ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ክፋትን በመልካም ለማሸነፍ ዕድሉ አሁንም አለን”!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንት እሁድ መስከረም 11/2012 ዓ.ም፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ጋር በመሆን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አድረሰዋል። በዕለቱ ከሉቃ. ምዕ. 16:1-13 ተውስዶ በተነበበው የወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሰሙት ስብከታቸው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ክፋትን በመልካም ለማሸነፍ ዕድሉ አሁንም አለን”! ብለዋል። ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ይነበባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በሉቃ. 16፤1-13 ላይ የሚገኘው የዛሬው የቅዱስ ወንጌል ምሳሌ በአንድ ሃብታም ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ስለሚሰራ ብልህ እና ታማኝነት ስለጎደለው አስተዳዳሪ ይናገራል። ንብረቱን እንደሚያባክን ከሌሎች ሰዎች የሰማው ሃብታሙ አሰሪ ክስ አቀረበበት። መጋቢውም ጌታው ከሥራው እንደሚያሰናበተው ስለተረዳ፣ ያጎደለውንም ስለሚያውቅ ይግባኝ ከማለት ይልቅ በችግር ውስጥ ከመውደቁ በፊት ማድረግ ያለበትን በልቡ እንዲህ ሲል አሰበ። ምን ባደርግ ይሻላል? ማረስ እንደሆን አልችልም፤ መለመን ያሳፍረኛል ይልና ለመጨረሻ ጊዜ ጌታውን በስውር ሊዘርፍ ይነሳል። ስለዚህ የጌታውን ባለ ዕዳዎች አንድ በአንድ ጠርቶ ዕዳቸው እንዲቀነስ ያደርግና ከእነርሱ ጋር ወዳጅነትን በመፍጠር ወደ ፊት ውለታ ከፋዮች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ያቀረበው የመጋቢውን እምነት አጉዳይነት ለማሳየት ሳይሆን ብልህነቱን ለማሳየት ፈልጎ ነው። ሃብታሙም ሰው እምነት ያጎደለውን መጋቢ በብልህነቱ አደነቀው። ምክንያቱም ብልጠቱን ከተንኮሉ ጋር በማዋሃድ ከደረሰበት ችግር ለመውጣት ጥረት አድርጓል። በዚህ ጥቅስ አማካይነት ኢየሱስ ሊናገረን የፈለገው መሠረታዊ መልዕክት፣ በሉቃ. 16:9 ላይ እንደተጠቀሰው “ስለዚህ በዚህ ዓለም ሃብት ወዳጆች አብጁ እላችኋለሁ፤ ይህን ብታደርጉ ገንዘባችሁ አልቆባችሁ ባዶ እጃችሁን ስትቀሩ ወዳጆቻችሁ ለዘላለም በሚኖሩበት ቤት ይቀበላችኋል” የሚል ነው። በሐሰት ወይም ሌሎችን በማጭበርበር የተሰበሰበ ሃብት ወይም ገንዘብ ወይም ንብረት በሙሉ ከዲያቢሎስ ነው።

በሃብት መበልጸግ በሰዎች መካከል ግድግዳን በማበጀት ልዩነቶችን ሊፈጥር ይችላል። ኢየሱስ በተቃራኒው ደቀ መዛሙርቱ ምንም ይሁን ምንም ያላቸውን ነገር አውጥተው ከሰዎች ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እንዲጠናክሩ ይመክራቸዋል። ምክንያቱም ከሃብት ይልቅ የበለጠ ዋጋ ያላቸው ሰዎች ናቸውና። በዕለታዊ ሕይወትም ያየን እንደሆነ መልካም ፍሬን የሚያፈራው ብዙ ንብረት ወይም ብዙ ገንዘብ ያለው ሳይሆን በእግዚአብሔር እርዳታ፣ በትክክለኛ መንገድ ሊያፈራ የቻለውን ያህል ሃብት በመጠቀም ብዙ ጓደኛን ማግኘት ወይም ከብዙ ሰዎች ጋር መልካም ግንኙነትን መፍጠር የቻለ ሰው ነው። ኢየሱስም ይህን እንዲህ በማለት አስገንዝቧል፥ “በዚህ ዓለም ሃብት ወዳጆች አብጁ፤ ይህን ብታደርጉ ወዳጆቻችሁ ለዘላለም በሚኖሩበት ቤት ይቀበላችኋል” (ሉቃ. 16:9)። የመንግሥተ ሰማይ ወራሾች ስንሆን በመንግሥቱ የምናገኘው እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር እርዳታ በትክክለኛው መንገድ ሰብስበን፣ በመልካም ሁኔታ አስተዳድረን በምናገኘው ሃብት አማካይነት ያፈራናቸውን ወዳጆቻችን ጭምር ነው።

ይህ የወንጌል ክፍል፣ ታማኝነቱን በማጉደሉ ምክንያት ከሥራው የተባረረውን እና “አሁን ምን ላድርግ ?” ብሎ የተጨነቀውን መጋቢ ወይም አስተዳዳሪ እንድናስብ ይጋብዘናል። በድካማችን እና በውድቀታችን ጊዜ ክፋትን በመልካም ለማሸነፍ ዕድሉ አሁንም እንዳለን ኢየሱስ ክርስቶስ ያረጋግጥልናል። ሌሎችን ያስጨነቀ እና ለእንባ ያደረሰ ቶሎ ብሎ ያስደስት፤ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ የበዘበዘ ወይም ያታለለ፣ ለተቸገረ ካለው ያካፍል። ይህን በማድረጋችን በእግዚአብሔር ምስጉኖች እንሆናለን። ምክንያቱም የእግዚብሔርን ልጅ የማወቅ ጥበብን በማግኘት የእርሱን ሰማያዊ መንግሥት ለመውረስ በመብቃታችን ነው።

ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊውን ሃብት እና ዘለዓለማዊውን ሕይወት ለመውረስ የምንበቃበት ጥበብ እንዲኖረን፣ በመጨረሻው የፍርድ ቀንም በምድራዊ ሕይወታቸው እኛ የረዳናቸው፣ በእነርሱ በኩል እግዚአብሔርን እንድናይ እና እንድናገለግለው ያደረጉን በሙሉ ምስክሮቻችን እንዲሆኑልን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን”።                                 

23 September 2019, 16:26