ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የአእምሮ መርሳት ሕመም ያለባቸውን በጸሎታቸው አስታወሱ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ መስከረም 7/2012 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባቀረቡበት ወቅት በአእምሮ መርሳት ሕመም የሚሰቃዩትን አስታውሰዋል። መጭው ቅዳሜ መስከረም 10/2012 ዓ. ም. በዚህ ሕመም የሚሰቃዩት የሚታሰቡበት ዕለት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በዚህ ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች ክብራቸውን በሚቀንስ የአመጽ፣ የመደፈር እና ባጠቃላይ የጭካኔ ተግባር ሰለባ ስለሚሆኑ መጸለይ ያስፈልጋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማሳሰቢያቸው በእነዚህ ሰዎች ላይ ጥቃትን ለሚፈጽሙ ሰዎች ልብ መለወጥ እንጸልይላቸው ብለው ለሕመሙ ተጠቂዎች እና ለቤተሰቦቻቸውም፣ ያለመሰላቸው በፍቅር መልካም እንዲያድርጉላቸው እንጸልይ ብለዋል።

እንደ ዓለም አቀፉ የአእምሮ መርሳት ሕመም ተንከባካቢ ድርጅት ያለፈው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. ሪፖርት መሠረት በዓለማችን ሃምሳ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ከአእምሮ ጋር በተያያዘ ሕመም የሚሰቃዩ ከእነዚህም መካከል ሁለት ሦስተኛው በአእምሮ መርሳት ሕመም የሚሰቃዩ መሆናቸው ታውቋል። በየዓመቱ ታስቦ የሚውለው ዓለም አቀፍ የአእምሮ መርሳት ሕመምተኞች ቀን ሕመሙን በተመለከተ በዓለም ዙሪያ ግንዛቤን ለማስያዝ በርካታ ዝግጅቶች የሚቀርቡበት ዕለት መሆኑ ታውቋል። በዚህም የተለያዩ ድርጅቶች ሕመሙን ለመቋቋም ድጋፍ የሚያደርጉበት እና በሕመሙ የሚሰቃዩትንም ለመርዳት ጥረት የሚያደርጉበት አጋጣሚ እንደሚሆን ታምኖበታል።         

18 September 2019, 18:38