ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የወጣትነት፣ የደስታ እና የወንጌል ተልዕኮ ሕይወት ይኑራችሁ”!

ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በሦስት የአፍሪቃ አገሮች፣ በሞዛምቢክ፣ በማዳጋስካር እና በሞሪሼስ ውስጥ የሚያደርጉትን 31ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በመቀጠል ወደ ሦስተኛዋ እና የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻዋ አገር ወደ ሆነችው ወደ ሞሪሼስ ተጉዘው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ማድረጋቸውን የቫቲካን ዜን አገልግሎት ባልደረባ ኤማኑኤላ ካምፓኒሌ የላከችልን ዘገባ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከማዳጋስካር ዋና ከተማ አንታናናሪቮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ትናንት ጠዋት የተነሱት ቅዱስነታቸው ወደ ሞሪሼስ ደሴት፣ ወደ ዋና መዲና ፖርት ሉዊስ፣ በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ በሁለት ሰዓት ተኩል ሲደርሱ በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በክቡር ፕራቪንድ ጁኛውት እና በፖርት ሉዊስ ከተማ ሊቀ ጳጳስ በብጹዕ ካርዲናል ማውሪስ ፒያት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል የክብር አቀባበል አበባም ተበርክቶላቸውል። በስፍራው ከነበሩት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ከሕዝባዊ ማሕበራት ተወካዮች ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰላም ንግሥት የንግደት ሥፍራ ሲደርሱ የቁምናው መሪ ካህን ከበርካታ ካቶሊካዊ ምእመናን ጋር አቀባበል አድረገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በተቀመጠላቸው የሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር መሠረት ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ከሩብ ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት መፈጸማቸው ታውቋል። በመስዋዕተ ቅዳሴው ስነ ስርዓት ወቅት እ. አ. አ. በ1970 ዓ. ም. ብጽዕናቸው የታወጀላቸው ሚሲዮናዊ፣ የብጹዕ ጃኮብ ዴዚሬ ቅዱስ አጽም በክብር ቦታ ተቀምጦ ለምዕመናን ይፋ መደረጉ ከሥፍራው የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።         

የ31ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ትናንት ጳጉሜ 4/2011 ዓ. ም. በሞሪሼስ ያካሄዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዋና ከተማዋ ፖርት ሉዊስ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰላም ንግሥት ካቴድራል ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ፈጽመዋል። ቅዱስነታቸው በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወደ 100, 000 የሚጠጉ ካቶሊካዊ ምዕመናን የትካፈሉ መሆናቸው ታውቋል። ለምዕመናኑ ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል እንደገለጹት ብጽዕና የክርስቲያኖች መታወቂያ ምልክት ነው ብለዋል።

“ብጹዓን ናቸው”፣

ስብከተ ወንጌላቸውን በብጹዓን ሕይወት ላይ ያስተነተኑት ቅዱስነታቸው፣ ብጽዕና የክርስትናችን መለያ ነው ብለው፣ “አንድ ሰው መልካም ክርስቲያን ለመሆን ምን ማድረግ አለበት”? ለሚለው ጥያቄ መሱ ግልጽ ነው ብለው ይህም እያንዳንዳችን በሕይወት መንገዳችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በማቴዎስ ወንጌል በምዕ. 5 እንደተገለጸው፣ በተራራ ላይ ስብከቱ ያስተማረውን መንገድ መከተል ነው ብለዋል።

ብጹዕ ዣክ ዴዚሬ ላቫል፣

የሞሪሼስ ሕብረት ሐዋርያ የሆነውን ብጹዕ ዣክ ዴዚሬ ላቫልን ያታወሱት ቅዱስነታቸው ይህ ብጹዕ ሰው የወንጌል ተልዕኮ ለሁሉም ሰው የሚበቃ ነው ያለውን አስታውሰው፣ ይህን ዓላማው በማድረግ የአገሩን ቋንቋ በመማር የወንጌልን መልካም ዜና ይመሰክር እንደነበር አስረድተዋል። ብጹዕ ዴዚሬ በዚህ የወንጌል ምስክርነቱ የፍቅር አገልግሎቱ ለሞሪሼስ ቤተክርስቲያን ለውጥን እና እኛም ዛሬ እንድናበርክትላት የተጠየቅነውን አዲስ የወንጌል አገልግሎት አበርክቷል ብለዋል።

የወንጌል መልዕክተኛ፣

የክርስቲያን ማሕበረሰብን ለማነቃቃት፣ የቤተክርስቲያን እድገትንም ተግባራዊ ለማድረግ የወጣት አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ወጣቶች በክርስቲያን ማሕበረሰብ መካከል ለሚያበረክቱት መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች እውቅናን በመስጠት የበለጠ እንዲሳተፋ ያስፈልጋል ብለዋል።

ወጣቶች፣

ሃሳባቸውን ወደ ወጣቶች የመለሱት ቅዱስነታቸው ባሁኑ ጊዜ የወጣቱን ሕይወት ፈተና ውስጥ የከተተ ነገር ቢኖ አንዱ ሥራ አጥነት ነው ብለው ይህም በሕብረተሰቡ መከከል ራሳቸው አሳንሰው እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል ብለዋል። ወጣቶች ለቤተክርስቲያን የተልዕኮ አገልግሎት ግንባር ቀደም ናቸው ብለው፣ ወጣቶችን በሩቁ ከመመልከት ይልቅ አብሮአቸው በመሆን ሃሳባቸውን፣ ምኞታቸውን እና ገጠመኞቻቸውን በማዳመጥ፣ እነርሱም በእግዚአብሔር የተባረኩ መሆናቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ደስተኛ ክርስቲያን፣

ሌሎችም እንዲጓዙ የተጠሩትበት የእግዚአብሔር መንገድ የተባረከ መሆኑን መግለጽ የሚችሉት ደስተኛ የሆኑ ክርስቲያኖች ናቸው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተባረከ ማለት ደግሞ ዘወትር ደስተኛ ማለት መሆኑ አስረድተው፣ ለእግዚአብሔር የታመኑት እና እርሱን ለማገልገል ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡት፣ እነርሱ እውነተኛ ደስታ ያገኛሉ ብለዋል።

በሞሪሼስ ዋና ከተማዋ ፖርት ሉዊስ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰላም ንግሥት ካቴድራል ያቀረቡትን ስብከተ ወንጌል ባጠቃለሉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ወጣቶች የክርስቲያን ሰው ሕይወት በደስታ የተሞላ መሆኑን ሲመለከቱ ለሕይወታቸው ብርታትን ያገኛሉ ብለው እነርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን በመቀበል፣ የእርሱን መንገድ በመከተል እውነተኛ ደስታን ሊያገኙ ይችላሉ ብለዋል።         

10 September 2019, 16:09