ፈልግ

በብራዚል የአማዞን ደን፣ በብራዚል የአማዞን ደን፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለፍጥረታት እንክብካቤ የሚያግዝ አዲስ ስምምነት ይፋ አደረጉ።

ለምንኖርባት ምድራችን የምናደርገውን ጥበቃ እና እንክብካቤ ይበልጥ እንድናሳድግ በማሰብ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሌላ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ቀን ይፋ ማድረጋቸው ተገለጸ። ግንቦት 6/2012 ዓ. ም. ለፍጥረት የምናደርገውን እንክብካቤ እንድናሳድግ የሚያግዙ ትምህርቶችን በስፋት ባማዳረስ “ዓለም አቀፉን የትምህርት ስምምነት እንደገና መገንባት” እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የቅዱስነታቸው ዓላማ ከጥር 26/28 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ በአቡ ዳቢ፣ የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች በተሰበሰቡበት ወቅት የተረቀቀው እና ከእርሳቸው ጋር ሆነው የግብጹ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም የሆኑት አል ጣይብ ፈርመው ያጸደቁትን የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ ሃሳብ የሚያጠናክር መሆኑን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ ሚኬሌ ራቪያት የላከልን ዘገባ አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ ተፈጥሮን በመጠበቅ እና በመንከባከብ ረገድ የሚሰጡ የትምህርት እና የግንዛቤ መስጫ ስምምነቶች ዓለማቀፋዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ፣ አዳዲስ ሃሳቦች እንዲመነጩ ዕድል የሚሰጥ፣ የተለያዩ ችግሮችን በማለፍ የምንኖርባትን ምድር ወደ ተሻለ ደርጃ ለማድረስ የሚያግዝ መሆኑ ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ በቀዳሚነት የሚመለከተው በማስተማር ሥራ ላይ የተሰማሩትን እና በተፈጥሮ ጥበቃ እና እንክብካቤ ዘርፍ ሳይንሳዊ ጥናቶችን የሚያካሂዱ ጠበብትን እና በሕዝባዊ ተቋማት ዓለም አቀፍ ሃላፊነትን ይዘው ለመጭው ትውልድ የወደ ፊት ሕይወት የሚጨነቁትን በሙሉ በግንቦት 6/2012 ዓ. ም. በቫቲካን የሚካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤን ለማሳተ መሆኑ ታውቋል።

የዓለማችንን የወደ ፊት ዕድል ማስተካከል፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የጋራ ውይይቶችን በማስፋት እና በማሳደግ ሰፊ ግንዛቤ የሚሰጥበት መድረክን ማዘጋጀት እና በዘርፉ ብቁ የሆኑ ባለሞያዎችን በማፍራት ሊፈጠሩ የሚችሉትን እንቅፋቶች ተሻግሮ መግባባት የሚገኝበትን ሰብዓዊ ወንድማማችነትን ለመገንባት መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባቀረቡት ጥሪ እንዳስገነዘቡት በዓለም ሕዝቦች እና በጋራ መኖሪያችን መካከል ግንኙነትን በመፍጠር ነዋሪዎቿም አስፈላጊውን ክብር እንዲሰጧት ለማድረግ ነው ብለዋል። ይህ በሁለቱ መካከል የሚደረግ ግንኙነት ሰላምን፣ ፍትህን፣ በእምነት ተቋማት መካከልም የጋራ ውይይቶችን በማድረግ ሰብዓዊ ቤተሰብን በመፍጠር፣ አንዱ ሌላውን በፍቅር ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ፈጣል ለውጥን ለመቋቋም የሚያግዝ እውቀት፣

በትምህርት አማካይነት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጥሪ በዘመናችን የሚታየው እና ዲጂታሉ ዓለም ያስከተለውን ፈጣን የባሕል ለውጥን ለመቋቋም ያግዛል ተብሏል። ይህ ፈጣን የባሕል ለውጥ አዳዲስ በሚፈጠሩ አገላለጾች አማካይነት ከዚህ በፊት የተገኙ ባሕላዊ እሴቶች እንዲጠፉ በማድረግ መሠረታዊ መነሻችንን በማዘናጋት ላይ እንደሚገኝ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ውዳሴ ላንተ ይሁን የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችሶስ፣ ሰብዓዊ ማንነት የራሱን እና የስነ-ልቦናዊው መዋቅርን በማጣት ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልጸው አሁን እየታየ ያለው ፈጣን ለውጥ ባዮሎጂካዊ እና ተፈጥሯዊ ለውጥን የሚቃረን ነው ብለዋል።     

የትምህርት ምስጫ መንደር፣

ይህ ፈጣን ለውጥ ይላሉ ቅዱስነታቸው፣ ይህ ፈጣን ለውጥ ሁሉም ሰው ሊሳተፍ የሚገባውን የትምህርት እና የግንዛቤ ጥረት ሊኖር እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ አንድን ሕጻን ለማስተማር አንድ መንደር ያስፈልጋል የሚለውን የአፍሪቃዊያንን አባባል ጠቅሰው፣ የትምህርት መስጫ መንደር ሲባል በመንደሩ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ልዩነታቸውን አስወግደው በመካከላቸው ያለውን ሰብዓዊ ግንኙነቶችን በማሳደግ ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በጋራ ለመካፈል ይረዳል ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ  የጸደቀው የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ሰነድ፣ ለምንኖርባት ምድራችን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ምዕመናኖቻቸው ጋር በመተባበር፣ በወንድማማችነት መንፈስ ብዙ ማበርከት የሚቻል መሆኑን አስገንዝበዋል።

12 September 2019, 16:38