ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የአፍሪቃን ጉዞ ሲጀምሩ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የአፍሪቃን ጉዞ ሲጀምሩ፣ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ 31ኛውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ዛሬ ጀመሩ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 31ኛውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን፣ በሦስቱ የአፍሪቃ አገሮች ለመጀመር ዛሬ ጠዋት ከቫቲካን ከተማ መነሳታቸውን የቫቲካን ዜና ክፍል ይፋ አድርጓል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት ወደ አፍሪቃ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ለመጀመር ከቫቲካን ከመነሳታቸው በፊት አት ፖንቲፈክስ በሚለው የቲዊተር ድረ ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክታቸው “የሁላችን አባት የሆነው እግዚአብሔር በአፍሪቃ ምድር ብቸኛውን የዘላቂ ሰላም ተስፋ የሆነውን የወንድማማችነት እርቅ እንዲያወርድን በሕብረት ሆነን እንጸልይ” በማለት አሳስበዋል። ወደ ሞዛንቢክ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተዘጋጀው መሪ ቃል “ተስፋ፣ ሰላም እና እርቅ” የሚል መሆኑን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት ወደ አውሮፕላን ጣቢያው ከማምራታቸው አስቀድመው ከሞዛምቢክ፣ ከማዳጋስካር እና ከሞሪሼስ የተሰደዱትን 12 ስደተኞች አግኝተው ማጽናናታቸው የተገለጸ ሲሆን እነዚህ 12 ስደተኞች ባሁኑ ጊዜ በሮም ከተማ በሚገኝ አስታሊ የስደተኞች እርዳታ መስጫ ማዕከል ሆነው በቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበረሰብ በኩል እርዳታ የሚደረግላቸው መሆኑ ታውቋል።    

ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ወደ ሚጀምሩባት ወደ ሞዛምቢክ የተነሱት ዛሬ ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ ከሮም ሌዮናርዶ ዳ ቪንቺ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማርፊያ መሆኑ ታውቋል። በ7,836 ኪሎ ሜትር በረራ ወቅት የተለያዩ አገራትን የአየር ክልል አቋርጠው፣ 10 ሰዓት ከ30 ደቂቃ የሚፈጅ ጉዞ ካደረጉ በኋላ በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1 ሰዓት ተኩል ላይ ወደ ሞዛንቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ የሚደርሱ መሆናቸውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል። በሚቀጥሉት ቀናትም ወደ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ በመጓዝ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዋዜማ ዕለት፣ ከዛሬ ነሐሴ 29/2011 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5/2011 ዓ. ም. ድረስ ወደ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ የሚያደርጉት 31ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት የተቃና እንዲሆን በሮም ከተማ ወደሚገኝ ወደ ታላቁ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ በመሄድ ጸሎታቸውን ማድረሳቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊትም የአሁኑን የመሰለ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው በተመሳሳይ ባዚሊካ ውስጥ ተገኝተው ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የሚያቀርቡ መሆናቸው ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ወደ ማፑቶ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች ጋር ሆነው ለቅዱስነታቸው የክብር አቀባበል የሚያደርጉት፣ በያዝነው ወር ከተቃዋሚያቸው የሬናሞ ፓርቲ መሪ ከሆኑት ከኦሱፎ ሞማዴ ጋር ታሪካዊ የሰላም ስምምነት የተፈራረሙት የአገሩ ፕሬዚደንት ክቡር ፊሊፔ ናዩዚ እንደሚሆኑ ታውቋል። ቅዱስነታቸው የክብር አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ በማፑቶ ከተማ ወደ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ መኖሪያ የሚሄዱ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ነገ ጠዋት በሞዛምቢክ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በይፋ ሲጀምሩ፣ በአገሪቱ ቤተመንግሥት ውስጥ ተገኝተው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከተለያዩ አገራት ዲፕሎማቲክ አካላት፣ ከሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ከወጣት ማሕበራት ተወካዮች ጋር የሚገናኙ መሆናቸ ታውቋል። በሞዝምቢክ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር መሠረት ነገ ሐሙስ ነሐሴ 30/2011 ዓ. ም. የከሰዓት በኋላ ውሎአቸው ከአገሩ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ከካህናት፣ ከገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ከዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና ከትምህርተ ክርስቶስ መምሕራን ጋር የሚገናኙ ሲሆን ቀጥለውም በማፑቶ ከተማ የሚገኘውን እና “ማቴዎስ 25” በመባል የሚታወቀውን የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች እና ሕጻናት እርዳታ መስጫ ማዕከልን የሚጎበኙ መሆናቸው ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 September 2019, 17:08