ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በአፍሪቃ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ንግግር አድረገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጳጉሜ 6 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በርካታ ምእመናን፣ መንፈሳዊ ነጋድያን እና የአገር ጎብኝዎች ባቀረቡት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ በሦስት የአፍሪቃ አገሮች፣ እነርሱም በሞዛምቢክ፣ በማዳጋስካር እና በሞሪሼስ ያደረጉትን 31ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ንግግር አድረገዋል። ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዕለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው ይነበባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

ወደ ሞዛምቢክ፣ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ ያደርኩትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽሜ ወደ ሮም ትናንት ተመልሼአለሁ። ወደ እነዚህ የአፍሪቃ አገሮች የተጓዘሁት የሰላም እና የተስፋ መንፈሳዊ ተጓዥ በመሆን፣ በዓለማች ለእውነተኛ ወንድማማችነት፣ ነጻነት እና ፍትህ መሠረት የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልዕክት ለማካፈል ነው። በሞዛምቢክ ባደርግሁት ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ወቅት ለመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ለፓርላማ አባላት፣ ለተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶች፣ ለሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና  ለሕዝባዊ ተቋማት ተወካዮች እና ለወጣቶች ባቀርብኩት መልዕክቴ በኩል በመካከላቸው ያለውን አንድነት በማጠናከር፣ በጋራ ሆነው ለጋራ ጥቅም እንዲሰሩ፣ ወጣቶች በበኩላቸው ለበርካታ ዓመታን በእርስ በእርስ ጦርነት የተጎዳችውን አገራቸውን መልሰው እንዲገነቡ፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ከእግዚአብሔር ለቀረበላቸው ጥሪ በልግስና የተሞላ አዎንታዊ መልስ እንዲሰጡ ብርታትን ሰጥቼአቸዋለሁ።

በማዳጋስካር ባደረግሁት ሐዋርያዊ ጉብኝቴ፣ ባሕላቸው በሚጠይቀው የአንድነት እና የመረዳዳት ልማድ በመመራት፣ ለሚኖሩባት ምድራቸው እና ለማሕበራዊ ፍትህ ክብርን እና ቦታን በመስጠት ለአገራቸው እድገት በርትተው እንዲሰሩ የሚያበረታታ እና ተስፋን የሚሰጥ መልዕክቴን አካፍዬአለሁ። በማዳጋስጋር የሚገኙ መነኮሳት፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም ወጣቶች ከእግዚአብሔር ዘንድ ለቀረበላቸው ጥሪ በቸርነት አዎንታዊ ምላሽን እንዲሰጡ ብርታትን ሰጥቼአቸዋለሁ።

በመጨረሻም የበርካታ ባሕል አገር በሆነች በሞሪሼስ ባደረግሁት ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ወቅት በአገሪቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት በመመልከት አድናቆቴን የገልጽኩላቸው ሲሆን በዚያች አገር ባቀረብኩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወቅት የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል በማስተንተን ብጽዕና ለኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለሆንን ለእኛ ክርስቲያኖች መለያችን መሆኑን እና የሰላም እና የተስፋ ምንጭ መሆኑን በመልዕክቴ አስገንዝቤአለሁ።

ስለዚህ በእነዚህ ሦስት የአፍሪቃ አገሮች ማለትም በሞዛምቢክ፣ በማዳጋስካር እና በሞሪሼስ ባደረግሁት ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ወቅት የተዘራው ዘር መልካም ፍሬን አብዝቶ እንዲሰጥ ወደ እግዚአብሔርን ዘንድ ጸሎታችን እናቅርብ” ብለዋል።      

ር. ሊ. ጳ. ጳጳስት ፍራንችስኮስ በሦስቱ የአፍሪቃ አገሮች ያደረጉትን 31ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት በቫቲካን በሚገኝ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን ያሰሙትን ንግግር ከፈጸሙ በኋላ በአደባባዩ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በዚህም መሠረት ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች ለመጡት ነጋዲያን፣ በተለይም ከእንግሊዝ፣ ከስኮትላንድ፣ ከአይርላንድ፣ ከደንማርክ፣ ከማልታ፣ ከኖርዌይ፣ ከስዊድን፣ ከዝምባቡዌ፣ ከሕንድ፣ ከማሌዢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከካናዳ እና ከሰሜን አሜሪካ ለመጡት ምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበው በአደባባዩ ለነበሩት በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ሰጥተዋል።

11 September 2019, 16:55