩል ለቀረበላቸው ግብዣ እና ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በተፈጥሮ ሃብት የታደለውን የአፍሪቃ ምድር ላይ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ከፍተኛ ደስታን የሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ለመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ለፓርላማ አባላት፣ ለተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶች፣ ለሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች በሙሉ የከበረ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለወደ ፊት ሰላም እና እርቅ ልቡት ለከፈተው መላው የሞዛምቢክ ሕዝብ በተወካዮቻቸው በኩል ሰላምታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በማስከተልም የውቅያኖስ ላይ አውሎ ነፋስ ባስከተለው ከፍተኛ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን በርካታ ቤተሰቦች አስታውሰው፣ በዚህ አደጋ ምክንያት አሁንም ቢሆን በችግር ላይ የሚገኙትን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ከፍተኛ ጉዳት ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች መድረስ የማይችሉ መሆናቸውን ገልጸው ነገር ግን መላው ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ ከእርሳቸው ጋር በመተባበር፣ ስቃዮቻቸውን እና ችግሮቻቸውን በመጋራት አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። ሌሎች ማሕበራዊ ተቋማትም በሕዝቡ ላይ የደረሰውን ከባድ መከራ በመገንዘብ፣ መልሶ በማቋቋም ረገድ  የበኩላቸውን ጥረት የሚያደርጉበትን ሃይል እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው በጸሎት የሚጥይቁ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው የምስጋና ንግግራቸውን በመቀጠል፣ በቅርቡ ሞዛምቢክን ባጋጠመው የተፈጥሮ አደጋ ሆነ ከርጅም ዓመታት ጀምሮ ሲያካሂድ ከነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት እና አመጽ የሚወጣበት ብቸኛው አማራጭ ሰላምን እና እርቅን በማስፈን መሆኑን በመገንዘብ፣ ለዚህም የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ለሚገኝ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የሰላምን እና የእርቅን አስፈላጊነት በመገንዘብ፣ በአገሪቱ ሲካሄድ የቆየውን እና የበርካታ ሰው ሕይወት የጠፋበትን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም በቅርቡ በመንግሥት እና በተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አስታውሰው ይህም እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1992 ዓ. ም. በሮም ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በሞዛምቢክ ውስጥ ከፍተኛ ውድመትን ያደረሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ያበቃ ዘንድ፣ ከጎርጎሮሳዊያኑ 1992 ዓ. ም. ጀምሮ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጥረቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካም ፍሬዎችን ማስገኘታቸውን ገልጸዋል። እነዚህ መልካም ፍሬዎች የወደፊት መልካም ሕይወት ተስፋ በመሆን፣ የሞዛምቢክ ሕዝብ ከአመጽ ይልቅ ሰላምን በመምረጥ፣ የአንድ አገር ወንድሞች እና እህቶች በመሆን ለተመሳሳይ ግብ ጥረት እንዲያደርጉ አግዟል ብለዋል። “ከልብ ከተነሱ ሰላምን ማምጣት ይቻላል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ “ሃይልን ለመጠቀም ወይም አመጽን ለማካሄድ የሚረዳ ድፍረት ሳይሆን በሰላም አብሮ በመኖር የጋራ እድገትን ለማምጣት የሚያገለግል ድፍረት ያስፈልጋል” በማለት፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ1973 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የሰላም ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉትን መልዕክት አስታውሰዋል።

“የሞዛምቢክ ሕዝብ ብዙ የስቃይ እና የሐዘን ሕይወት አሳልፏል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ያም ቢሆን በመካከላችው ያለው ሰብዓዊ ወንድማማችነት በጥላቻ እና በአመጽ እንዲጠፋ አልፈቀዱም ብለዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ እንደ ጎርጎሮሳዊው 1988 ዓ. ም. ወደ ሞዛምቢክ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በወቅቱ ባሰሙት ንግግር “በርካታ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት በመጠለያ፣ በበቂ ምግብ እና ውሃ፣ በትምህርት እና በጤና አገልግሎት እጥረት፣ በማምለኪያ ሥፍራ እጥረት፣ በርካታ አካባቢዎች የጦርነት አውድማ በመሆናቸው የተነሳ የእርሻ መሬት መጥፋት ምክንያት ብዙ መከራ ደርሶባችኋል፤ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብም ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል ከመኖሪያ አካባቢው እንዲፈናቀል ተግድዷል፤ ሌሎች ደግሞ ወደ አጎራባች አገሮች ተሰድደዋል፤ ይህን መከራ እና ጭንቀት የበዛበትን አስከፊ ኑሮን በመመልከት አመጽን በማውገዝ ሰላምን መፈለግ ያስፈልጋል” በማለት እንደ ጎርጎሮሳዊው 1988 ዓ. ም. የሞዛምቢክን ፕሬዚደንት በጎበኙበት ወቅት የተናገሩትን አስታውሰዋል።

ካለፉት በርካታ ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት እያንዳንዱ የአገሩ ዜጋ ለሰላም ያለውን ጥረት በተግባር መግለጽ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ፣ “ሰላም በድንጋዮች መካከል እንደሚበቅል ተሰባሪ አበባ ነው” በማለት በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ. ም. ያስተላለፉትን ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን መልዕክታቸውን አስታውሰዋል። በመሆኑም በምድራችን ሰላምን ለማምጣት በግትርነት ሳይሆን በመልካም ዓላማ እና ቆራጥነት በመነሳሳት፣ ብልህነትን በተከተለ መንገድ  ሰላምን እና እርቅን ማስፈን ያስፈልጋል እንጂ ጥፋትን የሚያስከትል ዓመፅን ማካሄድ አያስፈልግም ብለዋል።

“እውነተኛ ሰላም ተገኘ” ማለት የአመጽ እና የጦርነት መወገድ ብቻ ሳይሆን የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን፣ በተለይም ትልቅ ሃላፊነት የተጣለብን ሁላችን፣ ብዙን ጊዜ በሕዝቦች መካከል ዝቅተኛ ትኩርት የሚሰጠውን የሰው ልጅ ክብር በማስጠበቅ እና ዜጎችም በጋራ ሆነው ለሰብዓዊ ክብራቸው ደህንነት መቆም እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ማሕበራዊ ጥቅሞችን በጋራ ለመካፈል ዝግጁዎች ሆነን ካልተገኘን ለአመጽና ለጦርነት መልካም አጋጣሚዎች ይከፈታሉ ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም ዞሮ ዞሮ ለማሕበራዊ እድገት እንቅፋት ይሆናል ብለዋል። አንድ ማሕበረሰብ በብሔራዊ ወይም በዓለም አለም አቀፍ ደረጃ የተረጋጋ ካልሆነ ምንም ዓይነት የፖለቲካ እቅድ ተግባራዊ ሊሆኑ አይችልም፣ ለማሕበራዊ ሕይወትም ዋስትና የለም ብለዋል።

የሰላም መኖር የሞዛምቢክን እድገት በተለያዩ መንገዶች እውን አድርጎታል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አገሪቱ በትምህርት እና በጤና ዘርፍ የተደረገው መልካም ለውጥ ምስክር ይሆናል ብለዋል። በመሆኑም ማሕበራዊ ተቋማትን በማጠናከር፣ መዋቅሮቻቸውን በማሳደግ፣ በዜጎች መካከል የመገለል ስሜት እንዳይታይ፣ በተለይም ከአገሩ ሕዝብ መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወጣቱ ትውልድ ትኩርት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ወጣቶች የዚህ አገር የወደ ፊት ተስፋ ብቻ ሳይሆኑ የዛሬውም ተስፋ በመሆናቸው፣ በተሰጣቸው የተፈጥሮ ችሎታ ተጠቅመው የወደፊት ሕይወታቸውን ወደ መልካም አቅጣጫ ሊመሩ ፍላጎት አላቸው ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች ማሕበራዊ አንድነትን እና መግባባትን ለማምጣት የሚያስችል ሃይል ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የሰላም ባሕልን ለመገንባት ቀጣይነት ያለው የአዳዲስ ትውልዶች ጥረት ሊታከልበት ያስፈልጋ በማለት ንግግራቸውን ያሰሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ ባሕሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ግልጽ በማድረግ፣ እርስ በእርስ በመቻቻል አንድ የሚያደርጋቸውን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል። ወደዚህ ደረጃ እና ወደ ጋራ ግብ ለመድረስ የሚያግዙ መንገዶችን ለይቶ ማወቅ፣ የግል ጥቅምን ከማስቀደም ይልቅ ለማሕበራዊ እድገት ቅድሚያን መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተው፣ ይህን ያመቻቹ ከሆነ ለሌሎች ሰዎች በሚቀርቡ አገልግሎቶች በመታገዝ አገርን ወደ መልካም ደረጃ ማድረስ የሚያስችል እውነተኛ ሃብት አለ ብለዋል።

ሰላም፣ የምንኖርባትን ምድራችን ተመልሰን እንድንመለከት ያግዛል ያሉት ቅዱስነታቸው ለምንኖርባት የጋራ ምድራችን ትኩርትን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሞዛምቢክ በትልቁ የታደለች አገር ናት ያሉት ቅዱስነታቸው ከፈጣሪ የተገኘውን የተፈጥሮ ጸጋ የሞዛምቢክ ሕዝብ የመንከባከብ እና የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት ብለዋል። የሰላምን ባሕል በሞዛምቢክ ማሳደግ፣ ዘላቂ ምርታማነትን እና የጋራ እድገትን ማረጋገጥ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው የሞዛምቢክ ሕዝብ ከራሱ አልፎ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ወንድማዊ ግንኙነቶችን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመጨረሻም ለአገሩ ፕሬዚደንት፣ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ለፓርላማው አባላት፣ ለዲፕሎማቲካ አካላት እና ለሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች በሙሉ “እውነተኛ ሰላምን እና እርቅን ለማምጣት የሚያግዙ መንገዶችን በማበጀት፣ የልጆቻችሁን የወደ ፊት መልካም ተስፋን ማሳየት ያስፈልጋል” ብለው፣ በሞዛምቢክ በሚያደርጉት ቆይታ ከሌሎች ብጹዓን ጳጳሳት እና በአገሩ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን  ጋር በመሆን በሞዛምቢክ ዘላቂ ሰላም እና እርቅ እንዲወርድ በጸሎት የሚተባበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
05 September 2019, 17:53