ፈልግ

ር. ሊ. ጳ.  ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ የቀረበውን መባ ሲቀበሉ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ የቀረበውን መባ ሲቀበሉ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ኢየሱስን መከተል መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን አስገነዘቡ።

በማዳጋስካር የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ዛሬ የፈጸሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ትናንት በዋና ከተማዋ በአንታናናሪቮ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ለአገሩ ካቶሊካዊ ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን አስገንዝበዋል። በሉቃስ ወንጌል ላይ አስተንትኖን በማድረግ ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ የእግዚአብሔር እቅድ ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የተናገረውን ጠቅሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ኢየሱስን መከተል እንዲሁ ቀላል አይደለም፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንታናናሪቮ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሰፊ መናፈሻ ውስጥ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፣ “እናንተም በቁጥር በርከት ብላችሁ በዚህ ሥፍራ የተገኛችሁት ኢየሱስን ለመከተል ባላችሁ ፍላጎት ተነሳስታችሁ ነው” ነገር ግን ኢየሱስን መከተል ይህን ያህል ቀላል አይደለም ብለው መስዋዕትነትንም የሚያስከፍል ነው ብለዋል። ዛሬ በተነበበው የወንጌል ክፍል ኢየሱስ የተናገረው ይህንኑ ነው ብለዋል።

የኢየሱስ የመጀመሪያ ጥያቄ፣

እርሱን ለመከተል ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄ በቤተሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት ይመለከታል ያሉት ቅዱስነታቸው ለትክክለኛ እና መልካም ማሕበራዊ ኑሮ ቤተሰብ እንደ ወሳኝ መስፈርት ሆኖ ሲቀርብ፣ ባሕላዊ ውሳኔዎችን ለማድረግ በመነሳት በማሕበረሰቡ መካከል መለያየትን በመፍጠር በመጨረሻም የዚህ ሁሉ ውጤት ወደ ሆነው መልካም አስተዳደር እጦት እና ሙስና ውስጥ መውደቅ ይመጣል ብለዋል። ኢየሱስ በግልጽ እንደተናገረው ሌሎችን እንደ ወንድም እና እንደ እህት የማይመለከት፣ ለሌሎች ሕይወት የማጨነቅ፣ ሰዎችን በዘር እና በባሕል የሚከፋፍል፣ እርሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሊሆን አይችልም ብለዋል።       

የኢየሱስ ሁለተኛ ጥያቄ፣

በስፍራው ለተገኘው በርካታ የምዕመናን ቅይጥር ስብከተ ወንጌላቸውን ያሰሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ጥያቄ ነው ባሉት ማብራሪያቸው እንደገለጹት፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከግል አጀንዳዎች፣ የርዕዮተ ዓለም አስተሳሰቦች፣ የእግዚአብሔርን ስም ከሚያሳንሱ፣ እምነትን ተገን ካደረጉት የአመጽ ድርጊቶች፣ ከመለያየት እና ብሎም መገዳደል፣ ከስደት ከሽብርተኝነት እና ከማግለል ተግባር ጋር ማመሳሰል እንደማይገባ አሳስበዋል። ኢየሱስ ከእኛ የሚፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ የቅዱስ ወንጌል መልካም ዜና ከዓለማዊ ክፉ ተግባሮች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖር ያግዛል ብለው የወንድማማችነትን እና የአንድነትን ታሪክ ለመገንባት፣ በጋራ ለምንኖርባት ምድራችን እና ለምትለግሰን ስጦታዋ ክብርን በመስጠት የሚፈጸምባትን ብዝበዛ መቃወም ያስፈልጋል ብለዋል።    

የኢየሱስ ሦስተኛ ጥያቄ፣

ኢየሱስ ከእኛ የሚፈልገው ሦስተኛው ነገር ምን እንደሆነ ያብራሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በችሎታችን በመታገዝ ከምናገኘው በረከት በላይ ከእግዚአብሔር የምናገኘው በረከት ከፍተኛ እና ዘለዓለማዊ መሆኑን በመገንዘብ፣ ሕይወትን እና ጥበብን የሰጠን እግዚአብሔር ማመስገን ይኖርብናል ብለው እነዚህ የእርሱ የጸጋ ስጦታዎች በሙሉ ወደ እኛ የደረሱት፣ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ በዕረፍት ቦታ ላይ በሚገኙ ስዎች አማካይነት ነው ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በእነዚህ ሦስተ መንገዶች አማካይነት ደቀ መዛሙርቱን ነጻ ያደርጋቸዋል ብለው የሚያጋጥሟቸውን ከፍተኛ እንቅፋቶች በማሻገር ከሐጢአት ተግዥነት ነጻ በማድረግ ራስን ችሎ ለመቆም ሃይልን ይሰጣል ብለዋል።

ለእግዚአብሔር ቦታን መስጠት፣

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በመቀጠል፣ እነዚህን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ የሚፈልጋቸውን በማሟላት እና ቅድሚያን በመስጠት፣ እግዚአብሔር የሕይወታችን ማዕከል እንዲሆን ለእርሱ ቅድሚያን እና ሥፍራን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። በምድር ላይ ሰዎች እንዲሰቃዩ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መልዕክት ዓላማም ሰዎች በገዛ ራሳቸው የሚያመጡትን መከራዎች በሙሉ መዋጋት እና መከላከል እንደሚያስፈልግ ይመክረናል ብለዋል። በክርስቲያንነታችን የእርዳታ እጆቻችንን መዘርጋት እንጂ የአመጽ እና የጦርነት መሣሪያን መዘርጋት የለብንም ብለው ይህን የምናደርግ ከሆነ ኢየሱስም አጋዣችን ይሆነናል ብለዋል።

የእግዚአብሔርን እቅድ የራሳችን እናድረገው፣

የኢየሱስ ክርስቶስ ትዕዛዛት ሸክም እየቀለሉ የሚመጡት ከውጤቱ የሚመጡትን ደስታዎች ማጣጣም ስንጀምር ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ምክንያቱም እንደጠፋ በግ ወይም እንደ አባካኙ ልጅ ከጠፋንበት ስፍራ ሊያወጣን የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለዋል። ትናንት በዋና ከተማዋ በአንታናናሪቮ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ስነ ስርዓት ላይ ያሰሙትን ስብከተ ወንጌል በደመደሙበት ወቅት እንደገለጹት፣ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ የሚፈልገውን ፈጽማችሁ ከተገኛችሁ በአገራችሁ ማዳጋስካር ቅዱስ ወንጌል የሕይወታችሁ አካል ስለሚሆን የበኩላችንን ጥረት እናድርግ” ብለው “የእግዚአብሔርን እቅድ የራሳችን እቅድ እናድረገው” ብለዋል።

09 September 2019, 18:25