ፈልግ

ቅዱስነታቸው በቴክኖሎጂ እድገት ላይ ለተወያዩ ምሑራን ንግግር ሲያደርጉ፣    ቅዱስነታቸው በቴክኖሎጂ እድገት ላይ ለተወያዩ ምሑራን ንግግር ሲያደርጉ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የጋራ ጥቅም ከእያንዳንዱ ሰው ጥቅም ተነጥሎ ሊታይ እንደማይገባ አሳሰቡ።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ዛሬ በምንገኝበት የዲጂታል ዘመን ማሕበራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ” በሚል ርዕስ በሮም የተዘጋጀውን ስብሰባ የተሳተፉትን ምሑራን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው “የጋራ ጥቅም ከእያንዳንዱ ግለሰብ ጥቅም ተነጥሎ ሊታይ አይችልም” ብለው ስለ ቴክኖሎጂ እድገት በምናወራበት ጊዜ እና ውጤቱንም በምናይበት ጊዜ የቀድሞ አባቶች ያወረሱንን የስነ ምግባር እሴቶችን ከጥፋት የመከላከል እና ደህንነቱንም የመጠበቅ ሃላፊነት አለብን ብለዋል። ክብራት እና ክቡራን አድማጮቻችን፣ ከዚህ ቀጥሎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።   

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ብጹዓን ካርዲናሎች፣ ወድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

ይህን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቅድስት መንበር የባሕል ጉዳይ የሚመለከት ጳጳሳዊ ምክር ቤት በኩል የተዘጋጀውን ስብሰባ ለመሳተፍ የተገኛችሁትን በሙሉ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ይህን ስብሰባ ለማዘጋጀት ለተነሳሳችሁት ለብጹዕ ካርዲናል ፒተር ታርክሰን እና ለብጹዕ ካርዲናል ራቫሲ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። በቴክኖሎጂው ዓለም ከፍተኛ እድገትን በማሳየት ላይ ያለው በተለይም ሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታ፣ በሰዎች ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ የሆኑ ተፅእኖዎችን እያስከተለ ይገኛል። በመሆኑ በዚህ ርዕስ ላይ ግልጽ እና ተጨባጭ የሆኑ ውይይቶችን ማድረግ ከምን ጊዜም በላይ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን በማስመልከት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክቴ መካከል አሁን ከደረስንበት የዲጂታል ዘመን ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መሠረታዊ ሃሳቦች ማቅረቤ ይታወሳል። የሰው ልጅ እነዚህን ከፍታኛ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙትን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አግባብ ባለው መንገድ መጠቀም የሚችለው አንዳንድ የሥነ ምግባር መርሆችን ሲያከብ ነው። የቴክኖሎጂ እድገትን ከስነ ምሕዳራዊ አመለካከት ጋር አንድ ላይ ማድረግ ከፍተኛ ሃላፊነትን ይጠይቃል።

ይህ ካልሆነ የቴክኖሎጂው እድገት በሌሎች ማሕበራዊ የእድገት አቅጣጫዎች ላይ ጫናን በመፍጠር በሰዎች ላይ ከፍተኛ ችግርን ሊያስከትል ይችላል። እስካሁን ባካሄዳችሁት ምርምር በኩል በማሕበራዊ ኑሮ መካከል ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን የሚያግድ እና መልካም ውጤትን የሚያስገኝ ተጨባጭ የውይይት ባሕል እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ብዙዎቻችሁ በቴክኖሎጂ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በሰው ሰራሽ አዕምሮ፣ በማሕበረሰብ ጥናት፣ በማሕበራዊ መገናኛ፣ በኤሌክትሮኒክ መረጃ ደህንነት፣ እንዲሁም በፍልስፍና ፣ በሥነ ምግባር እና በሥነ መለኮታዊ ሥነ ምግባር ሳይንስ ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የምትገኙ ናችሁ። እነዚህን የተለያዩ ዘርፎችን በመዳሰስ በየጊዜ የደረሳችሁበትን ደርጃ በማጤን ተጨማሪ እድገቶችን ከማሳየት በተጨማሪ በዘርፎቹ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችንም በመጠቆም፣ በተለይም በሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታ በኩል ሊከሰት የሚችለውን ችግር በመጠቆም የበኩላችሁን አስተዋጽዖን ማበርከት ትችላላችሁ። የእነዚህን ችግሮች አሳሳቢነት ተገንዝባችሁ፣ ውጤታማ የሆኑ ውይይቶችን እርስ በእርስ ለማድረግ፣ ግልጽነት በተሞላ መንገድ አንዱ ከሌላው ለመማር በመፈለጋችሁ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በዚህ ርዕሠ ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ዓላማ ያደርጋችሁትም የቴክኖሎጂ እድገት ባስከተላቸው የስነ ምግባር ችግሮች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እና አስፈላጊው እርምጃ የሚወሰድበትን መሠረታዊ መንገድ ለማሳየት ነው። በግሎባላይዜሽን እና የተለያዩ የዕውቀት ዘርፎች ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሱበት ባሁኑ ዘመን፣ አንዳንድ ተቀባይነት ያላቸውን መሠረታዊ መርሆዎችን ሁሉም ሰው ሊጋራ በሚችል ቋንቋ መግለጽ ምን ያህል ከባድ መሆኑን እገነዘባለሁ። ቢሆንም ተስፋን ባለመቁረጥ፣ ዘላቂ እድገቶችን ለማምጣት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተጠቀሟቸውን መልካም መርሆችን በመጠቀም ያሰባችሁትን ዓላማ ወደ ግብ ማድረስ ያስፈልጋል። ከፍተኛ ትኩረትን በመስጠት እየሰራችሁ ያላችሁባቸው የጥናት ዘርፎች በበርካታ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ የዓለማችን ሰዎች ሕይወት ላይ ፈጣን እና እውነተኛ ተጽዕኖን እንደሚያስከትል ይታመናል።

የሰውን ልጅ ከደረሰበት ችግር ለማላቀቅ አምነንበት በቆራጥነት የተነሳንባቸው ርዕሠ ጉዳዮች ወይም የጥናት ዘርፎች ሙሉ በሙሉ አዳዲስ ተግዳሮቶች ናቸው። በዘመናችን የተፈጠሩ አዳዲስ ችግሮች አዳዲስ የማቃለያ ዘዴዎችን ይፈልጋሉ። ለመሠረታዊ ሥርዓቶች እና ባህሎች ታማኝ በመሆን፣ እንቅፋትን ሊፈጥሩ የሚችሉ የሌሎች ሰዎች ዘዴ ከመጠቀም ይልቅ በአዳዲስ የፈጠራ ሥራ የታገዙ ፍሬያማ ጥናቶች ሊኖሩ ይገባል። መሠረታዊ የሆኑ ሥነ-መለኮታዊ እና ተግባራዊ የሞራል መርሆዎች ይፋ በመደረግ ማሕበራዊ ጥቅምን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖን መፍጠር እንደሚችሉ የበኩሌን እምነት መግለጽ እወዳለሁ። ሰዎች የሚመኟቸውን መልካም ነገሮችን ማግኘት እንዲችሉ በማሕበራዊ ጥቅም ላይ ትኩረት ማድረግ እና እውቅናን መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው።

መፍትሄን ወይም አዎንታዊ ምላሽን እንድታገኙላቸው የተጠየቃችሁባቸው ማሕበራዊ ችግሮች መላውን የሰውን ልጅ የሚመለከቱ እና መፍትሄንም እንድታገኙላቸው የሚጠይቁ ናቸው። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት ሰው ሰራሽ አዕምሮ ወይም ሮቦት የምንላቸው ናቸው። በአንድ ወገን ለሰው ልጅ አስቸጋሪ እና ከባድ የሆኑ ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን፣ በተለይም ከኢንዱስትሪው አብዮት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የሰው ጉልበትን፣ አእምሮን እና ጊዜን የሚውስዱ የተለያዩ የሥራ ዓይነቶችን በቀላሉ በአጭር ጊዜ መካከል ማከናወን የተቻለ ሲሆን በሌላ ወገን ሮቦቶች ትርፍን በከፍተኛ ፍጥነት በማሳደግ እና በሥራው ዘርፍ የሰውን ጉልበት በመተካት የበርካታ ሰዎችን ሰብዓዊ ክብር አደጋ ላይ ጥለዋል።

ሌላ ምሳሌ የሚሆነው እነዚህ ሰው ሠራሽ አእምሮ ወይም ሮቦቶች ለሰው ልጅ የሚሰጡት ጥቅም እና የሚያስከትሉት ጉዳቶች ከሌሎች ማሕበራዊ ርዕሠ ጉዳዮች ጋር በመዳመር ከመወያያ ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ገብተዋል። የሰው ሰራሽ አእምሮን በመጠቀም አስተማማኝ እና ትክክለኛ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻልባቸው ይታመናል። በሌላ ወገን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አስተያየት አቅጣጫ እንዲለውጡ በማድረግ፣ ተቃራኒ ሃሳቦች ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ በሰላም አብሮ መኖርን የሚያረጋግጡ የሲቪል ተቋማት ላይ አደጋን በመደቀን ይታወቃሉ። በዚህ የተነሳ ስለ ቴክኖሎጂ እድገት በምናወራበት ጊዜ እና ውጤቱንም በምናይበት ጊዜ፣ ሌሎች ያወረሱንን የስነ ምግባር እሴቶችን ከጥፋት ተከላክለን ደህንነቱንም የመንከባከብ ሃላፊነት እንዳለብን እንገነዘባለን።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የፍትሃዊነት መጓደል ዋና መንስኤ የቴክኖሎጂ እድገት ከሆነ፣ እደገታችን እውነተኛ እድገት አደለም። የቴክኖሎጂ እድገት ለሰው ልጅ ማሕበራዊ ጥቅም ጠላት ሆኖ ከተገኘ ይህም ሕገ ወጥ የሆኑ እና በጉልበት ማስተዳደር ለሚፈልጉት ጨካኞች መልካም እድልን ይፈጥርላቸዋል። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ኤኮኖሚያዊ እድገትን፣ ትምሕርትን፣ ማሕበራዊ እና ባሕላዊ ለውጦችን ሊያመጡ የሚችሉ ብልጽግናን ለማምጣት ብላችሁ ለምታደርጉት ጥረታችሁ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

የሰውን ልጅ ክብር ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ የስነ ምግባር መሠረት ተክላችኋል። ማሕበራዊ ጥቅምም ከእያንዳንዱ ሰው ጥቅም ተነጥሎ የማይታይ አለመሆኑን አውቃችኋል። ሥራችሁ እና ጥረታችሁ በሙሉ ማንም ሰው ተነጥሎ ሳይታይ፣ እያንዳንዱ ሰው ስብእናውን አስከብሮ የማሕበራዊ እድገት ተጠቃሚ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ መቀጠል ይኖርበታል። በቴክኖሎጂው እድገት መልካም ስነ ምግባር ከታየ፣ ሃላፊነት እና የወንድማማችነት ፍቅር የታከለበት ከሆነ፣ ለሰው ልጅ እና ለመላው ፍጥረት ሙሉ እድገት በማምጣት መልካም ዓለምን መገንባት ይቻላል። ስብሰባችሁም የተባረክ እንዲሆን እመኛለሁ፤ በጸሎታችሁ እንድታስታውሱኝ አደራ እላለሁ”። በማለት መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
27 September 2019, 17:30