ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የሞዛምቢክ ሕዝብ ተስፋን በመሰነቅ በአንድነታችሁ ጸንታችሁ ኑሩ”!

ዛሬ በሞዛምቢክ ዋና ከተማ በማፑቶ ውስጥ በሚገኝ ዚፔቶ ስታዲዬም የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ስነ ስርዓት የፈጸሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሞዛምቢክ ሕዝብ ለሰላም ለእርቅ በርትተው እንዲሰሩ፣ ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ እና እርስ በእርስ እንዲዋደዱ አሳስበዋል። “ተስፋ፣ ሰላም እና እርቅ” ለሞዛምቢክ ሕዝብ የሚል መርሕ ቃል በመያዝ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሞዛምብክ የጀመሩት ቅዱስነታቸው መላው የሞዛምቢክ ሕዝብ ወደ ፊት የሚጠብቀውን ብሩሕ ዘመን በተስፋ እንዲጠብቅ፣ ሕብረታቸውንም ጠብቀው እንዲቆዩ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማፑቶ ስታዲዬም የቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞዛምቢክ ላደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጨረሻ ክፍል መሆኑን ከቫቲካን ዜና ክፍል የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ስቴዲዬሙ ሲደሩ በስፍራው የነበረው፣ ከ60, 000 በላይ ምዕመናን በደስታ እና በዝማሬ የተቀበሏቸው መሆኑ ታውቋል።

ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣

በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ላይ ከሉቃ. 6. ቁጥ. 27 ጀምሮ በተነበበው የወንጌል ክፍል በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው “እናንተ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ” የሚለው የወንጌል ትዕዛዝ ዛሬ ለእኛም ይነገረናል ብለዋል። የኢየሱስ የሚናገረን  የሚጠሉንን፣ የሚለያዩንን፣ የሚያዋርዱንን እና የሚክዱን ሰዎች ሳይቀር መውደድ እንደሚያስፈልግ ይናገረናል ብለዋል። ከጎርጎሮሳዊው 1977 እስከ 1992 ዓ. ም. ድረስ በእርስ በእርስ ጦርነት እና አምጽ ውስጥ የወደቀች ሞዛምቢክን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እነዚያን የስቃይ እና የመከራ፣ የአመጽ እና የጥላቻ ዓመታት ምን ይመስሉ እንደነበር መናገር የሚችሉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ አንዳንዶች ደግሞ ያ ዘመን ተመልሶ በመምጣት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገሪቱ የታየውን የሰላም ጭላንጭል ሊሄድብን ይችላል ብለው የሚሰጉ መኖራቸውን ገልጸዋል።

እርቅ እና ይቅርታ፣

ጦርነት እና አመጽ ያስከተለው ቅራኔ፣ ቁስሉም ባልዳነበት ጊዜ ውስጥ ስለ እርቅ ማውራት ወይም ምሕረትን ስለ ማድረግ መናገር ቀላል እንዳልሆነ የተናገሩ ቅዱስነታቸው ይመምን ችሎ ከማለፍ ጋር እኩል እንዳልሆነ አስረድተው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶቻችንን እንድንወድ፣ መልካምንም እንድናደርግላቸው፣ ክፉን ሳይሆን ደጉን እንድንመኝላቸው፣ እንድንባርካቸው እና እንድንጸልይላቸው ያዘናል ብለው ይህን ማድረግ ከባድ ቢሆንም ጦርነት እና አመጽ በነገሰበት ዘመን ሀገርን መገንባት፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ማሕበረሰብን መመስረት አይቻልም ብለዋል።

እርስ በእርስ ተዋደዱ፣

የምንኖርበት ዓለም የምሕረት እና የርህራሄ ልብ የደነደነበት መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለማችን የሚንጸባረቀውን የመከፋፈል እና የአመጽ ድርጊትን ማሸነፍ የሚቻለው እያንዳንዱ ሰው በየዕለቱ ለሚያጋጥመው በደል ይቅርታን በማድረግ፣ በክፉ ፈንታ መልካምን በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰላም እና ምሕረት፣

“ሰላም የነገሠበትን ዘመን እንሻለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ውስጥ እንደ ሕግ ይኑር” አስታውሰዋል። በሁለት የተለያዩ ውሳኔዎች መካከል ስንገኝ ለኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዝ በመገዛት፣ በእርሱ የፍቅር እና የምሕረት መንገድ በመመራት፣ በመካከላችን ተቸግረው የእኛን ድጋፍ ለሚጠይቁት ርህራሄን በማድረግ፣ ለፍጥረታትም አስፈላጊውን ጥበቃ እና እንክብካቤን በማድረግ የሰላምን ጎዳና መጓዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

ተስፋን ማድረግ ያስፈልጋል፣

በሦስቱ የአፍሪቃ አገሮች ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ አገር የሆነችውን የሞዛምቢክ ቆይታ ጳጉሜ 1/2011 ዓ. ም. ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የፈጸሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለተደርገላቸው መስተግዶ የአገሩን ሕዝብ በሙሉ አመስግነው፣ ከአገሪቱ ሰሜናዊ ሩቅ ክፍላተ ሀገራት ቀናት የፈጀ ጉዞን በማድረግ ወደ ዋና ከተማዋ ማፑቶ ለደረሱት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። “ተስፋ አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል” ብለው፣ ይህን ተስፋ ማንም ሊወስድባችሁ እንደማይገባ አሳስበዋል። ለመላው የሞዛምቢክ ሕዝብ ባቀረቡት ምክራቸው አንድነትን ከመጠበቅ የበለጠ ነገር የለም ብለው፣ የሞዛምብክ ሕዝብ ተከባብሮ እና ተዋድዶ ለመኖር የሚያስፈልገው እርቅ እና ሰላም ነው ብለዋል።         

06 September 2019, 19:29