ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሞዛምቢክ ቤተክርስቲያን የጋራ መገናኛ መድረክ መሆን እንዳለባት አሳሰቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ትናንት ነሐሴ 30/2011 ዓ. ም. ለሞዛምቢክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ለዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና ለትምህርተ ክርስቶስ መምህራን፣ በማፑቶ የእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ማርያም ካቴድራል ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በካቴድራሉ ውስጥ ከተገኙት የቤተክርስትያን አገልጋዮች የቀረቡትን ምስክርነቶች ካዳመጡ በኋላ ባሰሙት ንግግር፣ የሞዛምቢክ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን አስጨርናቂ የጦርነት ዓመታትን እና የውስጥ ድክመቶችንም አልፋ የመጣች ቢሆንም በእግዚአብሔር ምሕረት በመሞላት ደስታዋን በመግለጽ ላይ ያለች ቤተክርስቲያን መሆኗን ተናግረዋል።

በእሳት የሚቃጠል ልብ፣

ቅዱስነታቸው በእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ በቁጥር በርካታ ሆነው ለተገኙት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ባሰሙት ንግግር፣ ወደድንም ጠላንም ጊዜው ያመጣውን ችሎ መቀበል ያስፈልጋል ካሉ በኋላ የችግር፣ የፈተና  እና የመከራ ዓመታት የሚያልፉ መሆናቸው ካወቅን ነገር ግን ያ ጊዜ ካለፈ በኋላ የምንገኝበት አዲስ ምዕራፍ ምን እንደሚመስል ማወቅ ያስፈልጋል ብለው በዚህ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የምናበረክተው የወንጌል ስክርነት  የሰዎችን ልብ በፍቅር እሳት የሚያቃጥል፣ ለክርስቲያናዊ ሕይወታቸውም አጋዥ ሆኖ የሚቀርብ መሆን አለበት ብለዋል።

ማንነትን ለይቶ ማወቅ፣

በክህነታዊ ማንነት ላይ ለደረሰው ውድቀት መፍትሄው ምንድር ነው በማለት ጥያቄአቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ መልስ ይሆናል በማለት ባቀረቡት ምሳሌ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንደገለጸው፣ በአጥማቂው ዮሐንስን እና በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ያለውን ታሪክ አስታውሰው፣ የአጥማቂው ዮሐንስ በኢየሩሳሌም መወለድ የታወጀው በቅድስተ ቅድሳት ቤተመቅደስ ውስጥ እንደነበር ገልጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው የመንደር ከተማ በሆነች በናዝሬት በምትገኛ አንዲት ደሃ ቤት ውስጥ መሆኑን አስረድተው በዚህ ከፍተኛ ልዩነት መካከል የራሳችንን ማንነት ማወቅ እንችላለን ብለዋል።

የማንነት ጥያቄን ለመመለስ፣

በክህነታዊ ማንነት ላይ ስለሚደርስ ውድቀት የየተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ አንዳንድ ጊዜ በማሕበረሰቡ ዘንድ ከምንገኝበት ታላቅ የክብር ቦታ ወርደን ቀድሞ ወደነበርንበት ዝቅተኛ ሥፍራችን እንመለሳለን ብለው ከዚህ ዝቅተኛ ስፍራም ቢሆን ወጥተን ወደ ትልቅ ሥፍራ እንድንደርስ ያድረገን የእግዚአብሔር ሃይል መሆኑን አስረድተው፣ ወደ ናዝሬቱን ምሳሌ ተመልሰው ባደረጉት አስተንትኖ ናዝሬትም ካጋጠመን የማንነት ውድቀት ወጥተን በአዲስ ሕይወት ለእረኝነት እና ለወንጌል ተልዕኮ ታጥቀን የምንነሳበት ቦታ አድርገን መመልከት እንችላለን ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ቅድስት ድንግል ማርያምን አስታውሰው ባሰሙት አስተንትኖ፣ ዝቅተኛይቱ ማርያም ልጇ ከኢየሩሳሌም ይልቅ በናዝሬት እንዲወልድ ብላ ያደረገችው ምርጫ፣ በሕይወታችን ውስጥ ከባድ ፈተና ሆነውብን እንቅፋት የሚፈጥሩትን ነገሮች አውልቀን ጥለን፣ በልባችን ውስጥ ላደረብን የአገልግሎት ሕይወት አዎንታዊ መልስ መስጠት እንድንችል መልካም ምሳሌ ይሆነናል ብለዋል።

ጥሪን ማደስ ያስፈልጋል፣

በክህነታዊ ሃላፊነት እና መልካም ተነሳሽነት ላይ ድክመት ሊታይ ይችላል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የተጠራንበትን ጥሪ በጥበብ እና በማስተዋል፣ እንደገና በማጤን፣ በክህነታዊ ማንነት ላይ የደረሰው ውድቀት በእርግጥም በመንፈሳዊነት መዳከም ከሆነ ለይቶ በማወቅ፣ የተጠራንበትን ዓላማ ለማሳካት የገባነውን ቃል በማደስ፣ ደካሞች ሆነን ሳለ ይህ ድክመታቸን በእግዚአብሔር ፊት ፍሬን የሚያፈራ ሆኖ እንዲገኝ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በናዝሬት እና በኢየሩሳሌም መካከል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ በናዝሬት እና በኢየሩሳሌም መካከል ያደረጉትን ንጽጽር በመቀጠል በሁለቱ ሴቶች በኤስልሳቤጥ እና በማርያም መካከል ያለውን ግንኙነት ተመልክተ፣ ማርያም ኤልሳቤጥን ልትጎበኛት ከልብ መወሰኗ በሁለቱ ሥፍራዎች መካከል ያለውን እርቀት በብዙ እንዳሳጠረው አስረድተው፣ የሞዛምቢክን ታሪክ በማስታወስ፣ 17 ዓመታትን ያስቆጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት እና አመጽ በሞዛምቢክ ሕዝብ መካከል ልዩነትን ፈጥሮ ምን ያሕል እንዳራራቀው አስረድተው፣ ሊከሰቱ የሚችሉ ጥቃቅን ልዩነቶችን በማስወገድ መቀራረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የባሕሎች ግንኙነት፣

በማርያም እና በኤስልሳቤጥን መካከል የተጀመረው ውይይት እና አገልግሎት ለግንኙነታቸው መልካም መንገድን እንደፈጠረላቸው አስታውሰው ባሕልን ያማከለ ስብከተ ወንጌል በሕዝቦች መካከል ግንኙነት እንዲኖር ያግዛል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከእያንዳንዱ አገር ሕዝብ ባሕል ጋር ተስማሚነት ያለው ሊሆን ይገባል ብለዋል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ብልህነት እና ድፍረት ሊኖር ይገባል ብለው ይህ ካልሆነ የቤተክርስቲያን እድገት ተግድቦ የሚቀር ይሆናል ብለዋል።

ማርያም ወደ ኤልሳቤጥ ቤት ጉዞ እንዳደረገች ሁሉ እኛም እንደ ቤተክርስቲያን ኣዳዲስ ችግሮች ያሉበትን አካባቢ የሚያደርሰንን መንገድ ማወቅ ያስፈልጋል እንጂ መከፋፈልን በሚፈጥሩ የተቃዋሚዎቻችን አስተሳሰብ ተንበርክከን መቅረት የለብንም ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሞዛምቢክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ለዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና ለትምህርተ ክርስቶስ መምህራን፣ በማፑቶ የእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ማርያም ካቴድራል ተገኝተው ያደረጉትን ንግግር ባጠቃለሉበት ወቅት እንዳስረዱት፣ የሞዛምቢክ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሮችዋን ክፍት በማድረግ ለችግሮች መፍትሄ የሚገኝባት፣ የእርስ በእርስ መከባበር ያለባት፣ የጋራ ውይይቶች የሚካሄዱባት ሥፍራ መሆን አለባት ብለዋል።

06 September 2019, 16:41