ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ወደ ማዳጋስካር ደርሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሞዛምቢክ ቀጥሎ ሁለተኛ አገር በሆነችው ማዳጋስካር ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ትናንት ጳጉሜ 1/2011 ዓ. ም. መድረሳቸውን የቫቲካን ዜና ማሰራጫ አስታውቋል። ቅዱስነታቸው ትናንት ከሰዓት በኋላ 10 ሰዓት ላይ ወደ አንታናናሪቮ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የማዳጋስካር ፕሬዚደንት እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት የክብር አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን የአበባ ጉንጉንም ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ማዳጋስካር በሰላም በመድረሳቸ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በማዳጋስካር ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የመረጡት መሪ ቃል “የሰላም እና የተስፋ ዘር ዘሪ” የሚል መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ 31ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሦስት የአፍሪቃ አገሮች በማካሄድ ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉባቸው ሦስቱ የአፍሪቃ አገሮች፣ ሞዛምቢክ ማዳጋስካር እና ሞሪሼስ እንደሆኑ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል። የአሁኑ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ቅዱስነታቸው የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡበት ከመጋቢት 4/2005 ዓ. ም. ወዲህ  በአፍሪካ አህጉር የሚያደርጉት አምስተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲሆን ከዚህ በፊት በህዳር ወር 2008 ዓ. ም ወደ ኬኒያ፣ ኡጋንዳ እና የመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ፣ ቀጥለውም በሚያዚያ ወር፣ 2009 ዓ. ም. በግብጽ ማካሄዳቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞዛምቢክ ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 1/2011 ዓ. ም. ድረስ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው የጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር ወደ ሆነችው ማዳጋስካር ትናንት ጳጉሜ 1/2011 ዓ. ም. በሰላም መድረሳቸውን ከቫቲካን ዜና ክፍል የደረሰን ዘገባ ገልጿል።

07 September 2019, 10:20