ፈልግ

ቅዱስነታቸው ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት፣ ቅዱስነታቸው ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት፣ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እግዚአብሔር ሕይወታቸውን መልሰው ለመገንባት የሚጥሩትን ያግዛል”!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማክሰኞ መስከረም 13/2012 ዓ. ም. በሮም አቅራቢያ፣ ፍሮሲኖኔ ከተማ ውስጥ የ “ኑዎቪ ኦሪዞንቲ” ወይም “አዲስ አድማስ” ተብሎ በሚጠራ ማዕከል ውስጥ ገብተው በማገገም ላይ የሚገኙትን በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል፣ ከነበሩበት አስከፊ ሕይወት ወጥተው አዲስ ሕይወት ለመገንባት ጥረት የሚያደርጉትን በሙሉ እግዚአብሔር የሚያግዛቸው መሆኑ አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለማዕከሉ ነዋሪዎች የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ በተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከተ ወንጌል፣ ምንም እንኳን በሕይወት ጉዞ የመውደቅ እና ተስፋ መቁረጥም ቢያጋጥማቸው፣ ከዚያ ሁሉ ለመውጣት ብለው የሚያደርጉትን ጥረት ሳያቋርጡ እንዲገፉበት መክረዋቸዋል። ቅዱስነታቸው ምክራቸውን የለገሷቸው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የማዕከሉ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት፣ በማሕበረሰቡ ውስጥ የተጎሳቆሉ፣ የደሄዩ፣ በተለያዩ ሱሶች የተጠቁ እና የአእምሮ ሕመም ያለባቸው እና ባሁኑ ጊዜ በማዕከሉ ውስጥ በማገገም ላይ ያሉ መሆናቸው ታውቋል።

በዕለቱ ከቀረቡት የቅዱስ መጽሐፍት ንባባት መካከል የመጀመሪያ በሆነው በመጽሐፈ እዝራ ምዕ. 6 ላይ፣ ሙሉ በሙሉ የወደመውን የእግዚአብሔር ቤት መልሶ ስለመገንባት በሚናገረው ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው መልሶ የመገንባት ሥራ ቀላል እንዳልሆን አስረድተው፣ በዚህ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሰው አይሁዶች ያንን የፈረሰውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መልሰው መገንባት መቻላቸውን እና ይህን ማድረግ የቻሉትም እግዚአብሔር አብሯቸው ሆኖ ስለ ረዳቸው ነው ብለዋል። አክለውም የፈረሰውን መልሶ ከመገንባት ይልቅ አዲስ መገንባት እንደሚቀል አስረድተው፣ የፈረሰውን መልሰን መገንባት የምንችለው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል።  

በመከራ ውስጥ መኖርን ለምደናል፣

በሕይወት ውስጥ ውድቀት እንዳጋጠማቸው የተመለከቱት በርካታ ሰዎች ቀስ በቀስ ለማገገም ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ከዚህ ዓይነት ውድቀት ለመውጣት የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አስረድተው ይህ ካልተደረገ ግን በወደቁበት ይቀራሉ ብለዋል።

መልሶ የመገንባቱ ሥራ ለሁሉም ሰው ምቹ እና ቀላል እንዳልሆነ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ቀን ላይ የተገነባውን ግድግዳ በሌሊት ነጋዴዎች ማፍረሳቸውን የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አስታውሰው፣ ያንን የፈረሰውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግድግዳ መልሰው ለመገንባት የተጠቀሙት ዘዴ፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አገላለጽ፣ ቤተ መቅደሱን ዳግም ከመፍረስ ለመከላከል ብለው በአንድ እጃቸው ድንጋይ እያቃበሉ በሌላኛው እጃቸው ጎራዴን ይዘው እንደነበር አስታውሰው ቤተ መቅደሱ ዳግም ከመፍረስ የተረፈው የግንባታ ሥራው ሳይቋረጥ በተጨማሪም ጠንካራ ጥበቃ እየተደረግለት በትግል እንደሆነ አስረድተዋል።

የወደቀን ሕይወት መልሶ መገንባት እግዚአብሔር ምንም ሳይሰስት የሚሰጠው ጸጋ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ይህን የእግዚአብሔር ጸጋ እንዳይወስዱብን ወይም እንዳያጠፉብም መስዋዕትነት ከፍለን መጠበቅ እና መከላከል ያስፈልጋል ብለው የእግዚአብሔር ሰዎች ወደ ፊት ለመጓዝ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ዳግም ውድቀት እንደሚያጋጥማቸው አስታውሰው በዚህን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ደርሶላቸው ከወደቁበት በማንሳት ቤዛቸው  እንደሚሆናቸው አስረድተዋል።

ኢየሱስንም ውርደት ገጥሞታል፣

ኢየሱስ ክርስቶስም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለውርደት መብቃቱን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለውርደት፣ ለስቃይ እና ለሞት የተዳረገ ቢሆንም ይህን ሁሉ አሸንፎ ለትንሳኤ የበቃውም በእግዚአብሔር ሃይል መሆኑን አስረድተዋል። ከማዕከሉ ነውሪዎች የቀረቡትን የሕይወት ምስክርነት ያዳመጡት ቅዱስነታቸው ሕይወትን መልሶ ለመገንባት የተጠቀሙት ሃይል ምስክርነት በእርግጥም መነገር አለበት ብለው ምክንያቱም ማንም ሰው ከሕይወት ውድቀት መነሳት የሚችለው የእግዚአብሔር ሃይል ሲታከልበት ነው ብለው የተስፋችን ምንጭም እግዚአብሔር ነው ብለዋል። እኛ የተስፋ ልጆች ነን ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኢየሱስም ወደዚህ ዓለም የመጣው የእግዚብሔርን ልጆች በሐጢ አት ከወደቁበት በማንሳት ለድነት እንዲበቁ ለማድረግ ነው ብለዋል። ስለዚህ በሕይወት መካከል ውድቀት የሚገጥማቸው ተመልሰው ለመቆም ፍላጎት ኣና ምኞት እንዲኖራቸው፣ ሊያነሳቸው በሚችል በእግዚአብሔር ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው አሳስበው ራስን ለውድቀት አሳልፎ እንዲሰጡ የሚገፋፋ ፈተናን በብርቱ መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ከማዕከሉ ነዋሪዎች ጋር በጸሎት የእግዚአብሔርን ጸጋ ለምነው፣ እግዚአብሔር የድል ባለቤት ነው፣ የትግል መሣሪያችንም እርሱ ነውና መሸነፍ እና ተስፋን መቁረጥ የለብንም ብለዋል። ይህን ከልባችን እንድንገነዘብ እግዚአብሔር ዘወትር ይርዳን በማለት የዕለቱን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል።              

25 September 2019, 17:18