ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የማዳጋስቻርን ወጣቶች ባገኙበት ወቅት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የማዳጋስቻርን ወጣቶች ባገኙበት ወቅት፣ 

“ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየንን የፍቅር እና የእምነት መንገድ ከሌሎች ጋር መጋራት ይኖርብናል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ 31ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሦስት የአፍሪቃ አገሮች ውስጥ በማድረግ ላይ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በማዳጋስካር ባደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅትም ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከውጭ አገራት ዲፕሎማቶች፣ ከሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች፣ ከሐይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ከካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ከገዳማዊያን እና ገዳማዊያት፣ ከወጣቶች እና በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከሚመሩ የዕርዳታ መስጫ ተቋማት ጋር ተገናኝተው ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በማዳጋስካር ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ከተለያዩ ማሕበራዊ እና መንፈሳዊ ተቋማት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ንግግር ያደረጉላቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል የወጣቱ ማህበረሰብ ይገኝበታል። በማዳጋስካር ዋና ከተማ አንታናናሪቮ ውስጥ በሚገኝ የሀገረ ስብከቱ መዝናኛ ካምፕ ውስጥ፣ ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011 ዓ. ም. ከወጣቶች ጋር ተገናኝተው ንግግር አድርገውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማዳጋስካር ዋና ከተማ አንታናናሪቮ ለወጣቶች ያደረጉት ንግግር ትርጉም የሚከተለው ነው፥

“ለተደረገልኝ የመልካም አቀባበል ንግግር ብጹዕነትዎን አመሰግላለሁ። ከውብ የማዳጋስካር ደሴት አራቱ አቅጣጫዎች ሩቅ መንገድ ተጉዛችሁ በዚህ ሥፍራ ለተገኛችሁ ወድ ወጣቶች በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ  ጠርቶን በሕብረት ለመጸለይ መገናኘታችን ደስ አሰኝቶኛል። ላቀረባችሁት የመዝሙር አገልግሎት እና ላሳያችሁን ባሕላዊ ውዝዋዜ አመሰግናችኋለሁ። በማዳጋስካር በማደርገው ሐኣዋርያዊ ጉብኝቴ እጅግ መደሰታችሁን ሰምቼአለሁ።

በተስፋ እምነትን ለማግኘት ያደረጋችሁትን ጉዞ ወጣ ውረዶች በዚህ ስፍራ ተገኝተው ያካፈሉንን ወጣት ሮቫን እና ወጣት ኤሊሳን አመሰግናለሁ። ሕያው እና በማደግ ላይ የሚገኝ እምነት ያላቸውን እነዚህን ሁለት ወጣቶች ማግኘት ምን ያህል መልካም ነገር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁል ጊዜ ልባችንን በማነሳሳት በእምነት የምንጓዝበትን መንገድ ያሳየናል። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በፍቅር ለማደግ የሚፈልጉ ከሆነ ዝም ብለው መቀመጥ ወይም ማጉረምረም የለባቸውም። ጌታ እንደሚደግፋቸው እና አብሮአቸው እንደሚጓዝ እርግጠኛ በመሆን በቁርጠኝነት ወደ ፊት መራመድ ይኖርባቸዋል።

እያንዳንዱ ወጣት ጌታን ከልቡ እንዲፈልግ ብዬ የማስበው ለዚህ ነው። በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያቀረበውን ጥያቄ ታስታውሳላችሁ? የመጀመሪያው ጥያቄ፣ በዮሐ. 1.38 ላ እንደምናገኘው፣ ‘ምን ትፈልጋላችሁ’ የሚል ነበር። ዓለም ሊወስድብን የማይችለውን፣ እኛም የተፈጠርንለትን ታላቅ ደስታ እንደምንፈልግ ኢየሱስ ያውቃል። እያንዳንዳችሁ በተለያየ መንገድ ቢትገልጹትም በመፈለግ ላይ ያላችሁት ደስታ ማንም ሊወስድብን የማይችለው እውነተኛ ደስታ ነው።   

ወጣት ሮቫ፣ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለመጎብኘት ምኞት እንዳደረብህ ነግርህናል። ይህ ምኞትህ እውን የሆነውም ሐዋርያዊ አገልግሎቱን ለእስረኞች በማበርከት ላይ የሚገኝ ካህን ማገዝ በጀመርክበት እና ቀስ በቀስም የአንተ የግል ተልዕኮ ሆኖ ባገኘህበት ወቅት ነበር። ሕይወትህ የተልዕኮ ሕይወት መሆኑን ተገንዝበሃል። ይህን የተልዕኮ ሕይወት ያገኘሄው፣ ዓለም ራሱን ለወንጌል በማስገዛት ለሕይወት ተስማሚ ሆኖ እንዲገኝ ከሚያደርግ  ከእምነት ነው። ለሌሎች ያደረግሄው መልካም ተግባር አንተን ለውጦሃል። ለሌሎች ያለህን አመለካከት ለውጦታል። ይበልጥ ፍትሃዊ እንድትሆን አድርጎሃል። ጌታ ካንተ ጋር ሆኖ ዓለም ሊወስድብህ የማይችለውን ደስታ እንደሰጠህ ለማወቅ ችለሃል።

ሮቫ፣ በተልዕኮህ መካከል የተማርከው ነገር ቢኖር፣ ጌታ በስማችን እንደሚጠራን፣ አንተም ለሰዎች የማይገባቸውን ስም ከመስጠት ይልቅ በስማቸው መጥራት እንዳለብህ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢአታችንን እና ስህተቶቻችንን አልቆጠረብንም። በምሕረት ዓይኖቹ ነው የሚመለከተን። ሰይጣንም ስማችንን ያውቀዋል ነገር ግን የሚፈልገው ሳንለወጥ በሃጢአት ታስረን እንድንቆይ ነው። ከዚህ በተለየ መልኩ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስታውሰን በእርሱ ዘንድ ምን ያህል ወድ መሆናችንን እና የእርሱ ተልዕኮ ፈጻሚዎች መሆናችንን ነው። 

ወጣት ሮቫ፣ በተልዕኮ መካከል የተማርከው እያንዳንዱ ሰው ልዩ መሆኑን እና ከእያንዳንዱ ሰው በስተጀርባ የግል ታሪክ እንዳለው ነው። ለበርካታ ሰዎች አስቸጋሪ የሆነውን እና ሊተውት ዓመታትን የሚፈጅ አንድ ነገር ካንተ ላይ በቀላሉ አውልቀ ጥለሃል። ይህም በሰው ላይ የማይገባ ትችት ማቅረብን ነው። እስር ቤት ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ክፉ በመሆናቸው ሳይሆኑ ክፋ ምርጫ ማድረጋቸውን ተገንዝበሃል። የተጓዙበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን አውቀው ከዚያ መንገድ ተመልሰው በትክክለኛው መንገድ ለመጓዝ ይፈልጋሉ።

ይህም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን ወዳጅነት ሊያስገኝልን የሚችለውን መልካም ስጦታ ያስታውሰናል። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ውስጥ መሆኑን እና ፈጽሞ እንደማይተወን፣ ከእርሱ የራቅን ቢመስለንም ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከእኛ ጋር በመሆን ለእርሱ ተልዕኮ እንድንቆም፣ የእርሱን ስጦታ በሚገባ እንድናውቅ ይጋብዘናል።

እንደምናውቀው እና ከግል ተሞክሯችን እንደምንረዳው፣ ጊዜያዊ ደስታን በሚሰጡ ነገሮች በመታለል ወደተመኘነው ሥፍራ ሳንደርስ መንገድ ላይ እንቀራለን። ግማሽ መንገድ ላይ የሚያስቀር የሐሰት ተስፋን ተጠንቀቁ። በወጣትነት እድሜ ውስጥ ስንገኝ በጊዜያዊ ደስታ በቀላሉ ልንታለል ስለምንችል እና መጨረሻውም ስለማያምር መጠንቀቅ ያስፈልጋል።                             

ነገሮች ሳይሳኩ ሲቀሩ፣ ለዕለታዊ ሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማሟላት ሳንችል ስንቀር፣ ወይም ትምህርታችንን ማገባብደድ ሳንችል ስንቀር፣ ወይም ሥራ ሳናገኛ ስንቀር፣ ወይም ማሕበራዊ ፍትህ ሲጓደልብን፣ ባጠቃላይ የተረጋጋ ሕይወት ሳይኖረን ሲቀር፣ አሁንስ ምንም ማድረግ አልችልም፣ ተስፋም የለውም በማለት ታስቡ ይሆናል። ይህን የመሰለ ሃሳብ ሲገጥማችሁ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

ይህ አስተሳሰብ እና አካሄዳችሁ ትክክል እንዳልሆነ አስቀድሞ የሚነገራችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። መራመድ ያለባችሁ መንገድ ይህ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ስለሆነ እናንተም በሕይወት እንድትኖሩ ይፈልጋል። እርሱ የተሰጣችሁትን እውቀት እና ችሎታ እንዲሁም ምኞታችሁን እና ሕልማችሁን ተግባራዊ እንድታደርጉት ይፈልጋል። እርሱ እያንዳንዳችንን በስማችን በመጥራ ተከተለኝ ይለናል። በሚያታልሉን ነገሮች ተደናቅፈን እንድንቀር ሳይሆን ካሁን ጊዜ ጀምሮ የእርሱ ደቀ መዛሙርት እና መልዕከተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። መልካም ሕይወትን ለመኖር ብላችህ የምታደርጉትን ጥረት በማደናቀፍ፣ እላያችሁ ላይ ስንፍናን በመጫን ወደ ኋላ የሚጎትታችሁን ነገር ችላ እንድትሉት ይፈልጋል። ከኢየሱስ ጋር ከተጓዛችሁ በየቀኑ አዳዲስ መንገዶችን እና አቅጣጫዎችን የምታገኙበት ዕድል አላችሁ። እርሱ የቀድሞ ማንነታችንን ለውጦ የተልዕኮ ሕይወትን እንድንኖር ያደርገናል። እርሱ ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ይህም ፍርሃትን አስወግደን እርሱ የሚለንን ተግባራዊ እንድናደርግ ነው።

የአገራችሁ የማዳጋስካር እና የቤተክርስቲያናችሁ ተስፋዎች እናንተ ናችሁ። ኢየሱስ ክርስቶች እምነት ጥሎባችኋል። ከዚህም በተጨማሪ እናንተም በራሳችሁ በርካታ ችሎታችሁ እና እውቀታችሁ እምነት እንዲኖራችሁ ይጠይቃል። እርስ በእርሳችሁ በመተጋገዝ፣ ከእርሱ ጋር በመተባበር፣ የእርሱን እገዛ በመጠየቅ በሕይወታችሁ መልካም ታሪክ እንድታስመዘግቡ፣ እንደ ወጣት ሮቫ ለሚያጋጥማችሁ ችግሮች ክርስቲያናዊ ምላሽን እንድትሰጡ ይፈልጋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዓለምን እንድንገነባ ጠርቶናል። በመሆኑም በደስታ እና በእምነት በመታገዝ የቻላችሁትን ያህን አስተዋጾን እንድታበረክቱ ይጠይቃል። እያንዳንዳችሁ፣ ‘በእርግጥም ኢየሱስ ከእኔ የሚፈልገው ነገር አለ ወይ’? ብላችሁ ራሳችሁን እንድትጠይቁ አደራ እላችኋለህ። አገራችሁስ ማዳጋስካር በእናንተ ላይ ተስፋ አድርጓል?

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻችን እንድንባዝን አይፈልግም። ለሐዋርያዊ ተልዕኮ ሲያሰማራን ብቻችንን አይልከንም። ኤሊሳ ይህን በገሃድ አሳይታናለች። ሐዋርያዊ ተልዕኮን ብቻችንን የምንወጣው አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየንን የፍቅር እና የእምነት መንገድ ከሌሎች ጋር መካፈል ይኖርብናል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚኖረን የግል ግንኙነት አስፈላጊ ነው፤ እንዲሁም በተጨማሪ ከሌሎች ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በሕብረት ወደ እርሱ መቅረብ ያስፈልጋል። በርካታ መልካም ነገሮችን ብቻችን ማከናወን የምንችል ቢሆንም ከሌሎች ጋር በመተጋገዝ ሲሆን ያልተጠበቀውን እና ከአቅም በላይ መስሎ የሚታዩ ሥራዎችን ማከናወን እንችላለን። ወጣት ኤሊሳ እንደተናገረችው ኢየሱስን ማየት የምንችለው ሌሎች ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በመመልከት ነው ብላለች። እምነታችንን ከቤተሰቦቻችን ጋር ስንካፈል፣ ወንድማዊ አንድነትን ስንመሰርት፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካከል ያለውን ሕይወት በጋራ ስንካፈል፣ እርስ በእርስ ስንረዳዳ ኢየሱስ በመካከላችን መሆኑን፣ እርሱን መመልከት እንችላለን። ይህን የምናደርግ ከሆነ ኢየሱስ የሚያሳየን እና ያዘጋጀልን የሕይወት ጎዳና የቱ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። መለያየት በመካከላችሁ አይኑር፤ የአብሮነትን እንጂ የብቸኝነትን ሕይወት መኖር የለባችሁም። የብቸኝነት ሕይወት ከሌሎች ሊያጋጥሟችሁ ከሚችሉ ፈተናዎች መካከል አንዱ ነው።

ከሌሎች ጋር በማሕበር ስንኖር በየዕለቱ የሚከሰቱ አስደናቂ ነገሮችን፣ ኢየሱስን መውደድ እና መከተል መልካም መሆኑን እናውቃለን። እንደ ኤሊሳ ወላጆች፣ የኤሊሳ ወላጆች የተለያዩ ጎሳ አባላት ቢሆኑም፣ የራሳቸውን ልማድ እና ወግ በጋራ በመኖር፣ ፍቅራቸውንም በማጠንከር ልዩነታቸውን ለማስወገድ በቅተዋል። ይህን በማድረጋቸው ጥሩ ምሳሌ ሆነውላችኋል። በየዕለቱ የሚያደርጉት ጉዞ ፍሬን በማስገኘቱ፣ ይህን የምድር ፍሬ ወደ መንበረ ታቦት ይዘው እንዲቀርቡ አግዟቸዋል። ይህን የመሰለ ምስክርነትን መመልከት ምን ያህል መልካም እና አስፈላጊ ነው። ከሌሎች ወዳጆቻችሁ፣ ከትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪዎቻችሁ እና ከቁምስናችሁ መሪ ካህን በኩል የሚደረጉ እገዛዎች በእምነት እንዲትጠነክሩ ትልቅ አስተዋጽዖን ያደርጋሉ። እነዚህ እገዛዎች በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ እንድትሰጡ ያግዛሉ። ሁላችንም እንደየችሎታችን አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮችን ለሌሎች ማበርከት ስለምንችል፣ ከመካከላችን ማንም አንተ አታስፈልገኝም ወይም አንቺ አታስፈልጊኝም በማለት የብቸኝነትን ሕይወት መምረጥ አንችልም። በሕብርት በመጓዝ፣ የፈጠረን የእግዚአብሔር አባታችን የፍቅር እቅድ ተግባራዊ መሆን ያስፈልጋል።

እያንዳንዳችሁ ‘አንተ አታስፈልገኝም፣ አንቺ አታስፈልጊኝም’ ማለት እንደሌለባችህ መገንዘብ ይኖርባችኋል። ምክንያቱም ሁላችሁም ውድ እና ጠቃሚ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ። ንግግሬን ከማጠቃለሌ በፊት አንድ ነገር ላስገነዝባችሁ እፈልጋለሁ። እኛ ሁላችን የአንድ ቤተሰብ ልጆች ነን፤ ስለዚህ አንድ እናት እንዳለችን እናውቃለን። እርሷም የማዳጋስካር ባልደረባ ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ፈቃድ አሜን ብላ መቀበሏን ዘወትር አስባለሁ። ይህን መልስ በሰጠችበት ጊዜ ማርያም እንደ እናንተ ወጣት ነበረች። የመልአኩ ገብርኤል ሰላምታ በደረሳት ጊዜ ‘እንደ እርሱ ፈቃድ ይሁንልኝ` አለች እንጂ እስቲ እመለከተዋለሁ በማለት አላንገራገረችም ወይም የጊዜ ቀጠሮ አልሰጠችም። ለማንኛውም እንቅፋት ሳይፈሩ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብቻ ለመፈጸም ቆርጠው የተነሱት ሰዎች መልስ ሁል ጊዜ አዎ የሚል ነው። እናታችን የሆነች የናዝሬቷ ወጣት ድንግል ማርያም የልጆቿ የሕይወት ጉዞ ብርሃን እንዳይጨልም ዘወትር በመከታተል ላይ ትገኛለች። ለማዳጋስካር ወጣቶች እና ለጓደኞቻቸው ያለን ምኞትም የተስፋ ብርሃናቸው ሳያቋርጥ ዘወትር በርቶ እንዲቆይላቸው ነው። ዓለም እያስከተለ ባለው ጥፋት ውስጥ የሚገኘውን የወጣት ትውልድ፣ የሚወዳት ማርያም ከላይ ከሰማይ ሆና ትመለከተዋለች። ተስፋውም እንዳይጨልምበት ዘወትር ጸሎቱን ወደ እርሷ ዘንድ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

የእያንዳንዳችሁን ሕይወት፣ የቤተሰቦቻችሁን እና የጓደኞቻችሁን ሕይወት ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደራ እሰጣለሁ። ለመንገዳችሁ ብርሃን እና ተስፋ እንዲበዛላችሁ፣ እግዚአብሔር ለማዳጋስካር ሕዝብ ያዘጋጀው እቅድ እንዲፈጸም፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጉዞአችሁ መሪ እና ጠባቂ እንድትሆናችሁ ጸሎቴን አቀርባለሁ፤ እናንተም በጸሎታችሁ አስትውሱኝ” በማለት ንግግራቸውን ፈጽመዋል።                                                           

09 September 2019, 18:07