ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በተደረገ የእስረኞች ልውውጥ ተደስተዋል።

ር. ሊ. ጳ. ጳጳስት ፍራንችስኮስ ትናንት እሑድ መስከረም 4/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን ያሰሙትን የስብከተ ወንጌል አስተንትኖ ከፈጸሙ በኋላ በአደባባዩ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ከሰላምታቸው ባደረጉት ንግግር፣ በሩሲያ ፌዴረሽን እና በዩክሬን መንግሥት መካከል የተደረገው የእስረኞች ልውውጥ እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑንም ገልጸዋል። ይህን አስመልክተው የሚከተለውን አጭር ንግግር አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!

በሩሲያ ፌዴሬሽን እና በዩክሬን መንግሥት መካከል ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የእስረኞች ልውውጥ ባለፈው ሳምንት ተካህዷል። የሁለቱም አገሮች እስረኞች ወደየአገራቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት መብቃታቸው እጅግ አስደስቶኛል። በእነዚህ ሁለቱ አገሮች መካከል ጦርነትን የቀሰቀሰው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ እልባት እንዲያገኝ፣ በመካከላቸው ሰላም እንዲወርድ ሳላቋርጥ እጸልያለሁ።       

በፎርሊ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 1964 ዓ. ም. በ28 ዓመት ዕድሜዋ ያረፈች ወጣት ቤነዴታ ቢያንኪ ፖሮ ብጽዕና ይፋ ሆኗል። ሕይወቷን በሙሉ በሕመም ስትሰቃይ የኖረች ይህች ወጣት የደረሰባትን የሕመም ስቃይ ችላ የምትዘልቅበትን ችሎታ ከእግዚአብሔር በመቀበል የእምነት እና የፍቅር መስካሪ ልትሆን በቅታለች። ዛሬ በጀርመን፣ ሊምቡርግ ከተማም የአባ ሪካርዶ ሄንኬስ ብጽዕና ይፋ ሆኗል። እምነትን በሚቃወሙት ሰዎች በተሰነዘረው ጥቃት፣ አባ ሪካርዶ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1945 ዓ. ም. በጭካኔ የተገደሉ መሆናቸው ይታወሳል። የእነዚህ ሁለት ቆራጥ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምስክርነት እኛም የእምነት መንገዳችንን በቆራጥነት ተጉዘን ለቅድስና እንድንበቃ ያድርገን።

ከሮም እና አካባቢዋ እንደዚሁም ከተለያዩ አገሮች ለመጣችሁት ነጋዲያን ቤተሰቦች፣ የቁምስና ምዕመናን እና መንፈሳዊ ማሕበራት በሙሉ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ።

ከሆንዱራስ እና ከቦሊቪያ ለመጣችሁት ምዕመናን፣ ለአፍሪቃ እድገት በተለያዩ የንግድ እና የኢንቨስትሜንት ሥራ ላይ ለተሰማራችሁ እና በእነዚህ ቀናት ውስጥም በሮም ከተማ ለምትገኙት የአፍሪቃ ወጣቶች በሙሉ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ። ከፖላንድ አገር ለመጣችሁ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀስ መኪና ባለቤቶችም ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ።

የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆኑትን አባ ጃንፍራንኮ ኪቲን ለማስታወስ ለተሰበሰባችሁ የሚሊተሪ አባላት ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ። የቅዱስ የምሕረት አባት ደናግል ማሕበር ኣባላት፣ ከቨነዙዌላ ወዳጆች ጋር ለመጣችሁ፣ በኢጣሊያ ውስጥ የሞንቴኪዮ ኤሚሊያ ምእመናን፣ ምስጢረ ሜሮንን ለመቀበል ዝግጅት ላይ ለምትገኙ የክሮቶኔ ምእመናን እና በቅርቡ ወደ ሉርድ በሚደረገው ብሔራዊ መንፈሳዊ ጉዞ ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት ላይ ለምትገኙት በሙሉ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ።

በዚህ አደባባይ ለተገኛችሁት በሙሉ መልካም ዕለተ ሰንበትን እመኝላችኋለሁ” ካሉ በኋላ ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ” ብለው ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን በመስጠት የዕለቱን ስነ ስርዓት ደምድመዋል።  

16 September 2019, 17:48